ታላቁ የእምነት አርበኛ 100 አለቃው



"...ድንገት ያ የቅፍርናሆም ጸጥታ በታላቅ የጭንቀት ድምፅ ተሰበረ። አንድ የሮማ መቶ አለቃ የኃይልና የሥልጣን ምልክት የሆነው የኩራት ካባውን ጥሎ በናዝሬቱ ኢየሱስ ፊት ተንበረከከ። ለራሱ ክብር ወይም ለወርቅ ወይም ሌላ የሥጋ ፍላጎት ጉዳይ ለመጠየቅ አልነበረም፤ በቤቱ በሞት አፋፍ ላይ ስላለውና እጅግ ስለሚወደው ብላቴናው (ሎሌው) እንጂ። ይህ የዛሬው ታሪክ ተራ የጌታና የሎሌ ፍቅር አልነበረም፤ የአሕዛብ እምነት በአይሁድ አደባባይ ላይ የበራበት፣ ቃለ መለኮት በኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ያለን በሽታ የገሠጸበት ድንቅ የወንጌል ታሪክ እንጂ!"

(ክፍል ፱ ጠያቂ ትምህርት!)

በቅፍርናሆም የታየው ድንቅ ተአምር!

​የመቶ አለቃው ሎሌ በታላቅ ስቃይ ላይ ሆኖ በሞትና በሕይወት መካከል ይዋልላል። መቶ አለቃው ወደ ጌታ መጥቶ “ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል” (ማቴዎስ ፰፥፮) ሲል ማለደ። ጌታም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።

​ነገር ግን የመቶ አለቃው መልስ ዓለምን ያስገረመ ነበረ። “ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል” (ማቴዎስ ፰፥፰)። ይህ ሰው ጌታ በአካል መገኘት እንደማያስፈልገው፣ ቃሉ ብቻ እንደ ሰይፍ ርቀትን ሰንጥቆ መፈወስ እንደሚችል አመነ። ጌታም ተደንቆ “በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ታላቅ እምነት አላገኘሁም” (ማቴዎስ ፰፥፲) አለ። በዚያች ሰዓት ቃሉ ወጣ፤ ብላቴናውም በሩቅ ካለበት አልጋ ተነሳ።

​በቀደመው ጊዜ፣ መዝሙረኛው ዳዊት “ቃሉን ሰደደና ፈወሳቸው” (መዝሙር ፱፯፥፳) ብሎ እንደተነበየው፣ ይህ መቶ አለቃ የቃሉን ኃይል ተረዳ። አንዳንድ መምህራን በሐተታቸው እንደሚተርኩት፣ መቶ አለቃው ጌታን የሰራዊት ጌታ እንደሆነ ተረድቶ ነው የተመለከተው። "እኔ ለበላይ ሥልጣን የምገዛ ሰው ነኝ... ከእኔም በታች ያሉትን ደግሞ አንዱን ሂድ ስለው ይሄዳል..." ማለቱ፣ ጌታም በበሽታዎችና በአጋንንት ላይ ፍጹም ወታደራዊ ትእዛዝ ያለው አምላክ መሆኑን ማመኑን ያሳያል።

​በብራናው ድርሳን ላይ በደማቅ ቀለም እንደተሳለው፣ ይህ መቶ አለቃ ለአይሁድ ምኩራብ ያሠራ፣ ሕዝቡንም የሚወድ ደግ ሰው ነበረ። 

መቶ አለቃው ጌታን ወደ ​ቤቱ ጣራ እንዳይገባ አትድከም ብቻ ቃል ተናገር ብሎ መከልከሉ፣ የሰውን ባሕርይ ዝቅተኝነትና የአምላክን ግርማ መለኮት የሚያሳይ የትሕትና ምስጢር ነው። አባቶቻችን እንደሚሉት፣ መቶ አለቃው ጌታን ወደ ቤቱ ባያስገባውም፣ በልቡ ውስጥ ግን ግርማዊ መንበሩን አዘጋጅቶለት ነበረ። ለዚህ ነው ጌታ ከአይሁድ ይልቅ ታላቅ እምነት ያለው ብሎ ለዚህ ለአሕዛብ መቶ አለቃ የመሰከረው።

​ዛሬ በምንኖርበት በዚህ በመጨረሻው የመከራ ዘመን፣ ነፍሳችን እንደ መቶ አለቃው ብላቴና በኃጢአት ሽባ ሆናለች። ዓለም ሁሉ በበሽታ፣ በጦርነትና በጭንቀት ትታመሳለች። የመጨረሻው መከራ ምልክቱ፣ የጌታን የፍርድ ቃል መናቅ፤ በምድራዊ መድኃኒትና በግል መፍትሔ የሌላቸው መፍትሔዎች ብቻ መታመን ነው።

​“እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” (ዕብራውያን ፲፩፥፩) እንደሚል፣ ዛሬ እንደ መቶ አለቃው "ቃል ብቻ ተናገር" የሚል ጽኑ እምነት ያስፈልገናል። መከራው ቢበረታ፣ በሽታው ቢጠና፣ የጌታ ቃል ዛሬም በኢትዮጵያ አድባራትና ገዳማት ከተማዎችና ገጠሮች ባለስልጣናትና ሕዝባውያን እንዲሁም ሀብታምና ድሆች ሁሉም ላይ በዓለም ዙሪያ ይሠራል። የጌታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ የአብርሃሙ ሥላሴን ፈቃድና ቃል ወደ ቤትህ (ወደ ሕይወትህ) ለማስገባትና በተግባር ለሕጉና ለትዕዛዛቱ ለመገዛት ስትጀምር በዛ ላይ የመቶ አለቃው ትሕትና ካለህ፣ ሽባ የሆነው ሕይወትህ በቅጽበት ይነሳል። ከአንተም አልፎ ለሞት የቀረቡትን የምትጠግን መድኃኒት ያደርግሃል።

🔔 ከዚህ የወንጌል ብርሃን በመነሳት እነዚህን የእኛን ሕይወት የሚዳስሱ ጥያቄዎች እናሰላስል፦

▫ ​"አንባቢ ሆይ! ዛሬ በዚህ በመጨረሻው ዘመን፣ ከግል ፍልስፍናህ ይልቅ እንደ መቶ አለቃው በጌታህ 'ቃል' ብቻ ትታመናለህ? ወይስ ጌታችንን በአካል ካላየሁት ወይም ተአምር (ድንቅ ነገር ካልተደረገልኝ) በእጄ ካልጨበጥኩ ኃይሉን አላምንም ትላለህ?"

▫ ​"በቤትህ (በልብህ) ውስጥ በሩን በጉልበትህ ዘግተህ ጌታን እንዳይገባ የምታደርግበት ትዕቢት ተጭኖሃል? ወይስ እንደ መቶ አለቃው ለክብርህ ሳትጨነቅ በትሕትና ተንበርክከህ 'ጌታ ሆይ ቃል ብቻ ተናገር ሁሉ ይቻልሃል'  ትላለህ?" በቀጣይ ክፍል እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን!

Post a Comment

0 Comments