ነቀርሳ ጉንፋን አይደለም! እርሱን አምጪ ተውሳኮችን እንደታወቁ ካላጠፏቸው ነቀርሳ ሲኾን ያጠፋል! የጽንሰሃሳብ ነቀርሳዎችም እንዲሁ ናቸው!
ክፉ ሐሳብ በጭብጡ ልዕልና ወይም በመልእክቱ ቅድስና አሸንፎ አያውቅም። በጥበብ ትሕትና ተረድቶት፣ ማሸነፊያ ገንዘቡን ላልዋጀበትና “...የትም አይደርስም...” ብሎ ለናቀው ትውልድ ግን መቀበሪያ ምሱን ሳይቆፍርለት አይቀርም!
ዛሬ ዓለምን እየዘወሯት ያሉት እውነተኛ ሙግት ያላቸው አሸናፊ ሐሳቦች አይደሉም፤ ይልቁንስ “በአጉል አዛኝ ቅቤ አንጓችነት” ተጠፍጥፈውና ጣፍጠው የቀረቡ፣ ነገር ግን ትውልድን ከውስጡ ልብልቡን የሚበሉ ተውሳኮች ናቸው።
ምዕራባውያን ትናንት በሴቶች ከወንዶች “እኩልነት”፣ እርግዝናቸውን የመወሰን “መብት”፣ ያልፈለጉትን የማስወረድ “ነፃነት”፤ ዛሬ አድጎ ማንነታቸውን፣ ጾታቸውንም ጭምር እስከ “መወሰን” አድርሷቸዋል።
መጀመሪያውኑ ጽድቅ የመሰለው፣ ነገር ግን ብሶት የሚጠምቀው ማርክሳዊ ተውሳክ ተገቢውን ጥያቄ አጣሞና አራግቦ ሲያቀጣጥለው ዝም መባሉ ዛሬ ማባሪያ ማቆሚያ ላጣው ነቀርሳ የኾነ አጥፊ “ጽንሰሃሳብ” ተላልፈን ተሰጠን!
የሮሚና እስትራቲ ፕሮጀክት ድልድል እና የአሉላ ፓንክረስቱ ያንግ ላይቭስ ከእንግሊዛውያን የሚያጋቡብን እንዲህ ይህንን መሰሉን ተውሳክ ነው።
እርስ በእርሳቸው የማይተማመኑ እንደ ጃርት የሚፈራሩ ትውልዶችን በብዛት አፍርተው፤ ጋብቻን ፈርተው፣ ልጆች ከመውለድ ታቅበው መቅረታቸው ሳያንስ፤
ያገቡት እንኳ ልጅ እንዳይወልዱ በዓይነትና በብዛት በቀረበላቸው የእርግዝና መከላከያ ማርገዝ መውለዱን አዘግይተው ብሎም አስቀርተውና ቀርቶባቸው፤
የተረገዙትን እንኳ ሰበብ እየተፈለገ በዚያው በማኅጸናቸው እያሉ በእናቶቻው ፍርድ በመቀስና በመርዝ ቆራርጠውና በጣጥሰው ለአጋንንት እየሰውአቸው፤ ይህም ከመብት ተቆጥሮ(SRHR)፤
(ልብ አድርጉ በዓመት 73 ሚሊዮን ሕጻናት በዚያ አንባገነን፣ በዘሰባዥ፣ ጨቋኝና፣ በዳይ አባወራ የሚገደሉ አይደሉም፤ ይልቁንስ አሳቢና አዛኝ በኾኑት ነገር ግን “ሕልማቸውን” ለመኖር በመረጡት እናቶቻቸው እንጂ!)
ከእነዚህም የተነሳ ተተኪ ሀገር ተረካቢ ትውልድ አጥተው ተቸግረው እንዳሉ እየታወቀ፤ እነርሱ የሄዱበትን ይህንኑ የጥፋት መንገድ ለእኛም ይግቱናል!
የእነርሱን የጥፋት መንገድም “አይኾንም! በልጆቻችን አይደረግም!” ያለውን የሚስቱን፣ የልጆቹን፣ የቤተሰቡን፣ የትውልዱን ጠባቂ አባትና ሥርዓቱን ግን ሥር የሰደደ ጎጂና ጨቋኝ ይሉታል፤ (Entrenched Patriarchal Norms)!
ይህም የጥፋት መንገድ “ሊቅ፣ አጥኚ፣ ተመራማሪ፣ የፖሊሲ ምክረሃሳብ ሰጪ፣ ፖሊሲ አውጪ” በተባሉ የራሳችን ሊቃውንት በሀገራችን ሊደገም ከጫፍ ደርሷል!
እነርሱ “ውርጃን”፣ “መብት” ለማድረግ ይቸኩላሉ። ሴቷ በየስርቻው ‘ያለባለሙያ’ የምትፈጽመው ውርጃ ለጤናዋ ጎጂ ነው፣ ‘በብቁ ባለሙያዎች’ ጽንሱ በመቀስ ተቆራርጦ፣ በመርዝ ተበጣጥሶ ሊወጣ ይገባል” ሲሉ ለእርሷ ያሰቡ ይመስላሉ!
ምዕራባውያን ትናንት “የትም አይደርሱም” ያሉዋቸው ይህን መሰል መርዘኛ ሃሳቦችን የያዙ ሰዎች ተነስተው፦ መጋባትን ሲጠሉ፣ ጾታቸውን ሲቀይሩና ይህንኑም ሲያስተምሩ “...ይህ ከንቱ ሃሳባቸው በራሱ ጊዜ ተኖ ሲጠፋ ያበቃለታል...” ብለው ንቀዋቸው ነበር። ዛሬ የሰውን ዘር፣ የልጆቻቸውንም ሕይወት ከሰውነት ጎዳና አውጥተው እንዲጠፋ እንዲማስን አድርገውታል።
“እስኪጠፋ” በተጠበቀው ክፉ ሐሳብ፣ አስቀድመው እነርሱ ራሳቸው እየጠፉ፣ ልጆቻቸውንም እያጡ፣ ሀገሮቻቸውም ዓይናችን እያየ እተለወጡ መጡ።
ዛሬ በዩናይትድ ኪንግደም በዓመት 300,000 ፅንስ ማስወረድ (Abortion) እንደ ተራ ስታቲስቲክስ መቆጠሩ፣ ነቀርሳው ከትውልዱ ሰውነት ገብቶ፣ ከልቡ ተጣብቶ ምን ያክል አስተዋይ ልቡን እንዳጠፋው ማሳያ ነው።
ይህ ተፈጥሮን የመጥላትና አባታዊ (Patriarchal) ሥርዓትን የማፍረስ ንቅናቄ መጨረሻው መክኖ መጥፋት መኾኑን ሩቅ ሳንሄድ አሁን ባቀረብኩላችሁ፣ ከዚህ በፊትም በላኩላችሁ ማየት እንችላለን።
ዛሬ ጃፓናውያንና ደቡብ ኮርያውያን መጋባትን ጠልተው፣ ተተኪ ትውልድ አጥተው፣ እንደ ማኅበረሰብ እየጠፉ ነው። “የትም አይደርስም” የተባለለት የፌሚኒስቶቹ ከፍተኛ ተፈጥሮን ጠል ንቅናቄ፣ ዛሬ ዓይናችን እያየ ከምድረ-ገጽ ሊያጠፋቸው ተቃርቧል።
እኛ ግን ከእነርሱ እየተማርን አይደለም፤ ለመማርም የልባችን በር በትሕትና አልተከፈተምና ወደዚያው ከመጥፊያችን ገደል እያመራን ነው።
UN Women፣ ፕሮጀክት ድልድል፣ ያንግ ላይቭስ እና መሰል ሌሎችም ድርጅቶች በሴቶች እኩልነትና ነፃነት ስም የሚያቀርቧቸው ፖሊሲዎች መጀመሪያ ጽድቅ ይመስላሉ።
ነገር ግን በተለከፉበት ብሶት ጠማቂው ማርክሳዊ ተውሳክ አማካኝነት ተገቢው ጥያቄ ተጣሞ እንዲራገብ፣ በብሶት ጭረት ጥላቻና ልዩነት እንዲቀጣጠል በማድረግ፣ አባታችንንና አባታዊ ሥርዓቱን እንድንጠላ እየመከሩን ነው።
ይህ “አዛኝ ቅቤ አንጓችነት” እናትን ከልጆቿ፣ አባትን ከቤቱ ነጥሎ፣ ትውልድን መድረሻ የሌለው ባዕድ መረንም እያደረገው እያጠፋውም ይገኛል።
እኛ “አባወራዎቹ” ግን፦
💪 የእናት የአባቶቻችን ልጆች፣
💪 የውድ ሚስቶቻችን ባሎች፣
💪 የጣፋጭ ልጆቻችንም አባቶች፣
💪 የቤተሰባችን፣ የማኅበረሰባችንም መሪዎች ጠባቂዎችም ነንና ይህ ክፉ ሃሳብ “ራሱ እስኪጠፋ” አንጠብቀውም!
በጭራሽ! ነገር ግን እውነት የኾነ እውቀትን ታጥቀን፣ ለጽድቅ የሚያስጨክን ወኔ-ልባችንን ይዘን፤ ራሱ እስኪጠፋ ሳንጠብቅ ሳያጠፋንም እናጠፋው ዘንድ በወንድነት ለመስዋዕትነት ከተለየንበት ሚናችን የተነሳ እንዘምትበታለን!
ነቀርሳ ያደረበትን ሰውነት ሳያጠፋ አይጠፋም! እንደ ማኅበረሰብ የገባብንን የጽንሰ-ሃሳብ ነቀርሳ “የትም አይደርስም” ብለን ከናቅነው፣ መቀበሪያ ምሳችንን ቆፍሮ ጨረሶን መቅበሩ አይቀሬ ነው።
የደቡብ ኮርያ፣ ጃፓን ምክነት፣ የምዕራባውያን የፅንስ ግድያና የቤተሰብ መፈራረስ ብናስተውል ለእኛ ትልቅ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው። ክፉ ሃሳብ ጣፍጦ ቢቀርብም በውስጡ የሰወረው መርዙ ግን ገዳይ ነውና አስተዋይ ልብ እንያዝ።
ልቡ በአስመሳይ፣ አታላይና አድርባይ ሰዎች ክፉ ሃሳብ-ተውሳክ የጠፋበት ትውልድ ፈጥነው መድኃኒቱን ካልጠቆሙት፤ ነቀርሳ ኾኖበት ልቡን አጥፍቶት ሳያጠፋው አይቀርም፤ እንጂ በራሱ አይድንም!
0 Comments