ይህ ጽሑፍ የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት ለመግለጽ ቢሞክርም፣ በውስጡ የያዛቸው ቃላትና ትርጓሜዎች ግን ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ የወጡ ናቸው

ዮሐንስ አብነት ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምንነት ምስጢር በሚል ርዕስ ላቀረበው ፅሑፋ የተሰጠ ምላሽ፦

✍ የሮንሳ ጋሄ | ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን

ይህ ጽሑፍ የቤተ ክርስቲያንን ታላቅነት ለመግለጽ ቢሞክርም፣ በውስጡ የያዛቸው ቃላትና ትርጓሜዎች ግን ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ የወጡና ወደ "ኒው ኤጅ" (New Age) ፍልስፍና ያዘነበሉ ናቸው። ዋና ዋና ስህተቶቹን ከነማስረጃቸው እንደሚከተለው መመልከት ይቻላል፦

​፩. የ"ንዝረት" (Frequency) እና የ"ኮድ" ስህተት
​የጽሑፉ ስህተት፦ ኦርቶዶክስን "የንዝረት ማዕከል"፣ ተዋሕዶን "ቅዱስ ንዝረት"፣ ግዕዝን "መለኮታዊ ሶፍትዌር" ይለዋል።

​የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እውነት፦ ቤተ ክርስቲያን መለኮታዊ ኃይልን በቁሳዊ ንዝረት ወይም በዲጂታል ቋንቋ አትለካም። የምታስተምረው ስለ "ጸጋ" እና ስለ "መለኮታዊ ቃል" ነው።

​ምክንያት፦ ንዝረት የቁስ (Matter) ባሕርይ ነው። ጸጋ ግን ከመለኮት የሚገኝ ረቂቅ ስጦታ እንጂ በሳይንሳዊ ሞገድ የሚለካ አይደለም። ይህ አገላለጽ አምላክን እንደ "ኤሌክትሪክ ኃይል" አድርጎ የመቁጠር ስህተት አለበት።

​ማስረጃ፦ "የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለም" (፩ ቆሮ ፬፥፳)። ይህ ኃይል ደግሞ መንፈሳዊ እንጂ ሞገዳዊ አይደለም።

​ማጣቀሻ፦ መጽሐፈ አክሲማሮስ (ስለ ረቂቅ ፍጥረታትና ስለ መለኮት ባሕርይ)።

​፪. የሰባቱ ምስጢራት እና የ"ኃይል ማዕከላት" (Chakras) ስህተት

​የጽሑፉ ስህተት፦ "7ቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን በሰውነት ውስጥ ያሉትን 7 የኃይል ማዕከላት (Chakras) ይከፍታሉ" ይላል።

​የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እውነት፦ ሰባቱ ምስጢራት የተመሠረቱት ለነፍስ ድኅነትና ለጸጋ በረከት እንጂ "ቻክራ" የተባሉ የኃይል ማዕከላትን ለመክፈት አይደለም።

​ምክንያት፦ "ቻክራ" የሂንዱይዝም ፍልስፍና ውጤት ሲሆን፣ ሰውን እንደ "ኤነርጂ ጣቢያ" ይመለከታል። ቤተ ክርስቲያን ግን ሰውን የእግዚአብሔር አምሳል፣ የቅዱስ መንፈስ ማደሪያ (ቤተ መቅደስ) አድርጋ ታስተምራለች።

​ማስረጃ፦ "ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?" (፩ ቆሮ ፮፥፲፱)።

​ማጣቀሻ፦ ሃይማኖተ አበው እና መጽሐፈ ምስጢር።

​፫. የ"ዲሜንሽን" (Dimension) እና የስውራን ስህተት
​የጽሑፉ ስህተት፦ "ስውራን ቅዱሳን በ 5ኛው ዲሜንሽንና ከዚያ በላይ ሆነው ዓለምን ይዘውራሉ" ይላል።
​የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እውነት፦ ቅዱሳን የሚኖሩበትና የሚገለጡበት ዓለም ረቂቅ (ሰማያዊ) እንጂ በቁጥር የሚሰላ "ዲሜንሽን" አይደለም።

​ምክንያት፦ ዲሜንሽን የቦታና የጊዜ (Space-time) ስሌት ነው። መንፈሳዊው ዓለም ግን ከጊዜና ከቦታ በላይ የሆነ መለኮታዊ ግዛት ነው።

​ማስረጃ፦ ቅዱስ ጳውሎስ "እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ" (፪ ቆሮ ፲፪፥፪) ይላል እንጂ እስከ አምስተኛው ዲሜንሽን አይልም።
​ማጣቀሻ፦ ራእየ ዮሐንስ።

​፬. የቅዱስ ቍርባን እና የ"DNA" ስህተት
​የጽሑፉ ስህተት፦ "ቅዱስ ቍርባን መለኮታዊ ዳታን ወደ DNA በማስገባት የሞት ኮድን ያጠፋል" ይላል።
​የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እውነት፦ ቍርባን የክርስቶስ እውነተኛ ሥጋና ደም እንጂ "ዳታ" አይደለም። የሚሰጠውም ለኃጢአት ሥርየትና ለዘላለም ሕይወት ነው።

​ምክንያት፦ ይህ አገላለጽ ቍርባንን እንደ "ባዮሎጂካዊ መድኃኒት" በማቅረብ መለኮታዊ ምስጢርነቱን ያቃልላል።

​ማስረጃ፦ "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው" (ዮሐ ፮፥፶፬)።
​ማጣቀሻ፦ ሥርዓተ ቅዳሴ።

Post a Comment

0 Comments