የመከራ ጊዜ ጽድቅ፤ ከመልካም ጊዜ ንግድ


ማስታወሻ፦ "እኔ መምህር አይደለሁም ! አስታዋሽ እንጂ። እያስተማርኳችሁ አይደለም በአባቶቻችን ብዙ የተደከመብን፤ እስከሞት ድረስ ዋጋ የተከፈለልን መሆናችንን እያስታወስኳችሁ እንጂ።"

ክፍል ፩፦ በምቾት የታወረ ጽድቅ 

✍ ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ

​በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ፣ በታላቁ የአቡነ አረጋዊ ገዳም አቅራቢያ የሚኖር አንድ "ባለጸጋ" ነበር። እርሱ ዘወትር ነጭ ጋቢውን ይለብሳል፣ በእጁ የወርቅ መስቀል (በትረ መስቀል) ይይዛል፣ በቤተክርስቲያንም ሲቆም ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጸልያል። ምድሩ በረከት አውጥታለች፣ ጎተራው በሰብል ተሞልቷል፣ ዝናቡም በጊዜው ይዘንባል። ይህ ባለጸጋ በዚያ በደግ ዘመን እርሱን የሚያህል ጻድቅ ያለ አይመስልም ነበር። በስጋዊ ሩጫው መካከልም ቢሆን፣ "እግዚአብሔር ስለ ጽድቄ (ስለ ቀናው መንገዴ) ሰጠኝ" እያለ ራሱን ያሞካሽ ነበር።

​ነገር ግን አንድ ምሽት፣ ራእይ የመሰለ ክስተት ሆነ። ምድሪቱ ተንቀጠቀጠች፣ ሰማዩም እንደ ብረት ጠጠረ። ድርቅ መጣ። የዚያ ባለጸጋ ጎተራ ባዶ ሆነ፤ ከብቶቹም በፊቱ አለቁ።

​ያን ጊዜ፣ ያ ለዓመታት "አመሰግንሃለሁ" ይል የነበረው አንደበት በክፉ ቃላት ተሞላ። "አምላክ የለም! ቢኖርማ እንዲህ አያደርገኝም ነበር" ብሎ ጮኸ። ያ የወርቅ መስቀልም ከእጁ ወደቀ። ጽድቁ እንደ ጥላ ከብርሃን ጋር አብሮ ጠፋ።

ዛሬ ​የመቃብር አፋፍ ላይ የቆመ ትውልድስ ሲመረመር ምን ይገኛል?

​ይህ ታሪክ የእኔና የእናንተ የዛሬው ሕይወት መስታወት ነው። ዛሬ በሥጋዊ ሩጫ ተጠምደናል፤ አእምሯችን በ"ነገ ምን እበላለሁ? ምን እለብሳለሁ?" ጭንቀት ታውሯል። በደግ ጊዜያችን (ጊዜ ርቱዕ) ሁላችንም ጻድቃን ነን። ኪሳችን ሲሞላ "ሃሌ ሉያ" እንላለን፤ ማዕዳችን ሲሞላ "አምላክ ቸር ነው" እንላለን።

​ነገር ግን ከ መጽሐፍ ቅዱስ በሲራክ ፲፪፥፰ ላይ እንዲህ ሲል ያጋልጠናል።

​“ሰው በሀብቱ ጊዜ አይታወቅም፤ ጠላቱም በችግሩ ጊዜ አይሰወርም።” 😔

በዚህ ታሪክ ፊት ራስህን ያገኘው ወንድሜ፤ ራስሽን ያገኘሽው እህቴ፦

​ይህ ቃል ዛሬ የቆምክበትን አሸዋማ መሠረት ይነቀንቀዋል። ጽድቅህ የጥቅም ነው! ጸሎትህ የእግዚአብሔርን እጅ ለመሳብ እንጂ ፊቱን ለመፈለግ አይደለም። በሥጋዊ ሩጫህ እግዚአብሔርን እንደ ሎጅስቲክስ ድርጅት እንጂ እንደ ነፍስህ መድኃኒት አታየውም።

​የጽናት መለኪያ (ከገድላተ ቅዱሳን)

​ወደ ገድለ ሰማዕታት ተመልከቱ! ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽድቁ በጊዜ ርቱዕ አልነበረም። ሰባ ነገሥታት በፊቱ ሲዝቱበት፣ ሥጋው በመጋዝ ሲሰነጠቅ፣ በኖራ ጉድጓድ ውስጥ ሲጣል የነበረው ጽናት ነው እውነተኛው ጽድቅ። የእርሱ ጽድቅ መከራ ሲመጣ ይበልጥ ደመቀ፤ የእኛ ግን ምቾት ሲመጣ ብቻ ይበራል።

​ራስን የመፈተሽ ሰዓት፦ አንተ ምን ላይ ቆመሃል?

​ወንድሜ ሆይ! እኅቴ ሆይ! ዛሬ ቆም ብለሽ ራስሽን መርምሪ። ጽድቅሽ እንደ ፀሐይ ጥላ ከሆነ፣ ጨለማ (መከራ) ሲመጣ መክዳቱ አይቀሬ ነው። እግዚአብሔርን የምትከተዪው ስለ ሰጠሽ "እንጀራ" ከሆነ፣ እንጀራው ባለቀ ቀን ክርስቶስን ትሰቅዪዋለሽ።

ጥያቄ ለእኔ/ለአንተ/ለአንች? 

▫ ​ዛሬ እያመለክሽ ያለሽው እግዚአብሔርን ነው ወይስ በረከቱን?
▫ ​ዛሬ የምትሮጠው ለነፍስህ ነው ወይስ ለማይጠግብ ሥጋህ?

​ጊዜው ቢከፋ፣ ሀብትህ ቢጠፋ፣ ጤናህ ቢታጣ... አሁንም "ስሙ የተባረከ የተመሰገነ ይሁን" ትላለህ ወይስ እንደ ባለጸጋው የክብር በትረ መስቀሉን ትጥላለህ?

ጊዜውን ሁላችንም የምናውቀው ነው ወገኖቼ! ​ነፍስህ የመቃብር አፋፍ ላይ ቆማለች! ይህ "ጊዜ ርቱዕ" (የደግ ጊዜ) የንስሐ ጊዜህ ነው። ሞት ሳይቀድምህ፣ መከራ ሳይዘርርህ፣ ከሥጋዊ ሩጫህ ቆም በልና መሠረትህን በዓለት ላይ አንጽ። ካልሆነ ግን፣ ማዕበሉ ሲመጣ ውድቀትህ ታላቅ ይሆናል።

​ክፍል ፪፦ "በአዲስ ጠያቂ ርዕስ" እንመጣለን። እስከዛው የክፍል ፩ን ጥያቄ ለራሳችን እንጠይቅ!

Post a Comment

0 Comments