ብሶተኝነት ከአባወራነት ይለይሃል


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ልትገፋ፣ ልትጎዳ፣ ልትቸገር፣ ልትበደልም ትችላለህ ነገር ግን እድሜ ዘላለምህን እርሱኑ እያነሳህና እየጣልክ ተቀባይነትን ስትሻበት ከተፈጥሮህ ከፈጣሪህም ያርቅሃል!

የሙት ልጅ ነኝ፣ አናሳ ብሄር ነኝ፣ ደሃ ነኝ፣ አጭር ነኝ፣ ቀጭን ነኝ፣ ወፍራም ነኝ፣ ነጭ ነኝ፣ ጥቁር ነኝ፣ ስደተኛ ነኝ፣ ችግረኛ ነኝ፣ አካለ ስንኩል ነኝ፣ ሆድ የባሰኝ ነኝ፣ መጠቋቆሚያ ነኝ... እድል ስጡኝ፣ አካቱኝ፣ አስቀድሙኝ፣ አታወዳድሩኝ እዘኑልኝ እንጂ!

ተጨቁኛለሁ፣ ተገፍቻለሁ፣ ተደፍቻለሁ፣ ተረግጫለሁ፣ ተጎድቻለሁ፣ ተደፍሬያለሁ፣ ተበድያለሁ፣ ተዘርፌያለሁ፣ ተበዝብዣለሁ፣ ተንቄያለሁ፣ ተፈትቻለሁ(የትዳር ፍቺ)፣ ተገልያለሁ፣ ተሰድጃለሁ፣ ተቸግሬያለሁ …!

ብሶተኝነት ችግርን ወደ ችጋር ለውጦ፣ እንደ ሐምሌ ዝናብ “እኝኝኝ..ኝኝኝ...” ማለት አመልህ ያደርገዋል። በየትኛው ከባቢ ውስጥ ቢኾን እንኳ ከዚያ አንዳች ሰበብ እየፈለገ እድሜ ዘላለሙን ማላዘንና መነፋረቅን ለባለቤቱ ሰጥቶ በእርሱ ላይ እርሱን ኾኖና አክሎ ይገለጣል።

በብሶት ተወልዶ፣ ብሶትን እየጠባና እየተጋተ ላደገው ትውልድ ምን የገፋውን አካል ድል ቢነሳ፣ ወርቅ ለብሶና ተጫምቶ፣ ወርቅም ተነጥፎለት ቢቀመጥ፤ ምን ቢራቀቅና ቢመጥቅ ከብሶተኝነቱ አይላቀቅም።

ይኹንና ሆደ ባሻ በኾነ ቁጥር ደስ ያለውን ሲወቅስ፣ ደስ ያላለውን ሲከስ፣ የከፋበትንም ሲገድል፣ ገድሎም ከመቃብሩ ላይ ሲነግሥ እፎይታን፣ ይኹንታን፣ ተቀባይነትን የሚያገኝ ይመስለዋል።

በእርግጥ የብሶቱ መፍለቂያ፣ መፈንጪያና መቀመጫ ከሩቅ ከእርሱ ውጪ ያለ ይመስለዋል እንጂ መገኛ መፍለቂያውስ ከልቡ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ “በአዋቂዎቹ” ተጠምቆ ከተጋተው “ብሶተኝነቱ” መኾኑን አያውቅም!

🌟 በብሶት ስትኖር መሠረትህን አትወደውም!

🌟 በብሶት ስትወለድ ትናንትናህን አትፈልገውም!

🌟 በብሶት ስታድግ ትውፊትህን አትቀበለውም!

🌟 በብሶት ስትገለጥ ራስህን አታየውም!

🌟 በብሶት ስትገኝ ማንትህን አትወደውም!

🌟 በብሶት ስታይ እውነትን አትለየውም!

🌟 በብሶት ስትዳኝ ሕይወትን አትበይነውም!

🌟 በብሶት ስትመሠረት መሠረት አይኾንህም!

🌟 በብሶት ስትወልድ ሐቁን አታወርሰውም!

🌟 በብሶት ስትሾም ፍትሕን አታሰፍነውም!

🌟 በብሶት ስትመላለስ ራስህን አትኖረውም!

🌟 በብሶት ስትደናበር ብርሃንን አታወቅውም!

🌟 በብሶት ስትናገር ልብህን አትሰማውም!

🌟 በብሶት ስታስብ አእምሮህን አታሠራውም!

🌟 በብሶት ስትሳፈር ከስሜት ወጪ አትጋልበውም!

🌟 ብሶተኝነት ጥፋትና ሙስና እንጂ ልማትና ብልጽግና የለውም!

ይኹን እንጂ ብሶትን ጠላት ይፈልገዋል፣ ሆዳደሩም ትውልዱን ያስታውሰዋል፣ አሰሱም ከተጠያቂነትን ይሸሽግበታል፤ በስሜት ለሚነዳው ትውልድም ኹነኛ ልጓም ይኾናል!

ብሶተኝነት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የነበረ ቢኾንም በጽንሰሃሳብነት አርግዞት ርዕዮተዓለም እንዲኾን አምጦ የወለደው ግን ካርል ማርክስ ነው።

በእርሱም “ለተበዝባዡ፣ ለጭቁኑ፣ ለተበዳዩ” ሰው ለብዝበዛው፣ ለጭቆናው፣ ለበደሉ ማለቂያ መቋጪያ፣ መደምደሚያ ጠፍቶለት የብሶት ትርክት እየተረከ ከተፈጥሮውና ከፈጣሪው ይለይበታል።

ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብሶተኝነት ትውልድን ከተፈጠረበት፣ ከተገኘበት፣ ሰውነቱ ከተበየነበት፦ ተፈጥሮው፣ ባህሉ፣ እምነቱ፣ ወጉ፣ እሴቱ በተበዳይነት-ብሶተኝነት ወደ “መብትና ነፃነቱ” እየራቀ፤ ሰውነቱ ጠፍቶ የእንሰሳት መደብ እንኳ የማይመጥነው ኾኖ እየጠፋ ይገኛል።

አንተ ወንድ ነህ! ከወንድም አባወራ ምን ብትቸገር ችግርህን በመፈትፈት፣ በመዘርዘር፣ በማስጣት፣ በማስጣጣት፣ በማላዘን፣ በመነፋረቅ ወደ ችጋር ልትቀይር አይገባህም!

ልትገፋ ልትደፋ፣ ልትበደል፣ ልትገለል፣ ልትናቅም ትችላለህ! እንዲያ ያስደረገ ክፉ ጠባይ ካለብህ ጣትህን ሰው ላይ እየጠቆምክ ከማላዘን አስተካክል! ከሌለብህ ግን የለብህም አንተ አይደለህምና የሰጡህን ተቀብለህ አታላዝን!

🌟 ቅር ያሰኘህ፣ ሆድህን ያስባሰህ ያንተ የኾነን ነገር መቀየር የምትችል ከኾነ ያንጊዜ፣ እዚያው ጋር፣ ባወቅክበት ቅጽበት ለመቀየር ወስን!

የማትቀየረውን አንተን ግን ተቀበል! ለምሳሌ የመጣህበትን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ... ያንተ የኾነውን፣ አንተ ካልተቀበልከው ማንም አይቀበልህምና ሌላው ስላልተቀበለው አትከፋ ሆድ አይባስህ፤ ክደህ የምታስክደውን፣ ንቀህ የምታስንቀውን አንተን አምነህ ተቀበለው እንጂ!

ብሶተኛ ከኾንክ በራስህ ላይ ልዕልና ሉዓላዊነትም አይኖርህም! ይልቁንስ ላንተ ያሰቡ ይመስል ብሶትህን እያራገቡ፦ የሚያበሉህን፣ የሚያጠጡህን፣ የሚያለብሱህን፤ በዚያም የሚዘውሩህን በራስህ ላይ ትሾማለህ እንጂ!

ብሶት፦ ወንድነት ጥበቃህን፣ አባትነት ምሳሌህን፣ ባልነት ዘርህን፣ ራስነት ምሪትህን ይሽራቸዋል። በቦታቸውም ምሬትና ሮሮን፣ ሰበብና ለቅሶን ይተክላቸዋል። አንተን እያዩም ሚስትህና ልጆችህ ቤተሰብህም የሚከተሉህ ይኾናል።

ይህም የአንድ የአንተ ጠባይ ወደ ቤተሰብህ ተጋብቶ ሲቆይ ከውጪ ላለ ተመልካች በዘር የሚተላለፍ ይመስላል። ከቤተሰብ ወደ ማኅበረሰብ ሲዛመት፣ በሌሎቹም ሲደገምና ብሶቱ ከግለሰባዊነት ወደ ማኅበራዊነት ሲሻገር ደግሞ ለማኅበሩ ይኾናል።

ብሶተኝነት እውነትን ከሚፈልገው፣ እውነትን ከሚገልጠው፣ በእውነት መገለጥ ከሚሻው ወንድነት ከአባወራነቱም ልዕልና ለይቶ ያጠፋሃል!

እደግመዋለሁ! “አልተቸገርክም፣ አልተገፋህም፣ አልተበደልክም...” አላልኩህም ነገር ግን በተገፋህበት መጠን ተጠቅመህ ጽድቁን ወደሚፈጽም ልዕልና እንድትወጣ፣ በተበደልክበትም ልክ ጣፍጠህ ያለምን አልጫ ልታወጣ መጣህ እንጂ።

የአንድ ሰሞን ችግሩን ሊታነጽበት ሲገባ እየመነዘረና እየዘረዘረ ዘለዓለም ችጋርን የሚዘራ ፍጥረት ብሶተኛ ሰው ብቻ ነው፤ አባቱ ባለጸጋ እንደኾነ ማወቅና መረዳት የተሳነው!

ወንድምዓለም! መቸገረን፣ መገፋትን፣ መሳደድን ሳላውቀው ቀርቼ ይህን አልጻፍኩልህም። ነገር ግን በዚያ ማለፉ ለምትኖርለት ጽድቁ ሊያነጥርህና ሊያጠራህ ይችላልና ፈቃድህን ፈጽም!

ይኹን እንጂ እርሱም አልፎ አንተ ግን እያስታወስክ መጥራቱ ዛሬም ያንን የምትጠላውን የምትኖረው፣ የምትደግመው፣ የምትናፍቀው፣ የማትለየው፣ እንዲለይህም የማትፈልገው፣ በፈቃድህ በራስህም ላይ የምትጭነው ይኾናል።

ራስህን ጠይቅ ብሶተኛ ነህን?

Post a Comment

0 Comments