የማይካድ የማይደፈር ስብዕና



ሔኖክ ኃይለገብርኤል

በወሬና በጉራ ሳይኾን በተግባር የተፈተነ የኩሩ ስብዕና ባለቤቱ አባወራ!

አባወራነት በእኛ ዐውድ በዕድሜ ብዛት ወይንም በጋብቻ የሚገኝ የተለመደ ስም ሳይኾን በዕለት ተዕለት ፍልሚያ፣ ጭካኔ፣ ሥነ-ሥርዓት የሚገነባ የማይናወጥ ማንነት ነው።

የዚህ ኩሩ ስብዕና ባለቤት መኾን ማለት በወሬ ማዕበል የማይናወጥ፣ በችግር ዶፍ የማይበገር፣ በምስጋና ጎርፍ የማይሸረሸር፣ በብቸኝነት ጨለማ የማይደነግጥና በተግባር የተፈተነ ዐለት መኾን ማለት ነው።

አንድ አባወራ የቤቱ መሪና ቋሚ ምሰሶ ነው። የእርሱ ስብዕናው የማይደፈር ሲኾን፣ ቤተሰቡ በእርሱ ጥላ ስር የደኅንነት ስሜት ይሰማቸዋል።

በመከራ እቶን ውስጥ ሲያልፍ የማይበረከረክ፣ ዳገቱ ሲበዛ የማይቆም ስብዕና ካለው፣ የሚመራው አካል፡-ቤተሰቡ ሁሉ በእርሱ ይተማመናል።

የእርሱ መሪነት በሚስቱም ኾነ በልጆቹ ከሚያንባርቀው ጨኸቱ ሳይኾን ማንም ሊክደው ከማይችል ጽኑ አቋሙ (ስብዕናው)ይመነጫል፡፡

ይህ ደግሞ እንደአባትነቱ ወደዚህች ምድር ላመጣቸው በተለይ ይህንኑ ስብዕና የሚያወርስ ይኾናል፡፡ የማይካድ ስብዕና ያለው አባት ለልጆቹ የሚነበብ መጽሐፍ፣ የሚመላለሱበትም መንገድ ይኾንላቸዋል፡፡

ልጆቼ “ታማኝ ኹኑ” ብሎ አይሰብክም፤ ለቃሉ ታማኝ፣ ያለውን ፈጻሚ፣ ካፉ የወጣውን ጠባቂ በእርሱም ጎንም ቋሚ ኾኖ ይገኛል።

እንዲሁም ልጆቼ “ጠንክሩ፣ በርቱ፣ አትፍሩ” ብሎ ብቻም አይመክርም ይልቁንስ በሥራው አርበኝነት፦ ድፍረትን፣ ጽናትን፣ ቆራጥነትን፣ ጥንካሬን ያሳያል እንጂ።

በዚህ የማይካድ የማይደፈር ስብዕናው አርአያ ኾኖ ያሳደጋቸው ልጆቹ እርሱ በሌለበት፣ በዓለም አደባባይ ቀና ብለው የሚሄዱ ልበሙሉዎች ይኾናል፡፡ በአካሄዳቸው አስተዳደጋቸው፣ አፋቸው ሲከፈትም የሠለጠነ ልባቸው ይታያል።

በአባታቸው የማይታጠፍ ኩሩ ማንነትም ታንጸው ያደጉት ልጆቹ በገንዘብ፣ በጥቅም ተደልለው አልያም በስስትና በእስር ተይዘው ቃላቸውን የማያጥፉ፣ ኪዳናቸውን የማይሽሩ ይኾናሉ፡፡

ሚስቱ ክብሩ የኾነችለት ይኸው አባወራ የእርሱ የኾነውን ሁሉ በሕይወቱ ተወራርዶ ይጠብቃልና ይጠብቃታል፣ አያስደፍርምና ጥቃቷን ይመክታል። የሚስቱን፣ የቤቱን፣ የሀገሩን ክብር ለባዕድ አሳልፎ የሚሰጥበት አንዳችም ስንፍና አልያም ቸልተኝነት የለበትም።

ይህንን የመሰለ ኩሩ፣ ጠንካራና የማይደፈር ስብዕና ከወንዱ፣ በተለይም ከአባወራው ዘንድ ካላሰረጸ በልቡም ካላደረ፣ በቃላት ልንገልጸው የማንችለው የታሪክና የሞራል ክስረት ይከተላል።

ታናሼ አስተውል! ስብዕናህ የማይካድ የማይደፈር ጠንካራም መኾኑ ቀርቶ ልልና ቀላጭ ሲኾን ቤትህ መቅኖ ያጣል። ክብር የሚባለው ከቤትህ ይጠፋና “መተዛዘንና መተቃቀፍ” በዝቶ ስንፍናና ዋልጌነት፣ ቸልታና ግዴለሽነት ይሠለጥናሉ።

ቃሉን የማይጠብቅ አባት ባለበት ቤት ውስጥ ልጆች የሚማሩት እንደ “አሳ” መሙለጭለጭን፣ እንደ እስስት መለዋወጥን፣ እንደ ድመት ማላዘንን ይኾናል።

እርሱም “ይህ ክፉ ዓመሌ ነው” ብሎ እንደማይታዘበው፣ እንደማይጠላውና እንደማይጥለው ጭራሽም እንደ ችሎታና “የመኖር ዘዴ” እንደሚለው ሁሉ፤ ልጆቹም ማታለልን፣ አስመስሎ መናገርን፣ አስታኮ መጉረስን፣ አሳቦ መተንኮስን “ይጠበቡበታል”።

ከእነርሱም ጋር ምንም ዓይነት ቁምነገርን “ነው ወይም አይደለም” ብሎ በውል ለማሰር አስቸጋሪ ይኾናል። ሰው መኾንን ሳይኾን ሰውን መደለል፣ መሸጥና መለወጥ ይማራሉ፦ ምን ዘመናዊ መንፈሳዊ ቢባሉም!

ይህ የማይደፈርና የማይካድ ስብዕና የሚታነጽ የሚገነባ እንጂ በዘር በደም አይተላለፍም። ነገር ግን እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ጠባይ ያላቸው አባወራዎች በሚኖሩበት አካባቢ ማኅበረሰቡን የሚገነባው በእነርሱው ጠባይ የታነጸው የእነርሱው ቤተሰብ ነውና ለእርሱም ሊነገርበት ይችላል።

ስለኾነም የእነዚያ ጠንካራ ስብዕና ባለቤት አባወራዎች ጠባይ ከቤት-ከቤተሰባቸው አልፎ ለማኅበረሰቡ ተርፎ፤ የማኅበረሰብ ወግና ልማድ ይኾናል፤ ይታወቅበታልም!

እንዲሁም ደግሞ በጉራ የተቆለለ ነገር ግን ልል፣ ቀላጭ፣ ሸርታታ፣ የማይጨበጥ፣ ሙልጭልጭ፣ አስመሳይ፣ አድርባይ፣ ባንዳ ጠባይ ያላቸው አባወራዎች በሚኖሩበት ስብስብ፤ ትውልዳቸው ከሃዲ፣ አስመሳይ፣ ብሶተኛና ባንዳ ቢኾን ማኅበረሰቡም ቢወቀስ ከእነዚያው ከበዙት ጠባየ ልል ቀላጮች እንጂ ከተፈጥሮአቸው አይደለም።

ጠንካራ ስብዕና የሌለው አባወራ ለገንዘብ ክብሩን መሸጡ የጊዜ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም እንዳይሸጥ አድርጎ የሚያቆይለትን አቅጥር(አጥር ቅጥር) አልገነባም።

እርሱ ለዝና፣ ለሥልጣን፣ ለገንዘብ ለሌሎችም “ጥቅሞች” ሲል አቋሙን ይለውጣል! እንዲህ ያለ ሰው እየበዛ፣ ጠባዩንም በቤተሰቡ እያበዛ ሲመጣ የሀገር ታሪክ ውርደት ይኾናል።

አንድም የማይካድ የማይደፈር ጠንካራ ስብዕና የሌለው ትውልድ አባቶቹ የገነቡትን “አሮጌ ሥርዓት አይጠቅምም” እያለ ማፍረስ እንጂ ዐዲስ “እሴት” መገንባት አይቻለውም።

እርሱ በልል ጠባዩ የቆመበትን አፍርሷልና፤ የወለዳቸውም ሁሉ ሲመጡ እርሱን የሚያፈርሱት እነርሱም ከሰውነት ተርታ ፈርሰው የሚጠፉ ይኾናሉ።

አባወራነት በጉራ የሚገኝ የምስኪኖች በተለይም የአልጮች ጌጥ አይደለም! አባወራነት በተግባር የሚገለጥ፣ በፈተና የሚጠራ፣ በችግር የሚጎመራ፣ በጨለማም የሚጸናና በማንነቱ የማይደራደር ኩሩ ስብዕና ነው።

ቃሉና ተግባሩ የተጋጠመለት፣ ለክብሩ የሚሞትና ለዓላማው የሚኖር፣ በዚያም ጽዋውን የሚጨልጣት ሰው ብቻ ነው “የማይካድ ስብዕና ባለቤት” የሚባለው። እርሱ የወንድ ቁናው ነው! የአባወራነት ማማ ከፍታው ነው!

እንጂ ይህ ምን “አዋቂ መጣቂ” ቢባልም መልክና ልብሱን ያሳመረ ውሽልሽል-ሽልጥልጡ፣ አስመሳይ-አድርባዩ ሁሉ ስለ ወለደ አልያም ጫንቃው ስለደለበ ብቻ አባወራ ቢባል በእኛ ዐውድ ግን ብቁ አይደለም!

ወንድምዓለም! ዛሬ ካልጸናህ፣ ነገ የምታስረክበው ውድቀትን ብቻ ይሆናል! የእሴት፣ የባህል ውድቀት የታየባት ሀገራችን ትናንት በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ተሽለጥልጠው ባለፉት ነው፤ በአብዛኛው!

እነሆ! ትውልድን ከወደቀበት፣ ወንድነትን ከተጣለበት፣ አባወራነትንም ከተናቀበት የሚያነሳ ጽድቅንም የሚፈጽምበት ትውልድ ይነሳል!

Post a Comment

0 Comments