"ያልተዘመረለት ባለድል፦ የአንዲት ከተማ ምስጢራዊ ታዳጊ"

ክፍል፫ በሰው ለመጽደቅ አትድከም!

✍ ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ

​እስቲ ለአፍታ በሕሊናችሁ ቁጭ በሉና አንድ ታሪክ ላውጋችሁ። ታሪኩ ስለ አንድ ትልቅ ከተማና ስለ አንድ "ትንሽ ሰው" ነው።

​ከተማዋ ታላቅ ነበረች፤ ቅጥሮቿ ሰማይ የሚነኩ፣ በሮችዋም በወርቅ የተለበጡ ነበሩ። ነገር ግን አንድ ቀን ሞት በደጃፏ ቆመ። አንድ ኃያል ንጉሥ ሰራዊቱን እንደ አንበጣ አስከትሎ መጣና ከተማዋን ከበባት። ታላላቆቹ መኳንንት ተንቀጠቀጡ፤ የከተማዋ ጠቢባን መላ አጡ። ሞት በቅጥሩ ላይ ሆኖ ጥርሱን ያገጥጥ ነበር።

​በዚያች መጨረሻ ሰዓት ግን፣ ማንም ፊቱን ዞር ብሎ በማያየው መንደር ውስጥ፣ በአንድ አቧራማ ጎጆ ውስጥ አንድ ምስኪን ሰው ነበረ። እርሱ ታዋቂ አልነበረም፣ ኪሱም ባዶ ነበር። ነገር ግን በልቡ ውስጥ ዓለም የማታውቀው፣ የሰማይ ጌታ የቸረው ታላቅ "ጥበብ" ነበረች።

​ይህ ሰው ወደ አደባባይ ወጣ። መኳንንቱ ሲያዩት "ይህ ምስኪን ምን ሊያደርግ ይችላል?" ብለው ናቁት። እርሱ ግን ዝም ብሎ በጥበቡ የከተማዋን መከራ ፈታው። እንደ መብረቅ በወጣች ቃሉ የጠላትን ሰራዊት በተነው። ከተማዋ ዳነች! ከሞት አፋፍ ተመለሰች።

​ነገር ግን ታሪኩ እዚህ ላይ ነው የሚከፋው... 
ከዛስ ምን ሆነ!??...

​ከተማዋ በነገታው በደስታ ስትጨፍር ያ ምስኪን ሰው ግን አልነበረም። ስሙን ማንም አልጠራውም፤ "አዳኛችን ማን ነው?" ሲባል "እርሱማ ደሃ ነው" ተብሎ ታሪኩ ተቀበረ። ዓለም የዳነችበትን ጥበብ ወደደችው፤ ጥበበኛውን ግን በድህነቱ ምክንያት ጠላችው። ስሙም ተረሳ።

እዚህ ላይ እህቴ ፤ ​ወንድሜ ሆይ፤ አዳምጠኝ...

​ዛሬም በነፍስህ አደባባይ እንዲህ ትል ይሆን? "መልካም ሰርቼ ካልተመሰገንኩ፣ ጽድቄን ሰው ካላወቀልኝ ምን ዋጋ አለው?" ይህንን የመሰለ ቃል በአንደበትህ፡ የዚህስ መሳይ ሀሳብ በሕሊናህ ትላለህን? እንግዲያውስ አንተ ገና ለሰዎች ጭብጨባ የምትኖር ሕፃን ነህ።

​ያ ምስኪን ሰው እኮ "ስሜ ለምን አልተነሳም?" ብሎ አላዘነም። ለምን መሰለህ? እርሱ የሠራው ከተማዋ እንድትድን እንጂ የእርሱ ሐውልት እንዲቆም አልነበረምና። እውነተኛ ጽድቅ ለሰው ታይታ የሚደረግ አይደለም። የሰዎች ምስጋና እንደ ጢስ ተኖ ይጠፋል፤ በእግዚአብሔር ፊት የታተመ ጽድቅ ግን የዘላለም አክሊል ሆኖ ይጠብቅሃል።

​ያ ምስኪን ጠቢብ ከተማዋን አድኖ ስሙ እንደተረሳ ሁሉ፣ የዚህ የጠቢቡ ሰለሞን ምሳሌነት ትንቢታዊ ጥቆማ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደነበረ አስተውል። የናዝሬቱ ኢየሱስም ወደዚች ዓለም የመጣው በድህነት ተጎናጽፎ ነበር።

ምስጢሩ፦ ዓለም የጠበቀችው በወርቅ ዙፋን ላይ የተቀመጠ፣ ሰይፍ የመዘዘ ንጉሥ ነበር። እርሱ ግን "የሚተኛበት ስፍራ የሌለው" ደሃ ሆኖ መጣ። ያች የተከበበች ከተማ የሰው ልጅ ነፍስ ናት፤ ያ የከበባት ንጉሥ ደግሞ ሞትና ዲያብሎስ ናቸው። ክርስቶስ ግን በድህነቱ ውስጥ በነበረችው "መለኮታዊ ጥበብ" ዓለምን ከሲኦል ከበባ የታደጋት እርሱ ነው።

​ዛሬ አንተም "ማንም አላየልኝም" ብለህ የምታማርር የምትምሰለሰል ከሆነ፣ ጽድቅህን ለሽያጭ እያቀረብክ እንደሆነ እወቅ። ሰይጣን "ለምን ስምህ አልተጠራም?" ብሎ ሲያንሾካሹክልህ፣ ጽድቅህን በትዕቢት ሊሰርቅህ እንደመጣ ተረዳ።

"ጽድቄን ሰው ካላወቀልኝ ለምን?" ብለህ ለምትጠይቅ ነፍስ መልሱ እዚህ አለ። ክርስቶስ ጽድቁንና አምላክነቱን በሰው ጭብጨባ ላይ አልመሠረተም። እርሱ "ለአባቱ" ፈቃድ ብቻ ኖረ። አንተም እንደዚያው ሁን! ጽድቅህ እንዲታወቅልህ ስትመኝ፣ ከክርስቶስ መንገድ ወጥተህ ወደ ጨለማ መንገድ እየገባህ ነው።

​ያ ያልተዘመረለት ባለድል መክብብ የተናገረለት ዛሬም በሰማይ ዙፋን ፊት ስሙ በክብር ይጠራል።

ጥያቄ፦

▫ አንተስ? ስምህ በምድር መዝገብ ላይ ብቻ ተጽፎ እንዲቀር ትፈልጋለህ? ወይስ እንደዚያ ምስኪን ጠቢብ በምድር ተረስቶ በሰማይ መታወቅን ትመርጣለህ?

▫ ​ድሉ የማን ነው? የዳነችው ከተማ ወይስ የተረሳው ጠቢብ? በቀጣይ ክፍል እስከምንገናኝ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለነፍስህ ተወው።

መጽሐፈ መክብብ ፱ ፥ ፲፫ - ፲፮ 

​"ደግሞ ከፀሐይ በታች ይህችን ጥበብ አየሁ፥ ለእኔም ታላቅ መስላ ታየችኝ። አንዲት ታናሽ ከተማ ነበረች፥ በእርስዋም ውስጥ ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ ታላቅ ንጉሥም መጣባት፥ ከበባትም፥ ታላቅ ምሽግም ሠራባት። በዚያችም ከተማ አንድ ምስኪን ጠቢብ ሰው ተገኘ፥ ከተማዋንም በጥበቡ አዳነ፤ ነገር ግን ያ ምስኪን ሰው ድሃ ስለ ነበረ ማንም አላሰበውም። እኔም፦ 'ጥበብ ከኃይል ትበልጣለች' አልሁ፤ ነገር ግን የድሃ ጥበብ ትናቃለች፥ ቃሉም አይሰማም።"

Post a Comment

0 Comments