ልጆቻችንን ያሳደግንበት እንዲጠፉ እንዲመክኑበት

 ✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል

ከቤት እመቤትነት ወደ "ኮርፖሬት" መካንነት የሚደረገው የትውልድ አልባው ሥልጣኔያችን ሩጫ የሚያጠፋን እንደኾነ አስተውለን ይኾን?

በሰላቢ እጆች ድረ ገጻችን ደጋግመን የምናነሳው ጭብጥ ውስጥ ለሀገር መገንቢያ መሰረቷ፣ የብልጽግናዋም ሀብቷ ቤተሰብ እርሱም ደግሞ በአባወራው የሚመራው እንደኾነ ነው።

ይህንን ተፈጥሮአዊ የኾነ እውነት “እንቢ” ብለው በራሳቸው “እውቀት” የታበዩቱ፤ ለዚያው ለታበዩበት እውቀታቸው ተላልፈው ተሰጥተው፤ ዛሬ ጥፋት ሙስናቸውን በቁጭት ይጨልጣሉ።

ለሄዱበት የጥፋት መንገድ አስጠንቃቂ፣ መካሪ ዘካሪ ቢላክላቸውም እነርሱ ግን ለመስማት አልፈቀዱም፤ አንድም በመረጡት የጥፋት መንገድ ቀድሞ ሄዶ፣ ጠፍቶ የታያቸው ምሳሌም የሚኾን ትውልድ አልነበራቸውምና የጥፋቱ ቀዳሚ ኾኑ!

ለእኛ ግን እንዲህ አይደለም! በርካታ ታሪክ ኾነው ሊቀሩ የደረሱ ጠፊ ትውልዶች ከፊታችን እያሉ፤ ከራሳቸው ጥፋት ሌላው ይማር ዘንድ የሚጽፉ፣ የሚናገሩ እያሉ፤ እኛ ግን የእነርሱን በሚያስንቅ እብሪት ትዕቢቱ ጥፋታቸውን ጥፋታችን ውድቀታቸውን ውድቀታችን አድርገን በከፍተኛ ፍጥነት እየተከተልናቸው እንገኛለን።

ማኅበረሰባችን እየተጋተ ባለው አጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት የሕልውና መሰረቱ እርሱም ቤተሰብ እየተናደ ይገኛል።

ሀገር የሚገነባበት ጡቡን፣ ትውልድ የሚታነጽበት ልኩን ይቀርጽ የነበረው የእናትነት ሚና ዛሬ ዛሬ በዘራብን ባዕድ አስተሳሰብ “ኋላቀርነት” ተብሎ፤ አንድም እናትነት “ደመወዝ የማይከፈልበት ሥራ ነው” ተብሎ እንዲፈረጅ፣ እንዲጠላና እንዲጣልም ተደርጓል።

ልጆቻችንን ወላድ የልጆች እናት የሚያደርጋቸውን “የቤት እመቤትነትን” ጠልተው በሥራና በትምህርት ከመውለድ ዘግይተው፣ እርግዝና ቢፈጠር እንኳ አጨናግፈው መካን የኮርፖሬት ባለሙያ የሚያደርጋቸው ክፉ ምክር ከሩቅ ሳይኾን እዚያው በቤተሰባቸው ከወላጆቻቸው መገኘቱ ከላይ በርዕሱ ያነሳሁትን የጥፋት ጉዟችንን ያፈጥነዋል።

ዛሬ የሴቶች ልጆቻችን ስኬት የሚለካው በሠሩት ማስትሬትና ዶክትሬት፣ ከቤታቸው ወጥተው ርቀው በሚውሉበት መሥሪያ ቤት፣ በደረሱበት የኮርፖሬት እርከን፣ በዝናና ገንዘብም ኾኗል።

“እንደህ ብለሽ ከቤት እንዳትውዪ፣ ልጅ ለማሳደግ ብለሽ ከቤት እንዳትቀመጪ...” ይሉት ዛሬምክር፤ ዛሬ የወላጆች፣ የቤተሰቦች፣ የአዛውንቱ፣ የንስሃ አባቶችም ምክር ኾኗል። ይህ የጥፋት ሰበብ በአጋጣሚ የመጣ እንዳይመስላችሁ ኾን ተብሎ “በተገመደልን” ራሳችንን በራሳችን እንድናጠፋበት በተዘጋጀልን “ገመድ” እንጂ!

ሴቶች ልጆቻችንን “ዶክተርና ኢንጂነር፣ አካውንታንትና አንተርፕረነር” እያልን በረጃጅም ፎቆች ላይ፣ በጠባብና በተጣበቀ ልብስ፣ በቀዝቃዛ ድንጋዮች (ግርግዳዎች) እና መስታዎቶች መካከል ማዋልና ማስመሸት ቁሳዊ ትርፍ አምጥቶልን ይኾናል፤ ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ በትውልዱ እድገት፣ በማኅበረሰቡ ልማትና በሀገር ብልጽግና ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትላል!

ልጆችን መውለድ፣ ዘርን መተካት፣ እነርሱም ሀገርን እንዲረከቡ፣ ትውልድን እንዲያስቀጥሉ አድርጎ ማነጽ የቤተሰቡ በተለይም የእናታቸው የማነፈይናቅና የማይተካ ሚና ኾኖ ሳ፤ ዛሬ ግን ሴቶች ልጆቻችንን ለአንድ ድርጅት ቁሳዊ ስኬት ሲሉ ይህንኑ በጊዜ፣ በዕድሜ ተገድቦ የተሰጣቸውን ጸጋ እንዲገብሩት፣ እንዲሰዉ በረቀቀ መንገድ ይገፋሉ።

እናት ልጆቿን የምታሳድግበትን፣ በምግባርና በትውፊት አሠልጥና የምታንጽበትን ውድና ምትክ አልባ ዕድሜዋን ለኮርፖሬት ተቋማት “የስኬት ሪፖርት” ስትገብ፤ ውጤቱ፦ ትውልድ አልባ መኾን ሲኾን፣ ቢኖረንም ደግሞ ማንነቱን የማያውቅ አንድም የተነጠለ ትውልድ ይኾናል።

ይህ የጥፋት ሙስናችንን መንገድ ያስጀመረን እብሪታችን ልጅ አልባ፣ ትውልድ አልባ አድርጎ የሚያስቀረን እብሪታችንን “ትምክህታችን” እንደኾነ እየቆጠርን ስንመጣ ጥፋት ሙስናችንም በዚያ የሚታተም ይኾናል።

ሴቶችን ከአባታቸው በተለይም ከባላቸው፣ ይበልጡንም ከልጆቻቸው ለይቶ የገንዘብ ትርፍ ለሚያስቀድም ተቋም ተቀጣሪ ማድረግ በሴቶች “እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” ሰበብ ትውልዱን ለጥፋት ያሰቡት ማርክሳውያን ሸፍጥ ነው።

እውነት ይህ ሳይገባን ቀርቶ ነው? ወይንስ ወደን ፈቅደን አባታቸው(ፈጣሪ) በአደራ በሰጠን በልጆቻችንና በትውልዱ ላይ የምንፈጽመው ግፍ ነው?

ራሳችሁን ጠይቁ!

“የኑሮ ውድነት ነው” አትበሉኝ የሞላ የተትረፈረፈ ሀብትና ንብረት ያላቸው ሳይቀሩ ሴቶች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት፣ ከኮሌጅም ኮሌጅ፣ ከሀገር ውስጥ ቀጣሪም ዓለማቀፍ “ግብረሰናይ” ተቋም አሳደው ለጥፋትና ሙስናው አሳልፈው የሚሰጧቸው አይደሉምን?

ሀገር የሚገነባው በማስትሬትና በዶክትሬት ሳይኾን በሰው ነው! ይህ የታነጸ ሙሉ ሰው ደግሞ መገኛው ያ የሀገር መገንቢያ ጡቡ ከኾነው ጠንካራ ቤተሰብ ነው!

ያ ጠንካራ ቤተሰብ ደግሞ ራሷን፣ ተፈጥሮዋን፣ ጸጋዋን፣ ልጆች የመውለጃ ጊዜዋን “ለቀጣሪዋ” በሰዋች በዚያም ልጅ አልባ በኾነ፤ አንድም የልጆቿን ጊዜ “ለአትራፊ ተቋማት” በገበረች፣ በሰጠች፣ በሰዋች እናት አይጸናም!

ዛሬ የምናሳድደውን “የኮርፖሬትም ስኬትም ኾነ የሀገር ብልጽግና” ነገ በቅቶ፣ ጸንቶ የሚረከበውና የሚያስቀጥለው ትውልድ እስካላገኘ ድረስ ስሙ “ጥፋት” እንጂ “ስኬት” ሊባል አይገባም!

👉 ጃፓንን፣ ደቡብ ኮርያን፣ ቻይናን፣ ጀርመንን፣ ጣልያንን ...ተመልከት! ከዚህ በፊት የጻፍኩልህንም ደግመህ ከልስ!

ሀገር በብልጽግና ጎዳና ላይ ደምቃ እንድትቀጥል የሚያደርጓት በመብራትና በቀለም የተንቆጠቆጡ ሕንጻዎቿ ሳይኾኑ በሰውነት ጥበቡ፦ሰው በመኾኑ ረገድ፤ የበለጸጉት ዜጎቿ ናቸው።

ያመጣን፣ ከዚህ ያደረሰንን ማርክሳዊ ሶሻሊስት ትውልድ አጥፊ ማኅበረሰብ አምካኝ ነቀርሳ መንግሎ ለመጣል ስርነቀል የኾነ የባህል አብዮት በሀገር ደረጃ ይፈልጋል።

አለበለዚያ በማኅበረሰባችን ውስጥ የገባበት ርቀቱ፣ የተንሰራፋበት ስፋቱ፣ የተጣበቀበት ጥብቀቱ፣ የታመነበት ምጥቀቱ ሳያጠፋን አይቀርም!

“ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን  ይቀድማል” ይላልና መጽሐፍ በአጉል የ”እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” እውቀት ታጅረው ከጠፉት መማሩ ይበጀናል!

እንቢ ብለን ስንጠፋ ግን ጣታችንን ሌሎች ላይ ከመቀሰር በፊት ራሳችንን መመልከቱ፣ ከእብሪታችን የተነሳ የመጣን የጥፋትና ሙስና ጽዋ ከተጠያቂነቱ ጋር መጨለጡ እንዲገባ ማስተዋል ያሻል!


Post a Comment

0 Comments