ክፍል ፬ ጠያቂ ትምህርት
✍ ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ
የሞት ጥላ በታላቁ የኢየሩሳሌም ቤተ መንግሥት ላይ አጥልቶ ነበር። የሕዝቡ ጠባቂ፣ ኃያሉና ጻድቁ ንጉሥ ሕዝቅያስ በአልጋው ላይ በጠና ታሞ ወድቋል። በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሐኪሞች ሹክሹክታና የአገልጋዮች የጭንቀት ፊቶች ብቻ ይታያሉ።
በዚህ የመጨረሻ የጭንቅ ሰዓት፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ክፍል ገባ። የነቢዩ ፊት እርጋታ የሞላው፣ ይዞት የመጣው ቃል ግን እንደ መብረቅ የሚያንቀጠቅጥ ነበር፦ "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል።"
ይህ የማስጠንቀቂያ ቃል አልነበረም፤ የመጨረሻ የሞት ፍርድ እንጂ። የዓለም ሐኪሞች እጃቸውን ሰብስበዋል፤ አሁን ደግሞ ከሰማይ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቃል መጣ። ሕዝቅያስ ግን ከነቢዩ ጋር አልተከራከረም። ዘውዱንና የነገሥታት ግርማውን ረሳው። ኃይሉ ሲሟጠጥ፣ አንድ የመጨረሻ መሸሸጊያ ብቻ ነበረው። ፊቱን ወደ ግድግዳው አዞረ።
በእርሱና በግድግዳው መካከል ማንም አልነበረም፤ ከፈጣሪው ጋር ብቻውን ቀረ። ከዚያም እንደ ሕፃን ልጅ አምርሮ አለቀሰ። "አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ በፊትህም መልካም የሆነውን እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ" ብሎ ተንሰቀሰቀ። የእንባው ሙቀትና የልቡ ስብራት የቤተ መንግሥቱን ጣሪያ አልፎ፣ ሰማየ ሰማያትን ሰነጠቀ።
አስገራሚው ነገር የተፈጠረው እዚህ ላይ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ መልእክቱን አድርሶ ከቤተ መንግሥቱ መካከለኛ ግቢ ገና አልወጣም ነበር፤ የእግዚአብሔር ቃል ድንገት መጣበት፦ "ተመለስ! የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህን አይቻለሁ፤ እነሆ እፈውስሃለሁ... በእድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ!" አለው።
ነገር ግን የሰው ልጅ ልብ ማረጋገጫ ይፈልጋልና፣ ሕዝቅያስ "መፈወሴን በምን አውቃለሁ? ምልክቱስ ምንድን ነው?" ሲል ጠየቀ። ኢሳይያስም ፈጽሞ ሊታመን የማይችል ምርጫ አቀረበለት፦ በአባቱ በአካዝ የሰዓት መለኪያ (ደረጃ) ላይ ያለው የፀሐይ ጥላ አሥር እርምጃ ወደ ፊት ይሂድ ወይስ ወደ ኋላ ይመለስ? አለው!
ሕዝቅያስም መለሰ፦ "ጥላው ወደ ፊት ማዘንበሉ ቀላል ነው፤ ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን... ጥላው ወደ ኋላ ይመለስ!" (ሰዓቱ ወደኋላ ይመለስ!) አለ።
ያን ጊዜ ጸጥታ ሰፈነ። የዓለም የጊዜ ስሌት ተናጋ። በሰማይ ላይ የምትጓዘው ፀሐይ አካሄዷን ገታች። ተፈጥሮ ለፈጣሪዋ ድምፅ ታዛ፣ ፀሐይ በሰማይ ላይ ቆመች፤ ከዚያም ወደ ኋላ አፈገፈገች! በጥንታዊው የሰዓት መለኪያ ላይ ጥላው አሥር እርምጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።
በኦርቶዶክሳዊ ትርጓሜ፣ ይህ የፀሐይ ወደ ኋላ መመለስ ታላቅ ምስጢር አለው። እግዚአብሔር ለንስሐና ለጸሎት ሲል፣ በኃጢአትና በስንፍና ያባከንነውን፣ ያመለጠንን "የጠፋ ጊዜ" እንኳ ወደ ኋላ መልሶ ሊያድስልን እንደሚችል የሚያሳይ ሕያው ማረጋገጫ ነው። ጊዜ ራሱ ለእውነተኛ ጸሎት ሲል ተንበረከከ።
ጥያቄ አለኝ! ለእኔም ፤ ለአንተም ለአንችም?
▫ የሕይወትህ በሮች ሁሉ ሲዘጉብህና ሰዎች ተስፋ ሲያስቆርጡህ፣ ፊትህን እንደ ሕዝቅያስ ወደ ማነው የምታዞረው? ወደ ሰዎች ወይስ ወደ ግድግዳው (ወደ አምላክህ)?
▫ "አበቃ፣ አከተመ" በተባለለት ታሪክህ ላይ፣ በእንባህ ኃይል፡ በተሰበረው ልብህ ጩኸት በመረረ ንስሐ አዲስ ምዕራፍ መክፈት እንደምትችል ታውቃለህን?
▫ አምላክህ ዛሬ ፀሐይን አቁሞ ያባከንከውን ዘመንህን ቢመልስልህ፣ አዲሱን ጊዜህን በምን ታሳልፈዋለህ? መልስ ያስፈልግሃል !
0 Comments