ልቡን አጥፍተውበት ነፍሱን ከጦርም ኾነ ከፍርድ አደባባይ ቢያድኑት ቢሟገቱለት እንኳ፤ "ሰውነቱን" ራሱ ከሰውነት ተራ እንዲያወጣት እርግጥ ነው፡፡
የትውልዱ ሰውነት የሚበየነው እስከዛሬ በመጣበት እሴት፣ ሥነ-ቃልና ትርጓሜያቸውም ነበር። ይህ “ልብ” ተብሎ የሚጠራው የውስጥ ሚዛን፣ ትውልዱ የትኛው ክፉ የትኛው ደግ መኾኑን የሚለይበት ነው።
ኾኖም ዛሬ ከተማሩት ጥቂቶቹ ይህንን የልብ (አስተዋይ) ሚዛን ኾን ብለው እየሰበሩት ሲኾን አብዛኞቹ ደግሞ እነዚህን ጥቂቶቹን በቸልተኝነት ትውልድ አጥፊ ሥራቸውን ዕያዩ እንኳ ያልፏቸዋል።
ማኅበረሰባችን ለዘመናት ልጆቹን ያነጸባቸውን እሴቶች ማንኳሰስ ትውልድ እንዳይኖረው ማምከን፣ ሀገርንም ያለተረካቢ ማስቀረት ነው።
ጀግንነት፣ አባወራነት፣ እናትነት፣ የቤት እመቤትነት፣ ታዛዥነት... የመሳሰሉት “ጊዜ ያለፈባቸው” ወይንም “ጎጂ፣ በዳይ፣ በዝባዥ” ተብለው ሲኮነኑ ጃንደርባነት፣ አመንዝራነት፣ ፈትነት፣ ደቂላ መጎተት፣ “የቢሮ ሠራተኝነት” እና የመሳሰሉት ደግሞ ለትውልዱ እንደ ጥሩ ግብዓት ይሰጡታል።
እንዲህ አድርገን ልቡን ያጠፋነውን ትውልድ፤ አንድም ልቡ በእንዲህ ባሉ ቀጣፊዎች ሲጠፋ ያልጠበቅነውን ትውልድ ከረሃብና ከሰይፍ ብንታደገው እንኳ የሚመራበት ሚዛን-ልቡ የተስተካከለለት አይደለምና ሰውነት ተፈጥሮውን ጠብቆ መቀጠል አይችልም።
ይህ ሚዛን-ልቡ የተሰበረ ትውልድ በብዙዎች መስዕዋትነት በተገኘ ሰላማዊ፣ የተንቆጠቆጠና የተሽቀረቀረ ከባቢ (ሀገር፣ ከተማ፣ መንደር) ውስጥ ቢኖር እንኳ ሚዛኑ ከተዛባው፥ ሰውነቱን ይበይንበት ከነበረው ነገር ግን ከጠፋው እሴቱ የተነሳ በገዛ እጁ “ሰውነቱን” ከሰውነት ተራ ያወጣዋል፡፡
አንድም በከፍተኛ የደምና የአጥንት መስዕዋትነት ከጠላት ተጠብቆ የነበረን ሕዝብ፥ ትውልድ፥ ሀገር እሴት-አልባው ትውልድ ያጠፋዋል፡፡ ትውልዱ መረን፥ ሀገሪቷም የመረኖች መፈንጪያ ትኾናለች፡፡
አስረጅ፡- እንግሊዝ(UK)
እንግሊዝ በሁለት አስርት ዓመታት ብቻ የሚራራቁ ሁለት የዓለም ጦርነቶችን ተካፍላለች፡፡ በእነዚያም ጦርነቶች በርካታ ወታደሮቿ(ከሚሊዮን እጅግ የሚልቁ) አልቀዋል፡፡
ኾኖም ግን ሀገሪቷን በጠላት ከመወረር፣ ድንበሯንም ከማስደፈር ታድገዋል(ጦርነቶቹ ተገቢ ነበሩ አልነበሩም የሚለው ጥያቄ ይቆይና)፡፡
ይኹን እንጂ ልክ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እንደተጠናቀቀ፤ በዚያው ዓመት ማለትም እ.ኤ.አ. በ1945፤ በተለይ በማርክሳውያን ተለውሶ፣ በጀረመን ሀገር ተጠንስሶ፣ ከእንግሊዛውያን ሊቃውንት ደርሶ የነበረውን ነባር እሴቶችን የማጥፋት ሥራ ጉዳቱ ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ይልቅ ለእንግሊዝና ለሕዝቦቿ እንደሚከፋባቸው ከአንድ ሰው በቀር ያስተዋለ፣ አስተውሎም የገሰጸ፣ የተዋቀሰም አልነበረም፡፡
የወቅቱን ሊቃውንት የወቀሰው ይህ ሰው ሥራቸውን እየጠቀሰ በጽኑ ተችቷቸዋል፡፡ ይህ የምነግራችሁ ለዚህ ገጽ የዘወትር አነባብያን በተለይ ዐዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኔም የእርሱ ጊዜ ክፉ ዕጣ ሀገሬ ቢወጣባት፣ ብንናገርም ሰሚ ብናጣ እደጋግመዋለሁ እንጂ፡፡
በወቅቱ “ነባር” የተባለውን ሥርዓት/ እሴት ሁሉ ኋላቀር እያሉ ሲተቹ የነበሩት ሊቃውንትን፤ አንድም ምሁራን የጥንት ሰዎችን ጥበብ እና ወግ “ኋላ ቀር” በማለት ያለ ምንም ምርመራ ውድቅ ማድረጋቸውን አጥብቆ ተችቷል። “አንድ ነገር አሮጌ ስለሆነ ብቻ ስህተት ነው ማለት አይደለም” ይልም ነበር።
አሁን እኛ ባለንበት ወቅትም አባወራዊው ቤተሰብ/ማኅበረሰብ “የወንድ/የሴት” ብሎ መበየኑ “ኋላቀር” በተለይም “ጨቋኝና አድሏዊ” ተብሎ መፈረጁን ያስተውሏል። ይህም ደግሞ በአስኳላ ሊቃውንቱ ብቻ ሳይኾን በቤተክህነቱም ጭምር እንጂ፡፡
የ1945ቱን የሲኤስ ሊውስ ማስጠንቀቂያ ያልሰሙ እንግሊዛውያን ዛሬ ቤተመንግሥቱን(የሕዝብ አስተዳደሩን) ቤተክህነቱንም ተራማጅ፣ ዘመናይ፣ መንፈሳዊ ነን ባሉ ነገር ግን ልባቸው በጠፋ የራሳቸው ልጆች አጡ፡፡ ቤተክርስትያናቱ የግብረሰዶማውያን መፈንጪያ ኾነው፣ ልጆቻቸውም በጃንደርብነትና በቀላጭነት ጠፍተዋል፡፡
ከሚሊዮን በላይ ኾነው ሀገራቸውን ከጥፋት ለመታደግ የዘመቱት በዚያም አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ለሀገራቸው የተሰዉ እንግሊዛውያን አርበኞች ይህንን ቢያዩ ምን ይሉ?
ዛሬ ሀገራቸው የደረሰችበትን በተለይም ሊታደጓት በሚገባቸው፣ በሚቻላቸው፣ በሚጠበቅባቸው ሊቃውንት መጥፋቷን ቢመለከቱስ?
እንግሊዛውያን ለመጥፋት ዛሬ ወራሪ አላስፈለጋቸውም። ትውልዳቸው ራሱ መውለድን ጠልቶ፣ የዘር ፍሬውን(የልብ ፍሬውን እውነትን የሚዘራበት ወኔውንም ቢሉ) በጥሶ(ጃንደርባ ኾኖ)፣ ማንም ከማንም መዳራትን ከ”ዘመናዊነትና ከመንፈሳዊነት” ቆጥሮ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት፣ በፈቃደኝነት፣ በእልልታና በጭብጨባ ታጅበው “ታሪክ” ኾነው እንደሚቀሩ ይጠበቃል።
አጉል “ተራማጅ፣ ዘመናዊ ቤተሰብ ነን” እያላችሁ፦
🚨 እኔ ልጆቼን እንደቀድሞዎቹ አላሳድግም
🚨 ሴቶች ልጆቼ ተምረው ማስትሬትና ዶክትሬት ሳይሠሩ አያገቡም
🚨 ሴቶች ልጆቼ ለባሎቻቸው ገረድ አይኾኑም
የምትሉ የማርክሳውያንን እርሾ ቀመሳችሁ በተሳሳተ ሚዛን ትውልዱን የምትሰፍሩ እናንተ ከእንግሊዝ ተማሩ።
እኔ ምሳሌ ብዬ እርሷን አመጣሁ እንጂ በጣልያንም፣ በፈረንሳይም፣ በስፔንም፣ በሰሜን አሜሪካም ብትሄዱ አንድ ዓይነት ዕጣ የወደቀባቸው ናቸው።
ሰውነት ይበየንበት ዘንድ፦ “መልአካዊው” አእምሮ “ከእንሰሳዊው” ሥጋዊ አካል ጋር ታርቆ “ሰው” የሚባለው ፍጥረት የሚታወቅበት፤ የተሰጠን ማዕከላዊ፣ ሚዛን አደላዳዩ ልብ ከትውልዱ ከጠፋ፣ እንዲጠፋም ከተደረገ፤
ሕይወቱን ከሞት መታደግ ከንቱ ነው! እሴት-አልባ (እውነት-አልባ) በተደረገው ሰውነቱ ከዚያ ለባሰ የቁም ሞት፣ ከእንሰሳት በታች ለኾነ ለወረደና ለተዋረደ ሕይወት መዳረግ ነው።
0 Comments