ከአባቷ በላይ አዋቂ ነጣቂ




✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል 

"ከአባቷ በላይ አውቅላታለሁ" እያሉ ትውልድን ማጥፋት፤ ዐዲስ ሸፍጥ አይደለም። ይልቁንስ ሰው ትኩረት የነፈገው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ የመጣ የጠላት ሥራ እንጂ!

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቤተሰብ ጥንታዊ፣ ተፈጥሮአዊ እና መለኮታዊ መሠረት ያለው ተቋም ነው። ይህ ተቋም ደግሞ እንደማንኛውም ተቋማት አንድ መሪ-ራስ አለው፤ እርሱም አባወራው ነው። ኾኖም ዛሬ ይህ ለሀገር መገንቢያ ጡቡ የኾነው ቤተሰብና የቤተሰቡም ምሰሶ የኾነው አባወራ በታቀደና በታለመ “የአካዳሚክ”-በሊቃውንቱ እና “የፖሊሲ”-በልሂቃኑ ጥቃት ስር ወድቀዋል።

ይህ ጥቃት በሴቶች መብት፣ በሥርዓተ-ጾታ እኩልነት እና በአየር ንብረት ጥበቃ ስም ቢመጣም፣ ውስጡ ግን “ሰውነትን የማጥፋት” ጥልቅ ሴራ ያዘለ ነው።

ይህ ትውልድ ውስጥ የሚሰራጭ የማይድን፣ የሚራባ፣ የሚባዛ፣ የሚያጠፋም ነቀርሳን አዘል ተውሳክ ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚሰራጨው በመሃይማን ሳይኾን “ከኛ ወዲያ አዋቂ-ጠማቂ የለም” ሲሉ በእብሪት በታጀሩ ልሂቃን ሊቃውንትም ጭምር ነው።

የማርክሳውያን አስተሳሰብ “ያለ አብዮት ኮሚዩኒዝምን እውን ማድረግ አይቻልም” ሲል ነባር መንግሥታትን የሚገለብጥ የብሶት አብዮት እንዲጠመቅ ያበረታታል።

ኾኖም አንቶኒዮ ግራምሺ ማኅበረሰቡን እንደ ዐለት አጽንተው፣ እንደ ዋልታና ማገር ደግፈው፣ እንደ ባጥና ቆጥ አስጊጠው፣ እንደ አጥርና ቅጥር አጥረው የያዙት እምነት፣ ትውፊት እና የቤተሰብ እሴቶች እስካልተናዱ ድረስ አብዮቱ እንደማይሳካ ተንትኖ አስረድቷል።

ለዚህም የቆዩ፣ ትውልድ የተበየነባቸውን ባህሎች፣ እምነቶች፣ ወጎች “የበላይነትን” ለመስበር ነባር እሴቶችን ቀስ በቀስ የመሸርሸር ስትራቴጂ አስተማረ።

እነ ሶፊ ሊውስ “Abolition of the Family” (ቤተሰብን ማጥፋት) ስትል፣ የምታራምደው ይህንኑ የቆየ የማርክሳዊ ሸፍጥ ነው።

ቤተሰብን “የጭቆና መገኛ” አድርጎ በመሳል ከእርሱም ደግሞ በተለይ ወንዱን ይበልጡንም መሪውን፣ ጠባቂውን፣ እረኛውን፣ ገንቢውን፣ ባለቤቱን፦ አባወራውን በዝባዥ፣ ጨቋኝና በዳይ አድርጎ ዘወትር በመተረክ፤

የሰውን ልጅ ከተፈጥሮአዊው ፍቅርና ጥበቃ ነጥሎ፣ ሰውነቱን ከሚያገኝበት እሴት ነጥሎ “የመንግሥትና የኮርፖሬሽኖች ጥገኛ” የማድረግ ግብ አላቸው።

ለትውልዱ ወላጅ አባቱ ይበልጡንም የሰማይ አባቱ አባት እንዲኾንለት አይፈለግም። እያንዳንዱ ቤተሰብ በፍቅር እጦት፣ በዝሙት፣ በአመንዝራነት፣ በዲቃላ መጎተት ፈርሶ ማንም የማንም ሳይኾን ከማንም የትም ተጠንጠላጥሎ ሲቀር አባቱም፣ አምላኩም መንግሥት እንዲኾን እንጂ!

እነዚህ የነግራምሺ፣ ሲልቪያ ፍሬድሪቺ እና የሶፊ ሊውስ አጥፊ ሐሳቦች ዛሬ በ UN Women በኩል በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ተመድቦላቸው ሀገራት ወደ በፖሊሲ እንዲያጸድቋቸው እየተደረጉ ነው።

The Care Economy: “እናቶች በቤት ውስጥ የሚሠሩት ሥራ ክፍያ የለውም” በሚል ሰበብ፣ እናትነትን ወደ ንግድና ወደ ደመወዝተኛነት ብሎም በግብር ከፋይነት ለኢኮኖሚው አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ እየተባለ አባታቸው እነርሱን ከፈጠረበት እርሱን ከሚመስሉበት የመጋቢነትና የተንከባካቢነት ጸጋው እንዲለዩና እንዲጠሉት ይደረጋሉ።

በ2030ው ግብ ዓለም አቀፍ ተቋማት በርብርብ፣ ሴቶችን ከቤት በማስወጣት እና ሕፃናትን ገና በለጋነታቸው ከወላጆቻቸው በመንጠቅ “በመንግሥት ማቆያዎች” ውስጥ በማሳደግ ማንነቱን ያጣ፣ ትውፊትና ምግባር የተለየው ትውልድ የማሳደጊያ ስልት ነው።

የአሉላ ፓንክረስትና ያንግ ላይቭስ “Yong Lives” ሚናም በኢትዮጵያ ምድር ይህ ሸፍጥ እንዲፈጸም መንግሥትን በእርዳታዎች አጓግቶ ነገር ግን በእነዚህ ተቋማት “ጥናትን መረጃን መሠረት ባደረገ (evidence based” የፖሊሲ “ምክረ ሃሳብ” ጠፍሮ ለመያዝ ነው።

የብሪታንያ ከፍተኛ ባለሥልጣን፦ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊዋ ኢቬት ኩፐር ሰሞኑን እዚህ በቆዩበት ወቅት ከአሉላ ፓንክረስት ጋር መምከራቸው፣ የኢትዮጵያን ቤተሰብ ውስጣዊ መዋቅር በመሰለል ለማፍረስ የሚረዳ ግብዓት ለማግኘት፣ በዚያም መንግሥትን ወጥሮ ለመያዝ ነው።

እንዲህ ያሉ በትውልዱ መካከል ብሶት ጠማቂ፣ ልዩነት አርቃቂ፣ ወኔ-ጉልበቱን አድቃቂ ማርክሳዊ ተቋማት “እውቀታቸውን” ለጥፋት የሚያውሉት “ማስረጃን መሠረት ያደረገ ወይም በማስረጃ የተደገፈ high-standard research methodology” የሚሉት “ጥናታቸውን” በመጠቀም ነው።

እዚህ ጋር ሮሚና ኢስትራቲን ያስታውሷል!

ተቋማት “ጥናት አደረግን” ይላሉ፤ ነገር ግን ጥናታቸው የሚፈልጉትን ውጤት እንዲሰጣቸው፤ አንድም ገንዘብ የሚሰጧቸውን “የረጂዎቹን” ፍላጎት እንዲያመጣላቸው ከሚገኝበት ዐወዱ፦ እሴቱ፣ እምነቱ አውጥተው ይዘውሩታል።

ስለኾነም ለብዙ ዘመናት ማኅበረሰቡን ድርና ማግ ኾኖ የሠራው እሴት ተዘንጅቶ አባትን “አምባገነን”፣ አባወራነትን “የአየር ንብረት ጠላት” አድርጎ በመፈረጅ ልጆች ለጊዜው ለወላጅ አባታቸው፣ ለኋላውና በዘላቂነት ግን ለሰማዩ አባታቸው ያላቸውን ክብር እንዲያጡ ይደረጋል።

በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉት ከሺህ በላይ የሕፃናት ማቆያዎች የዚሁ “መወዝ የማይከፈልበት የቤት ውስጥ ሥራና እንክብካቤን” በክፍያ አሠርቶ ለሀገሪቷ GDP አስተዋጽዖ የሚያደርግበትን የ”Care Economy” ፖሊሲ አካል ናቸው።

የእነ አሉላ ፓንክረስትም ጥናትም እንዲህ ይላል፦ ሴቶች ወጣቶች በአብዛኛው በማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች ሲጠመዱ፤ ወንዶች በክፍያ መሥራታቸው በጥናቱ ከታዩ የጾታ እኩልነት ልዮነቶች ተጠቃሽ ነው፤ ይላል።

https://ethiopianreporter.com/151254/

ልብ አድርጉ! Young lives የተሰኘው የአሉላ ፓንክረስት “የጥናት ተቋም” እኔ “ለሀገሩ” እንግሊዝ የሚያገለግል የስለላ ተቋም ብዬ የማስቀምጠው ከ12,000 በላይ ሕጻናትን ከልጅነት ጀምሮ(ከሀያ አምስት ዓመት በላይ) ሲከታተል ቆይቷል።

የሚያገኘውንም መረጃ “በሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” ሰበብ ቤተሰብን ማጥቂያ እንዲኾን የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ሲያቀርብ ለሀገሩ(እንግሊዝ) ግልባጭ ልኮ ነው።

በዚያም እንግሊዝ የምታደርገውን ማንኛውንም ድጋፍ “በማስረጃ በተደገፈው ጥናት” እየተጫኑ የራሳቸውን ትውልድ እንዳጠፉት፣ ማኅበረሰባቸውን እንዳመከኑትና ሀገራቸውን እንዳፈረሱት ይኾን ዘንድ ግድ ይሉበታል።

“ሀገር ወዳዱ” አሉላ ፓንክረስት!

“ይህንን እናንሳ፣ ትውልዱን በተለይም ወጣቱን እንታደግ” ስላቸው “ኦ ኦ ይህ ሀሳብ መሞገት አለበት፣ ትውልዱ ያንተን ብቻ ሳይኾን የሌላውንም መስማት አለበት” ይሏችኋል።

ትውልዱን “የበላውን ያሳከከውን” አጀንዳ ወስደው በዘፈቀደ እንዳላቀረቡ፣ ልክ (as if) ሀሳቦችን አሟግተው ግራና ቀኙን አደላድለው የሚሰጡት “ሚዛናዊ” ይመስል። አልጫነታቸውን የሚገልጥ ጠጣርና ጽኑ እውነት ጋር ሲቀርቡ “ሀሳብህ መሞገት አለበት”።

እውነትን ላለመናገር ጠርንፎ ያጠፋህን አልጫነት ተመልከት!

እነርሱ ሰሞኑን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡበትን፣ ሚኒስትሮችና በርካታ “ባለድርሻ” አካላት በተገኙበት ያቀረቡትን ነገ “ፖሊሲ” እንዲኾን የሚጠበቀውን ባለ አስር ገጽ “ምክረሃሳብ” ሳነብ ከቀረበበትን መንገድ ሁለት ነገሮችን አስተዋልኩ።




ልብ አደረርግ! የፖሊሲ “ምክረ ሃሳቡን” ገና አንስቼ አልሞገትኩም። ግን ጽሑፉ በቀረበበት ጥቂት እርሷም አስር ገጽ ውስጥ ማርክሳዊውን ተውሳክ የሚያስነሱትን ቃላት(አገላለጽ) እንጂ።

፩ኛ Household

በአስሩ ገጾችው ውስጥ households የሚለው ቃል ከሃያ አምስት ጊዜ በላይ ተገለጿል። ለምን? ምንን ወክሎ? በማኅበረሰብ(ቤተሰብ) ጥናት ውስጥ ይህንን ቃል መቼ በይበልጥ መጠቀም ተጀረ? እነማንስ ያስገድዱታል?

Households የሚለውን ቃል በየትኛውም በተለይ ደግሞ በማኅበረሰብ ጥናት(sociology)፣ ይበልጡንም ደግሞ “በጾታ እኩልነት አጥኚዎች እና ተሟጋቾች” አካባቢ ስታገኙት ኾን ተብሎ የሚገባ ነቀርሳን የሚያስከትል ተውሳክ እንደ ኾነ አውቃችሁ ተጠንቀቁ!

Households በማኅበራዊ ጥናት፣ ንግግር እና ፖሊሲ(ሕግ) አወጣጥ ሂደት ውስጥ Family የሚለውን ነባር እሴት እንዲተካ፣ እንዲያስረሳና ከትውልዱ ልቡና እንዲያጠፋ የተመረጠ የማርክሳውያን ምልምል ቃል ነው።

ለምን? ቢሉ ማርክሳውያን እስከዛሬ እንደ ጻፍኩላችሁ ያ አባት የሚመራውን፣ የአባታችንም የኾነውን፦ አባት፣ እናት፣ ልጆችና ሌሎችም ወዳጅ ዘመዶች ያሉበትን (nuclear family) እንዲፈርስ ይፈልጋሉና።

ግራምሺ የኮሚኒስት ዓለምን በመፍጠሩ ረገድ መንግሥትን ከሚገለብጠው የጦር አብዮት ይልቅ “ውጤታማ” የሚለው፦ትውልዱን የገነቡ ጠንካራ እሴቶችን እንደ ቤተሰብ ወይንም በእንግልጣሩ The Nuclear Family ያሉት ሲጠፉ ነው።

ስለኾነም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በጠንካራ ትውፊት፣ ሃይማኖትና እሴት የተገነቡ ማኅበረሰቦችን ያጠፉበት ዘንድ ያመጧቸውን ልምምዶች ይሰይሙበታል፦ Housholdም ይሉታል።

Households ለተመረጠበት አስረጅ 1

ሴቷን በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ሰበብ ከአባቷና ከባሏ ለይተዋት ልጆቹንም ቀምታ፣ ያለ አባት ፈት ኾኖ ማሳደግን ጀብድ አድርገውላት የምትኖርበትን ነገር ግን በማኅበረሰቡ ባህልና ሃይማኖት የተወገዘውን “ግንጥል ጌጥ-ቤተሰብ” Household ሲሉ ይጠሩታል።

ማስታወሻ፦ ፈትነቱ ይምጣ እንጂ ይህንን ፈትነት ለማበረታታት፣ ለማለማመድም የአሉላ ፓንክረስቱ ያንግ ላይቭስ ይሠራል። ይህንንም በሌላ አካባቢ ያለውን ተሞክሮ በሕንድ አንድራ ፓርደሽና ተላንጋና ስር የሰደደ ፍቺ ማስተዋል ይቻላል፤ ድረ ገጹም ላይ በግልጽ አስቀምጦታል።

ስለኾነም በቲቪም ኾነ በማንኛውም መገናኛ የሚቀርቡ “ልጆቿን ብቻዋን ያለ አባት ያሳደገች ጠንካራ ንቁና ብቁ ሴት” እያሉ “አርአያ” ሲያቀርቡልህ ከኋላ ያለውን ለትውልዱ ሊያለማምዱት የፈለጉት “ፈትነት” እንዳለ ተረዳ።

Households ለተመረጠበት አስረጅ 2

2.1. አንድም ደግሞ በSRHR(sexual reproductive health and right) አማካኝነት (ስለ እርሱ በቀጣይ እጽፍላችኋለሁ) ግብረ ሰዶማዊ ኾነው ልጆችን በጉዲፈቻ አሳድገው ለሚኖሩት፣

2.2. እንዲሁም ደግሞ አሁን አሁን በከተማ እየተለመደ የመጣውን ሴቶች ከወላጆቻቸው ተለይተው ሦስት አራት ኾነው፣ ነገር ግን የትም ከማንም ተንጠላጥለው እየመጡ የሚኖሩበትን፣

2.3. ማናቸውም የማንም ሳይኾኑ ሁሉም የሁሉም ኾነው የሚኖሩበትን “ዘላንነት”፦ በምዕራባውያን የተለመደ እኛም ጋር እንዲመጣ የሚፈለገውን በልቅ ወሲብ የሚገለጠውን፣

እነዚህና የመሳሰሉት በተለመደው፣ በነበረው፣ በተቀደሰው “ቤተሰብ” ሊወከሉ አይችሉምና፤ ነገር ግን እንዲያ መኖር “ዘመናዊነት” ይባላልና ስብስቡን Household ይሉታል።

አንድም ያንን የመሰለውን ስብስብ ከማምጣት በፊት ስሙን ለትውልዱ ያለማምዱታል።

፪ኛ Entrenched Patriarchal Norms

ይህ ደግሞ እነርሱ ሊያመጡ ለሚፈልጉት መረን ትውልድ፣ ታሪክ አልባ ማኅበረሰብ፣ ድንበር አልባ “ሀገር” እንቅፋት የኾነባቸው “አባወራዊው ሥርዓት” ነውና እንዲፈርስ ይሠራሉና እንዲህ እያሉ ይጠሩታል።

“ወግ አጥባቂ፣ የማይቀየር፣ የማይለወጥ፣ የማይሻሻል፣ ግትርና አካባጅ፣ በዝባዥና ጨቋኝ... የአባወራው ልማዶች” እያለ አስራ አንድ ጊዜ በአስሩ ገጾች ውስጥ ጽሑፉ ይኮንነዋል።

አንድ “የኢትዮጵያውያንን ባህል፣ ሃይማኖትና ወጎች አውቃለሁ፣ አጠናለሁ እኔም በእነርሱ እገለጣለሁ እጠራለሁም” የሚል ሰው ለዘመናት ትውልዱን በጠንካራ ቤተሰብ፣ በጽኑ ማኅበረሰብ የገነቡ እሴቶችን እንዲህ ሲኮንን፤ ለረጅም ዓመታትም አጠናኋቸው ሰበሰብኳቸው ያላቸውንም መረጃዎች ለሌላ ሀገር በዚህ መልክ አሳልፎ ሲሰጥ ይህ ባንዳነት (treason) ነው።

የእነ አሉላ ፓንክረስቱ ያንግ ላይቭስ ለሴቷ ከአባቷ/ባሏ በላይ “አዋቂ ነኝ” ሲል “በበግ ለምድ” የተገለጠ ትውልድን በተለይም ሴቶቻችንን በፖሊሲ በኩል አድርጎ ሊያጠፋቸው የመጣ “ነጣቂ ተኩላ” ነው።

በቀጣይ የተወሰኑ ፖሊሲዎችንንና ማብራሪያቸውን እያነሳን በዚያ መንገድ ሄደው የጠፉትን ሀገራት እያወሳን፣ ለእኛም የተዘጋጀልንን “የጥፋት” ፖሊሲ ምክረሃሳብ እንታዘባለን።


Post a Comment

0 Comments