ትውልዱ የተነፈገውን አባት መላሽ!

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ትውልዱ እውነትን የሚያወራለት ሳይኾን ጽድቁን ፈጽሞበት ጸንቶ የሚቆመውን መልክ-አባቱን ይሻል፣ ይጣራልም! አልጫነትን ተጠይፎ ተፈጥሮውን በልቡ በወሬ ሳይኾን በተግባር የሚስልለትን!

በየሚዲያውና በየመድረኩ የሚቀርቡ፦

🚨 ልስልስ፣

🚨 ቅልስልስና

🚨 ኩንስንስ ወንዶች ነባሩን፣ ታሪካዊውን፣ ባህላዊውን፣ ሀገር አቅኚውን፣ ቤተሰብና ድንበር ጠባቂውን፣ ትውልድ አናጺውን፦ ቆራጡን፣ ቆፍጣናውን፣ ደፋሩን፣ በሚስቱና በልጆቹ የማይደራደረውን ኢትዮጵያዊ አባት ለመተካት ኾን ተብለው “በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት” ስም ተሳበው ለትውልዱ የሚቀርቡ ማታላያ፣ ማቅረቢያና ማጥመጃ “የመንጠቆ ላይ ስጋና ወጥመዶች” ናቸው።

ከትውልዱ ብዙኃኑ ደግሞ ቀድሞ በራሳቸው በልሂቃኑና በሊቃውንቱ “አስመሳይ፣ አታላይ፣ አድርባይ ስብከት” ልቡ ቀልጧልና፤ የነገሩትን፣ የጠየቁትን፣ ያዘዙትን እየተቀበለ ሳይመረምር ዋጥ ስልቅጥ ያደርጋል። በዚያም ዘወትር ከሚያለቅስበት ባርነትና ሞቱ አይወጣም፤ እንደውም ይጸናበታል እንጂ!

እነርሱ “አዋቂ፣ ታዋቂ፣ ነገር አርቃቂ፣ ተመራቂ፣ በመድረክ ደማቂ አድማቂም...” ናቸውና ለዝናም ለገንዘብም ይመረጣሉ፤ ነባሩን ኢትዮጵያዊ አባትነት፣ ጽድቁን ይፈጽም ዘንድ የጨከነውን ወንድነት የሚሰማው የለም!

ስለኾነም ከትውልዱ በተለይ ወንዱ በተፈጥሮ ስጦታ፣ በባህል ቅብብሎሽ (በትውፊት) የመጣውን አባታዊ (አባወራዊ፣ ተፈጥሮአዊ) ወንድነት የሚያሳየው አባት፣ ወንድም፣ ጎበዝ፣ ማኅበረሰብ፣ ባህል በማጣቱ ለማንነት ቀውስ ተላልፎ የሚጠፋና የሚያጠፋ ኾኗል።

ዛሬ ወንዶቻችን አባታቸው በቤት እንኳ ቢኾን አባትነት ምን መምሰል እንዳለበት ያላወቀ፣ ወንድነታቸው እንዴት መብሰል እንዳለበት ያልጠነቀቀ ይኾንና ተፈጥሮአዊ ለኾነ ጥያቄና ስጋታቸው መልስ በራሳቸው መንገድ እንዲፈልጉት ይተዋሉ።

በዚህ አጋጣሚ ታዲያ “ከእኛ ወዲያ አዋቂ ጠማቂ ከወዴት” ላሉ ባፍጡም ተደፍተው ትውልዱ አባቶቹን የማይመስልበትን፣ በትውፊት ያልመጣለትን የባዕዳን “ተረት” ከሚግቱት ሆዳደርና አልጫ ልሂቃን ስር ይወድቃል።

አንድም የማይኖሩትን ወንድነት ወይም የሚኖሩትን አልጫነት “ወንድነት” ብለው ለሚሸጡ “ሱቃቸውን” የመገናኛ ብዙኃን እና የማትገጽ ላይ ለከፈቱ ነጋዴዎች ተላልፎ ይሰጣል።

ይህም ቢኾን ከበዛው የታይታና የይኹንታ ሩጫና ጫጫታ ውስጥ ከልጆቻችን ድምጽ መካከል አሁንም የአርአያ፣ የምሳሌ፣ የአብነት ጉድለት የአባትም መሻት ይሰማል።

ይህ ከጠንካራ የመሻት ፍላጎት የመነጨ ድምጽ አብሮ የሚበላ፣ ልብስ የሚገዛ ወይም ፊርማ የሚፈርም ሰው ፍለጋ አይደለም፤ ወንድነቱን የሚስልለት፣ በውስጡ የሚፈላውን ወኔ የሚቀድስለትና በእርሱም እንዴት ጽድቁን እንደሚፈጽምበት፣ በዚያም የሰጠውን አባቱን እንደሚባርክበት የሚያሳየው አባት ፍለጋ እንጂ!

አባት ሳይኖረው ቀርቶ፣ “አባት” የሚባሉትን ሳያውቅ ቀርቶም ብቻ አይደለም። ነገር ግን የሚያውቀው አባቱ በሚነግረው እውነት ጎን ቆሞ ጽድቁን በመፈጸም ጽዋ መከራውን ለመጨለጥ የሚፈራ ከኾነ፤

አባቱ ለባዕድ አጀንዳ እውነትን ለጥቅሙ ሽጦ ለውጦ በዚያም እነርሱን አንቀባሮ ያኖረ “አድርባይ” ከኾነ፤

አንድም አባቱ በእውነት ከሚመራው ቤቱ ተከሶ፣ ተወቅሶ፣ ተኮንኖም በሥነ-ልቦናም ኾነ በአካል ከልጆቹ እንዲርቅ ተደርጎ ከኾነ፤

ትውልዱ ከማንነት ቀውሱ የተነሳ፣ ወንድ መኾንን ባለማወቁ የተነሳ፣ “አባ የት ነህ?” ብሎ መጮኹ አይገርምም። ልጁ አባቱን ያጣው በሞት ሳይሆን፣ አባቱ የገዛ ማንነቱን በመጣሉ ነው።

አባት የሌለው ትውልድ፣ ወንድነቱን የሚያጸድቅለት ታላቅ ያጣ ትውልድ፣ ለተኩላዎች የተጋለጠ ነው። ልጆቻችን በውስጣቸው ያለውን ጥንካሬና ጀብደኝነት የሚያፈሱበት የጽድቅ መስክ ሲያጡ፤ ወደ ሱስ፣ ጋጠወጥነት፣ መረንነት፣ ብቸኝነትና ራስን ማጥፋት ይሸሻሉ።

ሊቃውንቱ በጥቅም ተለውጠው ለተኩላ ሲጥሏቸው፣ “ለምን እንዲህ ኾንክ?” እያለ የሚወቅሳቸው፣ የሚከሳቸውና የሚኮንናቸው እንጂ “እንዲህ ኹን” ብሎ ቀናውን መንገድ የሚያሳያቸው ጠፍቷል።

ቤተ-ክርስቲያንም ወንዶቿን “አልጫ” በማድረግ ሂደት ውስጥ የራሷን ድርሻ ተወጥታለች። ወንድ ልጅ መንፈሳዊ ለመኾን ወኔውን መግደል፣ “ጃንደርባ” መኾን፣ ወንድ ልጅ ከሚገለጥበት ጠባይ ይልቅ ልስልስ፣ ቅልስልስና ኩንስንስ እንዲኾን ከመድረክ ይልቅ በተለይ በይበልጥም በሕይወት(በኑሮ) ተሰብኳል።

ወንድነት ተፈጥሮውን የሚቀድስለት፣ የሚያጸድቅለት፣ ጽድቁንም ይፈጽምበት ዘንድ ፈጽሞ የሚገለጥበትን፦ ወንድም አባት፣ አርአያ ትውልዱ ይፈልጋል!

አስመሳይነት፣ አድርባይነት ትውልዳችንን ከተፈጥሮው አርቆ፣ ከማንነቱ አውጥቶ ከጠላት ሜዳ፣ ከበላቾቹ ሆዳደሮች ካራ ስር ጥሎታል!

አሁንም አባቶቻቸውን የሚፈልጉ፣ መልካቸውን ይስሉላቸው ዘንድ የሚሹ፣ አርአያ አብነት ይኾናቸው ዘንድ የሚቃትቱ የልጆቻችን ድምጽ ይሰማል!

አባወራዎቹም ይመጣሉ! ትውልዱን ከአስመሳይ አድርባዩ “አዋቂ” ይናጠቃሉ! ወንዶቻቸውን ወደ ልባቸው አባቶቻቸውንም ወደ ክብራቸው ይመልሳሉ።




Post a Comment

0 Comments