ምስኪን "የበይ ተመልካች" (passive) ነው! እርሱኑ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም አጽድቆ የተቀመጠ፣ አጽድቆ መቀመጡንም ከ"እውቀት" ቆጥሮ በእብሪት የተወዘተ!
ሊሠራ ያለውን ትቶ “ምንም ማድረግ አልችልምን” መርጦ ለተወዘተው፤ ወንድነት የጠፋበት ብቻ ሳይኾን አጥፊውም እንጂ እርሱ ነው!
በተለይ አሁን ላይ በዘመቻ ጦርነት የተከፈተበት፦ የሀገር መገንቢያ ጡቡ፤ ቤተሰብ እየፈራረሰ፤ እርሱን የሚመራው፣ ትውልዱን ቅጥና ሥርዓት የሚያስተምረው አባወራ እየተኮነነ፣ ትውልድ እየጠፋ፣ ማኅበረሰብ እየመከነ፣ ለዘመናት የተገነባንበት “ምሰሶና ማገር፣ ጣርያና ድምድማት” እሴታችን እየተነቃቀለ ዕያየ፤
“ምንም ማድረግ አይቻልም! ክፉ ሃሳብ ‘ክፉ’ ነውና በራሱ ጊዜ ጠፊ ነው፤ ያን ግዜ ሲጠፋ እናርፋለን፣ እስኪጠፋም እንጠብቃለን” የሚለው እርሱ ወንድነትን የማያውቀው፣ ያላየው፣ ያልኖረበት ከዚያም የተነሳ በተሳሳተ ሃሳብ ትውልድ ይሳሳት ዘንድ የሚመክር ነው።
ሌሎች እንደፈለጋቸው ዓለም(ዐለሙን) ሲዘውሩ እርሱ “የበይ ተመልካች”(passive) ኾኖ ባርነት ክፍሉን፣ ካገኘ በልቶ ካጣ ተደፍቶ ማደሩን፣ ሙስና መቃብሩን አቆለጳጵሶ የሚዘግብ፤
እርሱ ሊኖር እንዳለው፣ እንደተሰጠው፣ እንደታዘዘው፣ እንደተጠራለት፣ እንደተለየለትም ለመኖር ያልሠለጠነ፣ ያላደገ፣ ያልበለጸገ፣ ያላየለበትም ነውና፤ ሊመራበት፣ ሊገዛበት፣ ሊያሰማራበት፣ አርአያም ሊኾንበት የተሰጠውን ወንድነት መክሊቱን ቀብሮ፤ ከሌሎች ምሪትና ስምሪት የሚጠብቅ ነው።
ይህ ሰው እንዲህ የበይ ተመልካች (passive) ኾኖ ቢኖር ይህ ዓመሉ በዚያው በሚኖርበት፣ በቤተሰቡ፣ በልጆቹ ላይ፣ በሚታወቅበትም አካባቢ ባሉት ተከታዮቹ ዘንድ ብቻ ይወሰን ነበር።
ነገር ግን በመገናኛ ብዙኃን ወጥቶ፣ “ከተከታይ፣ ተመልካች” ጠባዩ የተነሳ “ለሁሉም የሚስማማና ደስ የሚል” አስተያየቱን በለስላሳና በቀስታ በሚንቆረቆረው አነጋገሩ ሰድሮ ሲናገር፤ ከዚህ የሚከፋው ደግሞ በዚሁ ጠባዩ ስለ ወንድነትን ሲያብራራ እንዲያብራራም ሲጋበዝ ጉዳቱ የከፋ ይኾናል።
በተለይ ይህ ዓይነቱ የተሳሳተ አካሄድ “ሃይማኖተኛ ነን፣ መንፈሳዊ ነን” በሚሉ ወንዶች ዘንድ ያይላል። ስለኾነም ጠላት እነርሱን መሣሪያ አድርጎ ሲሠለጥን ትውልዱ በሀገሩ፣ በመንደሩ፣ በባህሉ ባባቱ ቤት፣ በርስቱም “የበይ ተመልካች” ይኾን ዘንድ “ፍዝ፣ ድንዙዝ” ይኾናል!
🚨 ምስኪንነት ይጸድቃል!
🚨 አልጫነትም ይቆለጳጰሳል!
🚨 “የበይ ተመልካችነትም” (passiveness) በዘመናዊነት ይበልጡንም በመንፈሳዊነት ሰበብ ትውልዱን ለባርነት ወደ ግዞት የሚጠራ የጠላትና የሆዳደሮች “ተወዳጅ ፉጨታቸው” ይኾናል!
ታናሼ! በአባወራ ገጽ ውስጥ እኔ ከወላጅ አባቴም ኾነ ከሌሎች በታሪክ ከማውቃቸው አባቶቼ፣ ከሰማዩ አባታችንም ቢኾን ዐይቼ፣ አንብቤ፣ በተግባር ተምሬ፣ በፈተና ኖሬውም እስከዛሬ ያካፈልኩህ፦
🚨 በምትሠራ፣ በምትዘወር፣ በምትሽከረከር ዓለም ውስጥ “የበይ ተመልካች” መኾንን አይደለም!
በፍጹም! በጭራሽም!
💪 ይልቁንስ ለትውልድ ያሰብነውን ጽድቁን፣ ቤተሰባችን የሚጠቀምበትን፣ ልጆቻችን የሚያይሉበትን አስፈላጊውን፣ ዓለም(ሀገር) የምትጣፍጥበትን ጨዉን በፍጹም ጥብዓት(ጭካኔ) ተነስተን እንድንፈጽመው እንጂ!
በጭራሽ ግን በሌሎች የሚኾንብንን “ምንም ማድረግ አንችልም! እርሱ እንዳመጣ እርሱ ይውሰድልን፣ አልያም በራሱ ይክሰምልን እንጂ” ብለን ያቅመቢሶችን፣ ግፋ ሲልም ያልጮችን ሰበብ በዜማ እንድናላዝን እንድንነፋረቅም አይደለም!
ከወንድ በተለይም ለትውልዱ ይበልጡንም ለወንዱ “መሪ፣ አስተማሪ፣ መካሪም ይኾናል” ተብሎ በአደባባይ ተጋብዞ ከሚናገረው ይህ በፍጹም አይጠበቅም!
ይህ ሰው ታይታና ይኹንታ ካልፈለገ በስተቀር በሠለጠነ መንገድ “አይ! ይህ ነገር ከእኔ ይለፍ! ስለ እርሱ አላውቅም!” ቢል ለሰዓታት ከተናገረው አሳሳች መልዕክት ይልቅ ትውልዱን ከክፉ ይጠብቃል!
እንዲህ ከሚሉት ጋር አንተም ብትስማማ ንግግራቸው የተስማማህ ከውስጥህ ካለ፣ ካላጠፋኸውም፣ ባርነትክን እውን ሊያደርግ ካደፈጠው፣ ጽድቅን መፈጸም ከተሳነው፦ ምስኪንነት ከአልጫነቱም ቢሉ፤ ተናቦ ተገናዝቦልህ እንጂ “ልከኛ ተፈጥሮ” ስለኾነ አይደለም!
🚨 አይደለም!
አባቶቻችንም ኾነ አባታችን ይህንን አላስተማሩንም! ኖረውም አላሳዩንም! ስለ ጽድቅ፣ ስለ እውነት ተገዳዳሪው፣ ባላጋራውን ተጋፍጦ መከራን መጨለጥን እንጂ!
ሃይማኖትና ታሪክን “አውቃለሁ” አልያም “ያውቃል” ከሚባል ሰውም እንዲህ ዓይነት አስተያየት ሲወጣ፣ ያውም በአደባባይ እጅግ በጣም አደገኛ ነው ትውልድንም ገዳይ!
ለምን?
ምክንያቱም ወንድ ልጅ የአባቱን ርስት እንዲያበጅ፣ እንዲያበጃጅ እንጂ ሌሎች እንደፈለጉ ሲፈነጩበት፣ ሲያጠፉትም “ምንም ማድረግ አልችልም” ብሎ የበይ ተመልካች (passive) እንዲኾን አልተጠራምና!
ይህ ለሴቶቻችንም ቢኾን ዕዳና ሸክም ነው! ምን በወጣቸውና!
“የበይ ተመልካች” (passive) አትኹን! በጭራሽ!
ሠሪ፣ ፈጣሪ፣ ቀራጺ፣ አናጺ፣ መሪ ያውም እንዳባትህ እንጂ “የበይ ተመልካች” ምስኪን (passive) ልትኾን ያልመጣህ አንተ፤ እንደዚያ የኖሩትን አባቶችህን አንብባቸው፣ ኑራቸው፣ ተገለጥባቸው፤ እርሱ መምከር ማስተማሩን ይቀድማልና!
0 Comments