✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
የእውቀት፣ የገንዘብ፣ የዝና ብዛቱ ሳይኾን ጽድቅን የናፈቀ የራስ ላይ ሥልጣኔ ትውልድን ከባርነት ነፃ ማውጣት የሚችልን ጀግና ያፈራል!
ዛሬ ዓለማችን በ”ምቾት” እና በ”ድሎት” ሰክራለች። መከራን እንደ እርግማን፣ ፈተናን ደግሞ እንደ ውድቀት የሚያይ ትውልድ አፍርታለች።
ነገር ግን በአባወራ ሚዛን፦ መከራ ጀግና የሚቀጥቅጥበት መዶሻ፣ ነጥሮ የሚወጣበትም እሳት ነው! መከራ ለሌለው ወንድ ጽድቅ አይርበውም፤ ጽድቅ ያልራበው ወንድ ደግሞ ለፍትሕ የሚከፈልን መስዋዕትነት አያውቀውም!
እውቀትማ ዛሬ በየመንገዱ ሞልቷል፤ መረጃ በየኪሳችን ተገኝቷል። ነገር ግን ያወቁትን ለመኖር “ጭካኔ” የሌላቸው፣ የተረዱትን ለመፈጸም “ወኔ” የራቃቸው ስልብ-ሊቃውንት ትውልዱን አልጨውታል እንጂ።
ጀግና የሚወለደው ከዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ሳይሆን፣ ከመከራ ዳገት ላይ ነው። ራስን ማሸነፍ፣ በስሜትና ብልቶቹ ላይ መሠልጠን ያልቻለ ሰው፣ ገንዘብና ዝና ቢከመርለትም ባርነቱ የከፋ ነው።
እውነተኛ ጀግና ማለት ከውጭ የሚመጣውን ወረራ በዚያም ለሚነሳ እሳት “ጭዳ” ከመኾኑ በፊት በውስጡ ያለውን “አልጫነት” የገደለ ነው።
ወንድነት ዝም ብሎ “በዘፈቀደ” የተሰጠ “ጾታ” ሳይኾን፣ ጽድቅ የሚፈጸምበትና ፍትሕ የሚሰፍንበት ታላቅ መክሊት ነው። ይህ መክሊት ግን የሚሠራው በፈተና ሲታነጽ ብቻ ነው።
መከራ ወንድን ልጅ “ለምን?” ብሎ እንዲጠይቅ፣ ተፈጥሮውን እንዲመረምርና ለቤተሰቡና ለማኅበረሰቡ የሚሆን “ቤዛ” እንዲሆን ያስገድደዋል። መከራን የሸሸ ወንድ፣ ጽድቅን የከዳ ባንዳ ነው።
☀️ ልጆቻችሁን ከመከራ ስታሸሿቸው አልጫ ይኾኑ ዘንድ እየፈረዳችሁባቸው ነው!
ዛሬ ትውልዱ በረቀቀ መንገድ ለባርነት እየተመቻቸ ነው። ይህንን ባርነት ሰብሮ መውጣት የሚቻለው ደግሞ በምቾት በለዘበ፣ በቃላት በተዋበ፣ ለስላሴ አንደበት ሳይሆን፣ በመከራ በነጠረ ጽኑ አቋምና ስብዕና ነው።
አባወራነት ማለት መከራን መጋፈጥ፣ ፋና ለጠፋው ትውልድ በጨለማ ውስጥ ብርሃን መኾንና ለትውልድ የሚኾን “የሥልጣኔ ዳና” መተው ነው።
አባወራ ጀግና ነው! ጀግንነቱም መከራን እየሸወደ “ዕድሜ ጠግቦ” መሞት አይደለም! ይልቁንስ በመከራው ውስጥ አልፎ ዐለም የተጠማችውን፣ የምትጣፍጥበትንም ጽድቅ ፍትሕንም መስጠት ነው።
ታናሼ! ምቾት ካሳሳተህ፣ ዝና ካታለለህና እውቀት ካሳበጠህ ለባርነት የተመቸህ “አልጫ” ነህ። መከራ ሲመጣ አትሽሽ፤ ይልቁንስ ጽድቅን አስርቦ ጀግናው አንተን እንዲወልድልህ በወንድነትህ ቁም!
ዛሬ ባንተ ላይ የሚፈሰው መከራ፣ ነገ ለትውልድህ የሚተርፍ የነፃነት ቅርስ ይኾናልና። አትፍራ አትደንግጥም! ከአቅምምሀ በላይ የሚመስሉህ መከራዎች በራስህ ላይ በሠለጠንክበት ልክ አጅግ ይቀሉሃል፤ እንደ ተጣራ ቀዝቃዛ ጠላም ትጨልጣቸዋለህ!
ይህ የእኔም ኾነ የወንድሞቼ ልምድ ነው! እርሱም የአባወራው መንገድ ፈለግም ነው! ለእውነት ጨክነው፣ ለጽድቅ ለቆረጡት፦ መከራ የጀግኖች “ማኅፀን” ነው!
እነዚያ ጀግኖች ጽድቅን ተጠምተው በመከራው መካከል ሲገማሸሩ ደግሞ ለባርነት ጥፋትና መርዶው ነው!
ይህ የጠፋው አባወራነት ትንሳዔ ነው!💪
ሀገራችን፣ ትውልዳችን በልሂቃኑና በሊቃውንቱ ክህደት ተፈጽሞበት ለአልጫነት ተላልፎ፣ ለባርነት ተሽጦ፣ ወዶ ገብ ባርያ እንዲኾን በካይ መጤ ትርክቶችን በሚጋትበት በዚህ ወቅት እንዳንተ ዓይነት ጽድቅን የተራቡ አባወራዎች ያስፈልጉታል!💪
ሀገርህ፣ ትውልድህ፣ ልጆችህ ሲፈልጉህ አንተ ከወዴት አለህ?!
0 Comments