ታላቁ ናዝራዊ በንስሐ ጩኸት ሺዎችን ደመሰሰ!


(ክፍል ፯ ጠያቂ ትምህርት)

✍ ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ

​በጥንት ዘመን፣ የእስራኤል ተራሮችና ሸለቆዎች የአረማመዱን ኮቴ ሲሰሙ ይንቀጠቀጡ ነበር። እርሱ ሲራመድ ነፋሱ ራሱ መንገዱን የሚለቅለት ይመስላል። አንድ ሺህ የፍልስጤም ጦረኞችን በአህያ መንጋጋ አጥንት ብቻ የፈጀ፣ የአንበሳን መንጋጋ እንደ ፍየል ግልገል በባዶ እጁ የሰነጠቀ፣ የጋዛን የከተማ በሮች ከነመቃኑ ነቅሎ በተራራ ጫፍ ላይ የተከለ አስፈሪ አውሎ ነፋስ... እርሱን ታውቃታላችሁ? ሶምሶን ይባላል።

​ሶምሶን ተራ ሰው አልነበረም፤ ገና በእናቱ ማኅፀን ሳለ ለእግዚአብሔር የተለየ "ናዝራዊ" (የተቀደሰ) ነበር። ኃይሉ በግዙፍ ጡንቻዎቹ ውስጥ ሳይሆን፣ በራሱ ላይ በተንዘረፈፈው ጸጉሩ ውስጥ የተደበቀ ረቂቅ ምስጢር ነበረ። ጸጉሩ የሥጋ አካል ብቻ ሳይሆን፣ ከሰማያዊው አምላክ ጋር የተሳሰረበት የማይታይ የኪዳን ገመድ ነበር።

​የፍልስጤም ሰይፎች፣ ጦሮችና ሠረገላዎች ሊጥሉት ያልቻሉትን ይህን ግዙፍ ዋርካ፣ ከጦር ሜዳ ርቆ በሚገኝ አንድ ጸጥታ የሰፈነበት ክፍል ውስጥ፣ የሐር ትራስ ላይ ወደቀ። በደሊላ ጭን ላይ።

​ደሊላ... የውበቷ ማራኪነት እንደ ጥልቅ ማዕበል የሚስብ፣ ግን ደግሞ የሞት መርዝ ያዘለች እንቆቅልሽ ነበረች። የሺህ ጦረኞች ጩኸት ያላስፈራውን ልብ፣ የደሊላ ለስላሳ ድምፅና የማባበል እንባ አቀለጠው። "እስኪ ንገረኝ... ታላቁ ኃይልህ ያለው የት ነው?" እያለች ምስጢሩን ስትፈትሽ፣ ሶምሶን በእውነተኛ ፍቅርና በአታላይ ፈተና መካከል ይዋልል ነበር። ብዙ ሸወዳት ሊያታልላትም ሞክሮ ነበር። በመጨረሻም፣ ያ ደረቱን ለጦር ያላስደፈረ ጀግና፣ ልቡን ለሐሰተኛ ፍቅር አስደፈረ። "ጸጉሬ ከተላጨ ኃይሌ ይወጣል" ብሎ የኪዳኑን ምስጢር አሳልፎ ሰጠ።

​በዚያች ሌሊት፣ ሶምሶን በደሊላ ጭን ላይ ጥልቅ እንቅልፍ ወሰደው። ጸጉሩ ሲቆረጥ የተቆረጠው ጸጉሩ አልነበረም፤ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጸጋ ኪዳን እንጂ። ከእንቅልፉ ሲነቃ "እንደ ቀድሞው እወጣለሁ" ከጠላቶቼም አመልጣለሁ ብሎ አስቦ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደራቀ አላወቀም ነበር። አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ! የብርሃን ዓይኖቹ ተፈነቀሉ፣ በእግር ብረቶች ታሰረ፣ በጨለማ ወኅኒ ቤት ውስጥ እንደ ከብት እህል መፍጨት ጀመረ። ታላቁ አርበኛ የጠላቶቹ መሳለቂያ ሆነ።
​ግን ታሪኩ እዚህ ላይ አያበቃም። በጨለማው እስር ቤት ውስጥ፣ ዓይኖቹ ባያዩም፣ የነፍሱ ዓይኖች ግን በንስሐ መከፈት ጀመሩ። የተላጨው ጸጉሩም ቀስ በቀስ ማደግ ጀመረ—ይህም የተቆረጠው የእግዚአብሔር ጸጋ በንስሐ ሲመለስ የሚያሳይ ጥልቅ የቤተ ክርስቲያን ምስጢር ነው።

​ፍልስጤማውያን ጣዖታቸውን (ዳጎንን) ለማመስገን በተሰበሰቡበት ታላቅ አዳራሽ፣ ሶምሶንን ሊሳለቁበት አመጡት። በሁለቱ መካከለኛ ምሰሶዎች መካከል ቆመ። በዚያች ቅጽበት፣ የዓይኑን ብርሃን የነጠቁትን ጠላቶች አላየም፤ ነገር ግን ወደ ሰማይ አሻቅቦ የልቡን ጩኸት አሰማ፦ "አቤቱ አምላክ ሆይ፣ እባክህ አስበኝ፤ አቤቱ፣ እባክህ፣ በዚህች ጊዜ ብቻ አበርታኝ!" ቀጥለና ሶምሶን ሁለቱን ምሰሶዎች በኃይል ገፋቸው። ታላቁ ቤተ ጣዖት በላያቸው ላይ ተደረመሰ። በሕይወት ዘመኑ ከገደላቸው ይልቅ፣ በሞቱ የገደላቸው ፍልስጤማውያን በዙ። የሶምሶን እጆቹን ዘርግቶ በሁለቱ ምሰሶዎች ላይ መሞትና ጠላቶቹን ማጥፋት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጆቹን በመስቀል ላይ ዘርግቶ፣ በሞቱ ሞትንና ዲያብሎስን ድል የመንሳቱ ጥልቅ ጥላ ወይም ቅድመ ትንበያ ነበር።

​እነሆ ማጠቃለያ የቤት ሥራ... ለእኔም/ለአንተም/ ለአንቺም፦

የሕሊና ማነቂያ (የሕይወት ጥያቄዎች ወደ አንባቢው)፦
​ወዳጄ ሆይ... የሶምሶን ታሪክ የጡንቻና የጉልበት ተረት አይደለም፤ የነፍሳችን የዕለት ተዕለት ውጊያ እንጂ።

​የአንተ "ደሊላ" ማናት/ማነው? በሕይወትህ ውስጥ፣ ጸጋህንና መንፈሳዊ ጉልበትህን ቀስ በቀስ እየቆረጠ፣ በሐሰተኛ ማባበል ጭኑ ላይ ያስተኛህ የኃጢአት ልማድ፣ ሱስ ወይም መጥፎ ጓደኛ ማን ነው?

የኪዳን ጸጉርህ (ምስጢርህ) አለ ወይ? ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ የግል ጸሎትህ፣ ንጽሕናህና ቃል ኪዳንህ ተጠብቆ አለ ወይስ በዓለም መቀስ ተቆርጦ የጠላቶች መሳለቂያ ሆነሃል?

​ነገር ግን ታላቁ ተስፋ ይህ ነው፦ ምንም እንኳን በኃጢአት ምክንያት ብትወድቅም፣ ጸጋህ ቢገፈፍም፣ የንስሐ ጸጉርህ ዳግም ማደግ ይችላል። እግዚአብሔር የንስሐን ጩኸት ይሰማል። ዛሬ በመንፈሳዊ ዕውርነት ወኅኒ ቤት ብትሆንም፣ እንደ ሶምሶን "አቤቱ በዚህች ጊዜ ብቻ አበርታኝ!" ብለህ ከልብህ ከጮህክ፣ የኃጢአትን ቤተ ጣዖት አፍርሰህ ነጻ መውጣት ትችላለህ! ዛሬውኑ የንስሐ ጸጉርህን ማሳደግ ጀምር!

Post a Comment

0 Comments