(ክፍል ፮ ጠያቂ ትምህርት)
✍ ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ
በእስራኤል ተራሮች ላይ ጽኑ ጭጋግ በነገሠበትና የፍርሃት ጥላ በሰፈረበት በዚያ ዘመን፣ አንድ አስደናቂ ትንግርት በዝምታ መሃል ተጠነሰሰ። ይህ ታሪክ ስለ ሺዎች ሠራዊት ወይም ስለ ግዙፍ የጦር መሣሪያዎች አይደለም፤ ይህ ታሪክ በሁለት ሰዎች ልብ ውስጥ ስለነደደው እሳትና ስለማይቻል ድፍረት የሚተርክ የመለኮታዊ ድል ምስጢር ነው።
እነሆ፣ የዮናታንና የጋሻ ጃግሬው አስደማሚ ጉዞ (፩ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ ፲፬)።
የእስራኤል ንጉሥ ሳኦልና ስድስት መቶ የሚሆኑ ተዋጊዎቹ ከአንድ ትልቅ ሮማን ዛፍ ሥር ተጠልለው ተቀምጠዋል። ከፊታቸው ግን የፍልስጥኤማውያን ሠራዊት እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶ፣ በሠረገላና በፈረሰኛ ታጅቦ ተራራውን ለተመልካች አስፈሪ በሚመስል ግርማ ወርሶታል። እስራኤላውያን በፍርሃት ወደ ዋሻና ወደ ገደል ተሸሽገዋል። ሰማዩ በጸጥታ ተውጧል፤ ተስፋም እንደ ጧፍ ኩስታሪ እየጠፋች ነበር።
በዚህ የጭንቀት ሰዓት፣ የሳኦል ልጅ ልዑል ዮናታን ለጋሻ ጃግሬው ብላቴና እንዲህ አለው፦ "ና፤ ወደነዚህ ወዳልተገረዙት ሰዎች ጭፍራ እንለፍ፤ ምናልባት እግዚአብሔር አንድ ነገር ያደርግልን ይሆናል፤ እግዚአብሔር በብዙ ወይም በጥቂት ለማዳን አይሳነውምና።"
ይህ ቃል ተራ ድፍረት አልነበረም፤ "ምናልባት እግዚአብሔር አንድ ነገር ያደርግልን ይሆናል!" የምትለው ንግግሩ ተስፋን በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ የመጣል ታላቅ ትሕትናና እምነት ነበረች። ጋሻ ጃግሬውም በታማኝነት፦ "ልብህ የወደደውን ሁሉ አድርግ፤ እነሆ እኔ እንደ ልብህ ከአንተ ጋር ነኝ" አለው። ይሄኔ ሁለት ልቦች በአንድ ዓላማ ተሳሰሩ።
ወደምስጢራዊው ረቂቅ ጉዞ እንለፍ...
ወደ ጠላት ሰፈር ለመድረስ በሁለት ገደላማ ድንጋዮች መካከል ማለፍ ነበረባቸው። አንደኛው "ቦጽ" (የሚያበራ)፣ ሁለተኛው "ሴኔ" (እሾሃማ) ይባላሉ። እነዚህ ድንጋዮች የሕይወት ተምሳሌቶች ናቸው፤ ወደ ድል ለመድረስ በፈተና (እሾህ) እና በጽናት (ብርሃን) መካከል ማለፍ ግድ ይላል።
ዮናታን ምልክት ፈለገ። "ለጠላቶቻችን እንታያቸው፤ እነርሱም፦ 'ወደ እኛ ውጡ' ካሉን፣ እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል ማለት ነው" አለ። ዮናታንና ብላቴናው ከገደሉ ወጥተው ታዩ። ፍልስጥኤማውያንም በፌዝ፦ "እነሆ፥ ዕብራውያን ከተደበቁበት ጉድጓድ ወጡ" እያሉ ሳቁባቸው። "ወደ እኛ ውጡና አንድ ነገር እናሳያችኋለን" ሲሉ ጮኹ።
ምልክቱ እንደ ቃላቸው እንደ እምነታቸው ከእግዚአብሔር ተሰጠ! ዮናታን ለብላቴናው፦ "እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና በኋላዬ ውጣ" አለው። አሁን ታሪኩ ይበልጥ አስደማሚ ይሆናል። ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው ቆመው ሳይሆን "በእጃቸውና በእግራቸው" እየዳኹ በዚያ አቀበት ላይ ወጡ።
ይህ ትልቅ ምስጢር አለው። ወደ መንፈሳዊ ድል የሚደረግ ጉዞ በትሕትና (በመድፋት) የሚጀመር ነው። ጠላት "ወደቁ" ሲላቸው፣ እነርሱ ግን ወደ ሰማያዊ ድል እየተሳቡ ነበር። ኮረብታው ላይ እንደደረሱም፣ ዮናታን መምታት ጀመረ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከኋላው ሆኖ ይገድል ነበር። በግማሽ እርሻ በሚያህል ጠባብ ስፍራ ውስጥ ሀያ የሚሆኑ ሰዎችን በድንገት ረቷቸው። ፈጇቸው።
በዚያች ቅጽበት ሰማይና ምድር ተባበሩ። በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ውስጥ ታላቅ ድንጋጤ ሆነ፤ ምድርም ተናወጠች። ያ ድንጋጤ "ከእግዚአብሔር ዘንድ" የመጣ ነበር። ጠላቶች ግራ ተጋቡ፤ አንዱ ሌላውን በሰይፍ ይወጋ ጀመር።
በሮማን ዛፍ ሥር ተቀምጠው የነበሩት ንጉሡ ሳኦልና ጭፍሮቹ ሰፈሩ ቀየው ሲታወክ አዩ። ዮናታንና ብላቴናው ግን ብቻቸውን የሺዎችን ሠራዊት አናውጠውት ነበር። በዚያ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን በዮናታን ድፍረት አዳነ።
ወንድም እህቶቼ! እስኪ ልብ በሉና ረቂቅ ወደሆነው ትንተና እንሻገር...
የዮናታን ታሪክ የብቸኝነት ድል ሳይሆን የ"ሃይማኖትና የታማኝነት" ምስጢር ነው፦
💚 ዮናታን፦ በክርስቶስ መሠረትነት የጸና በእሱ ፈቃድና እውነት የሚያምንና በጸጋው የሚታመን የአንድ እውነተኛ ክርስቲያን ተምሳሌት ነው።
💛 ጋሻ ጃግሬው፦ "እንደ ልብህ ከአንተ ጋር ነኝ" የሚል፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ፈጻሚና አስፈጻሚ ባሮቹ ራሱን ዝቅ በማድረግ የሚታዘዝና የሚከተል ታማኝ የሆነ አገልጋይ ምሳሌ ነው።
❤ በእጅና በእግር መሳብ፦ መንፈሳዊ ተጋድሎ ጥረትንና ትሕትናን፤ መውደቅና መነሳትን እንደሚጠይቅ ያሳያል።
🔔 የሕይወት መስተዋት፦ ራስን የመፈተሻ ጥያቄዎች፦
እስኪ ይህን አስደናቂ ታሪክ በልብህ እያብሰለሰልክ፣ እነዚህን ነጥቦች በራስህ እምነትና ሕይወት መዝን፦
▫ የአንተ "ቦጽና ሴኔ" ምንድን ናቸው? በሕይወትህ ድል ለማግኘት በምትጓዝበት መንገድ ላይ ያሉብህ መሰናክሎችና እሾሆች ጋሬጣዎች ተስፋ አስቆርጠውሃል? ወይስ እንደ ዮናታን "እግዚአብሔር ለማዳን አይሳነውም" ብለህ ትጓዛለህ?
▫ እንደ ጋሻ ጃግሬው ታማኝ ነህ? በጎ ነገር ለሚጀምሩ ወንድሞችህ፤ መንፈሳዊ መሪዎችና ሥጋዊ የሥራ ባልደረቦችህ ቀና በሆነው ምክር ኹሉ "እኔ እንደ ልብህ ከአንተ ጋር ነኝ" ብለህ አጋር ትሆናለህ? ወይስ ብቻቸውን ሲለፉ ትመለከታለህ?
▫ መከበብኽን እያወቅኽ እረፍት በበዛበት በ"ሮማን ዛፍ" ሥር ተቀምጠሃል? እንደ ሳኦል መከራውን እየቆጠርክና እየፈራህ ተቀምጠሃል? ወይስ እንደ ዮናታን "እስኪ እንለፍ እግዚአብሔር ያግዘናል" ብለህ ወደ ድል እርምጃ ትራመዳለህ?
በአጠቃላይ የዮናታንና ጋሻ ጃግሬው ድንቅ ጀብዱ የሚያስተምረን፣ እግዚአብሔር ድልን የሚሰጠው የቁጥር ብዛት ላላቸው ሳይሆን የልብ ጽናት ላላቸው በእሱም ለሚታመኑት ብቻ መሆኑን ነው። ቆራጥ እምነት ይስጠን፤ ቸር ይግጠመን!
0 Comments