ጽድቅን አስተዋይ ልብ እንጂ አዋቂ አእምሮ አይፈጽመውም!


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ስለ ጽድቅ ምን ቢያሰላስሉ፣ ቢጽፉና ቢራቀቁ፣ ፍጻሜውን ለማምጣት ጭካኔ፣ ድፍረትና እምነት በሌለበት "ተረት ተረት የላም በረት" ይኾናል!

ዓለማችን በእውቀት “ቋቶች” እንጂ በጽድቅ “አንበሶች” አልተሞላችም። መጻሕፍትን በልተው ያገሱ፣ የታሪክ ድርሳናትን አኝከው የሚተፉ፣ በማዕረግ ብዛት የጎበጡ፣ ነገር ግን አንዲት ጠብታ እውነትን በተግባር ለመግለጥ፣ ስለፍትሕ ለመቆም “ወኔ” የራቃቸው ስልብ (ልብ-አልባ) ሊቃውንት አደባባዩን ሞልተውታል እንጂ።

የጀግኖችን ታሪክ ይተርኩልናል—ነገር ግን ራሳቸው ካልጫ ጠባያቸው በአስመሳይነት ያደሩ ናቸው። የቅዱሳንን ገድል ይሰብኩልናል—ነገር ግን ራሳቸው ለጥቅምና ለዝና የተንበረከኩ ሆዳደሮች ናቸው።

እነዚህ ሊቃውንት የጀግኖችን ታሪክና የቅዱሳንን ገድልን ልክ እንደ ሸቀጥ ይነግዱበታል። በንግግራቸው መድረክ ያደምቁበታል፣ በጭብጨባ ይሰቅሉታል፣ በእልልታም ያሳርጉታል፣ በጽሑፋቸው ሰማይ ያደርሱታል።

ነገር ግን ያንን ታሪክ በተግባር ስንፈልግባቸው “ምንም ማድረግ አንችልም፣ እርሱ ያመጣውን እርሱ ይመልሰው እንጂ” በሚል የአልጫ ሰበብ ይሸሸጋሉ።

ጽድቅ በመጻሕፍት መካከል የምትኖር “ጥቅስ” አይደለችም፤ ነገር ግን በመከራ እቶን ውስጥ የምትፈተን የምትኖር “ሕይወት” እንጂ!

ማወቅ ብቻውን ሰውነትን አይበይንም፤ ያወቁትን ለመኖር መጨከን ግን ወንድነትን ያጸናል፤ ወደ አባወራነቱም ማማ ይሰቅላል! በተለይም አንድ ትውልድ አባቶቹ ከመጡበት፣ ማንነቱን ከተቀበለበት፣ ሰውነቱን ከበየነለት እሴቱ የተለየ፤ አንድም የሚለይ “ትምህርት” ከተማረ ልቡ የጠፋ፣ ልባልባ መኾኑ አይቀርም!

እርሱም ተምሮ ምን ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት፣ አሰላሳይ ቢባል ጽድቅን፦ መልካሙን፣ ልኩን፣ ተገቢዉን፣ ውቡን፤ መፈጸም የተሳነው አልጫ ይኾናል!

ስለ ነፃነት እየሰበኩ ባርነትን የሚልሱ፣ ስለ እውነት እያወሩ በሐሰት የሚዳሩ፣ ስለ ጥንካሬ እያስተማሩ በትንሽ ፈተና የሚቀልጡ፣ ስለ እውነት እያስተማሩ ባስመሳይነት(ባድርባይነት) የሚያድሩ “ሊቃውንት” የሚፈጥሩት ትውልድ ቢኖር እንደ ራሳቸው መረጃ የታጨቀበት ነገር ግን “ልብ-አልባ” የኾነ ባርነቱን የወደደ አልጫ ትውልድ ነው!

ይህ ደግሞ ጽድቅ ፍጻሜ የማያገኝበት ቅዠት፦ “ተረት ተረት የላም በረት” ነው። ምን ለጽድቅ እኖራለሁ፣ ጽድቅ እፈጽማለሁ ቢል ተረት እንደማውራት የቀለለ እንደተረትነቱም እውነትነቱ የቀረ ከንቱ ነው።

በአእምሮ ሰሌዳ፣ በናላ ግድግዳ የተሳለ እውቀት ልብን ካላጨከነ፣ ጭንቅላትን ካላበለጸገ፣ ሰውነት ላይ ካላሠለጠነ ጽድቅን ለመፈጸም አያበቃምና ፋይዳ የለውም!

አባወራነት ጽድቅን መተረክ ሳይኾን፣ “ፈጽሞ” ለሌሎች አብነት፣ አርአያ፣ ምሳሌ መኾን ነው። ጽድቅን ለመፈጸም ደግሞ ድፍረት፣ ጭካኔና እምነት ብቃትም (ሃይማኖት አላልኩም) ይጠይቃል።

ታናሼ! የታሪክ ማኅደር ብቻ አትሁን፤ የታሪክን ሠሪ ኹን እንጂ። የታሪክ ድርሳናትን፣ የቅዱሳንን ገድል ማንበብህ የሚጠቅመው ያንን ቅድስናና ጀግንነት በቤትህ፣ በትዳርህና በማኅበረሰብህ ውስጥ ጽድቁን ለመፈጸም “እንድትጨክንበት” እንጂ ነው።

ከመስማትና ከማንበብ የተነሳ ንባባት በአእምሮህ ሰሌዳ ላይ ብቻ ተስለው ከቀሩ፣ ወደ ልብህ ዘቅጠው ሚዛን ካላደላደሉ፣ ከሰውነትህ ብልቶች ተሰራጭተው በእነርሱ ላይ ካላሠለጠኑህ፤

የበድኖቹ መጻሕፍት ግልባጭ (copy) እንጂ ጽድቁን መፈጸም፣ ለመፈጸምም መጨከን፣ ለመጨከንም እምነት ያለው “አባወራ” አትኾንም!

ጽድቅ የሚፈጸመው በወረቀት ላይ ሳይኾን፣ ለእርሱ በጨከነ ወንዳዊ፣ አባወራዊ ጀግና ልበሙሉም ልብ እንጂ ነው! በተግባር እየኖርክ ካልተለማመድከው የእውቀትህ ብዛት የፍርሃት፣ የስጋትህ ምንጭ፣ ልክ ይኾንብሃል!

ጽድቅን ብዙ “የተማሩ፣ የተመራመሩ፣ ያሰላሰሉ” በዚያም በርካታ ማዕረጋትን ለትከሻቸውም ኾነ ለጠሪያቸው እስኪከብድ የደረቡቱ ይፈጽሙታል ብለህ ተስፋ አታድርግ!

ከዚያ ይልቅ ግን “ተማሩም አልተማሩም” ጽድቁን ያወቁ፣ የናፈቁ፣ የበቁ፣ የጨከኑ፣ ዋጋውን የሚከፍሉ ጥቂቶች ይፈጽሟታል እንጂ!

እነዚያ ጥቂቶች ከትውልዱ እስኪገኙ ደረስ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ተንኮል፣ አስመሳይነት፣ ባንዳነት ከመሃይምናኑ ይልቅ “በሊቃውንቱ” ልብ በቅሎ ባፋቸውም ተዘርቶ ትውልድን እያጠፋ ይቆያል!


Post a Comment

0 Comments