ከአባትነት የተገኘ ወንድነት፤ ከወንድነትም ለተገኘ አባትነት ወስደው ጽድቁን ይፈጽሙበታል እንጂ ማንንም አይለምኑበትም!
ወንድነት ከሰው የሚሰጥ “ፈቃድ” ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተቸረ “ሕልውና” ነው። ብዙዎች ወንድነትን እንደ ሰብአዊ መብት በየአደባባዩ ሲከራከሩለት ይታያሉ፤ እውነታው ግን ወንድነት የሚከራከሩለት አጀንዳ ሳይኾን የሚኖሩት ሕይወት ነው። ወንድ በተለይም አባወራ ወንድነት መክሊቱን ይኖረዋል እንጂ ስጡኝ አትስጡኝ ብሎ አይለማመጥም!
ጽድቅ የሚፈጸሙበትን ወንድነት ይዘው “እባካችሁ እወቁልኝ” አይሉም፤ እንደ ፀሐይ ይወጣሉ፣ እንደ ጨው ይጣፍጣሉ፣ እንደ ብርሃንም በጨለማ ውስጥ ያበሩበታል እንጂ።
ሚስቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ ሀገራቸውን፤ ሊጠብቁ፣ ሊመሩ፣ ያላቸውን ወንዶች ልጆቻችንን የምናሳድግበት መንገድ፤ በተለይ ልመናና ልምምጥን “ጀብድ፣ ቅድስናም” አድርገን ማሳደጉ፤ ቤተሰብ ላይ ልጆቻችን ላይ፣ በተለይም ጥበቃ በሚያስፈልጋቸው ሴቶቻችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው።
ይኸውም ዛሬ እንደምናየው ተፈጥሮአዊ፣ መልኮታዊ በኾነ ኃይል የተዋቀረው ቤተሰብ ላይ ከፍተኛ የኾነ ጥቃት እንዲደርስበት፣ በልጆቻችን በተለይም በሴቶቻችንም ላይ “ለመብታቸው በተሰፋ ካባ” የሚደርስባቸውን ከራሳቸው(ከተፈጥሮአቸው)፣ ከአባትና ከባላቸው፣ ከአምላካቸውም እንዲለዩ ለሚያደረገው ሸፍጥ ያጋልጣቸዋል።
ከአባወራው ወደ ልጁ የሚተላለፈውን የደም ርስት(ወንድ በኾነው ደሙ ውስጥ የሠለጠነው ወንድነት) በልምምጥ፣ በእሹሩሩ፣ በእንኮኮ፣ በታይታና በይኹንታ አይገለጥም፣ አይሠለጥንም፣ አይበለጽግም፣ አያይልምም።
እንዲህም ኾኖ ለመጣው የአባታችንና የአምላካችን ጽድቁ አይፈጸምበትም! ይልቁንስ ይህንን ተፈጥሮውን ተጠይፎ፣ ጠልቶና ጥሎ ምን ልሂቅና ሊቅ ለሚኾነው አስመሳይ፣ አድርባይ ባንዳም(ራሱን፣ ተፈጥሮውን ክዷልና ከሃዲ መኾኑ እርግጥ ነው) ይኾንበታል እንጂ!
በዚያም ወንድነት ጽድቅ የምንሠራበት የአምላካችን ስጦታ መኾኑ ይቀርና በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም ተጠይፈን፣ ጠልተንና አርቀን በቀበርነው ልክ የምንበድልበት “እርግማን” ይኾናል።
ማነህ አንተ ሰጪው ጽድቅ ትሠራበት ዘንድ ባወቀ ጽድቅ ትፈጽምበት መራራውን ዓለም ታጣፍጥበት፣ ፍትሕ ታሰፍንበት ዘንድ የሰጠህን “መልካም” የኾነ ስጦታውን በአጉል “አውቃለሁ፣ መንፈሳዊ ኾኛለሁ” እብሪት ታጅረህ፣ ኮንነኸውም፦
ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መኾንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ ..” የምትለው!
“መብቴን መልሱልኝ፣ ወንድ መኾን ፍቀዱልኝ፣ አባወራነቴን አጽድቁልኝ” የሚል ትውልድ የታሪክ፣ የትውፊት፣ የእሴትም ኪሳራ ውስጥ ያለ የሚጠፋም ለመኾኑ ምልክቱ ነው።
በሚስቱ(በሴቲቱ) ያለመወደዱ፣ ያለመሳም ያለመታቀፉ፣ ያለመፈቀድ ያለመተኛቱ አሳስቦት ትካዜ የሚገባው፣ አማካሪ የሚፈልገው፣ “ምከሩልኝ ለምኑልኝ” የሚለው፣ በዜማና በግጥም የሚያላዝነውን ትውልዴን ሳስብ ወንድነት ምን እንደኾነ ሳይገባው ቆሞ በመሽናትና ተኝቶ በማስረገዝ ብቻ ወንድነቱን ለሚበይነው እርሱ ኁልቁ መሳፍርት እንደሌለው እረዳለሁ!
ወንድ ኾኖ ለተፈጠረው በሰውነቱ የተሰጠው እርሱ እንደኾነ ሲያውቅ እርሱን ወስዶ አበልጽጎና አይሎበትም ጽድቅ ይፈጽመበታል እንጂ አባቱ የሰጠውን መክሊት በእርሱ ሊፈጽመው ላለውም ሚና ማንንም፣ ማንንም፣ ማ.ን.ን.ን.ም. አይለማመጥበትም!
“እባካችሁ ወንድነቴን እወቁልኝ፣
አባወራነቴን አጽድቁልኝ፣
ተረዱኝ፣ ውደዱኝ፣ እቀፉኝ፣ አክብሩኝ” ብሎ የሚለማመጥ ሰው፣ ገና ከጅምሩ የወንድነት ትርጉም ያልገባው “ንክርርርር ያለ” ምስኪን ነው።
ወንድነት ከተፈጥሮው የሚታወቅ ከታሪክ፣ ከትውፊትና ከአያት ቅድመ አያቶች ፈለግም የሚቀዳም የኃላፊነት መንፈስ፣ የመኾን እውነት እንጂ ከሰዎች “ይኹንታ” የሚገኝ መሳይ-አስመሳይነት አይደለም።
ትውልዳችን በተለይም ወንዶቻችን፦
👉ቀላጭነት እንደ ዘመናዊነት፣
👉አልጫነት እንደ መንፈሳዊነት
👉ምስኪንነት ደግሞ እንደ ጽድቅ ተቆለጳጵሰው በሚጋቱበት ዓለም ውስጥ ይገኛሉ።
የራሳቸው በሆነው ተፈጥሯዊ ጸጋ ላይ እንኳ “ይኹንታ” ፈላጊዎች እንዲሆኑ እየተገፉ ነው። በአስመሳይነት እንዲያድሩ፣ የሌሎችን ፈቃድና ይኹንታ ዘወትር እንዲሹ ይደረጋሉ።
ለምን?
ለባርነት የተመቹ ወዶገብ ባሮች እንዲኾኑ!
ይህ ግን ተፈጥሮአዊነት፣ ኢትዮጵያዊነትም ኾነ ክርስትና አይደለም፤ ዛሬ ሆዳደሮች ቢያስተምሩትም ኾኖ አያውቅም።
የአርበኞች ልጆች፦ ሚስቴን፣ ልጆቼን፣ ቤቴን፣ ማንነቴን፣ ሀገሬን፣ እምነቴን...፤ ለሚሉት የነፃነት እንጂ የልመና ልብ በተለይም የአስመሳይና የአድርባይም አልወረሱም የላቸውምም!
አባወራነት የቤት ባለቤትነት ብቻ አይደለም፤ የራስን መብትና ኃላፊነት አውቆ፣ በአምላክ የተሰጠውን ጸጋ ተረክቦ ለተለየለበት ሚና፣ ግዳጅ፣ ኃላፊነት መኖር ማለት ነው፤ ይህም ጽድቅ ነው!
ወንድ ልጅ ወንድነት መክሊቱን ጽድቁን ይፈጽምበታል እንጂ ለማንም በልምምጥ አያድርበትም፣ ማንንም አይለምንበትም።
ታናሼ! ወንድነትህን ለማስከበር አባወራነትህን ለማጽናት ሌሎችን አትጠብቅ፤ መብትህን ለማግኘት፣ ተፈጥሮህን ለመኖር፣ በልዕልናህም ለመስፈፍ ማንንም አትማጸን።
ይህ ከተፈጥሮአዊ ባሕሪህ ጋር ይቃረናልና። ይልቁንም እንደ አባቶችህ ጽና፤ በጽናት ቁም! የተሰጠህን መክሊት በወኔና በቅንነት ለጽድቁ ተጠቀምበት እንጂ።
የወንድነት ቁና፣ የአባወራነት ልዕልና መፈክር መርሑ ግልጽ ነው፦ ልመና የለበትም፣ መለማመጥን አያውቅም፣ አስመሳይነትን አይይዝም፣ አድርባይነትን አይጎትትም፣ በባንዳነት አየገኝም፤ የምትናገረውን፣ የፈለግከውን በጽድቁ ሚና ኾነህ መገኘት እንጂ!
የትውልድ ሕልውና የሚቀጥለው፣ ታሪክና እሴቱ፣ ባህልና እምነቱ ማንነቱን እየበየነ የሚቀባበለው ይህንን ተፈጥሮአዊ የኾነ ከአባቱ የገኘ መብቱን በሚያውቅና ኃላፊነቱን በሚወጣ፣ የአባቶቹን አርበኝነት በደሙ በሚያዘምን ወንድ ብቻ ነው።
ተፈጥሮህን አውቀህ፣ ጸጋህን ተረድተህ፣ መክሊትህን ተቀብለህ፦ በወንድነትህ ጽድቅን ፈጽም!
ከማንም የማይለመን፣ የማይጠየቅ፣ የማይፈቀድ፣ የማይወደስ ግን የሚኖር ያውም ለጽድቅ የኾነ ታላቅ ክብር አለህ - እሱም ወንድነትህ ነው!
በቃልህ፣ በአቋምህ፣ በኪዳንህ ጸንተህ ተገኝ! አባወራ፦ ወንድነት መክሊቱን አውቆ፣ ሠልጥኖና በልጽጎ አይሎበትም ጽድቅ ይሠራበት ዘንድ በደም በወረሰው ርስቱ፤ የማንንም ይኹንታና ፈቃድ አይፈልግም!
ለእርሱ በዚህ ከመገለጥ ከመኖርም ውጪ ሕይወት የለም፤ አይኾንምና!
0 Comments