እጅን አጣጥፎ ጽድቅ፤ አፍን ለጉሞ ጥበብ!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል

ጎበዛዝት ቸልተኝነታቸውን ትዕግሥት፣ ዝምታቸውንም ብልህነት ብለው ራሳቸውን ሲያሳምኑ፤ ተስፋ ያደረጋቸው ትውልድ ይጠፋል!

የአባወራው አቋም የሚለካው በታይታና ይኹንታ ሳይሆን፣ በመከራ ቀን በሚያሳየው ቆራጥነትና ልበሙሉነቱ ነው።

ዛሬ ማህበረሰባችንን ከማኅበረሰባችንም በተለይ ወንዱን በክፉ ተውሳክ ተጠቅቷል። የብርቱዎቹ፣ የወንዶቹ፣ የጎበዛዝቱ መዛል፦ ከጠጣር እውነት ይልቅ ለታይታ እየቀለጡ መጥፋት እና የምስኪኖች ወይም የአልጮች ስር የሰደደ “ትዕግሥት” የተወሳኩ መገለጫዎች ናቸው።

ወንድምዓለም! ራስህን ጠይቅ ወደ ውስጥም ተመልከት

👉 “ትዕግሥተኛ ነኝ” ትላለህን?

👉 እውነትስ “ትዕግሥተኛ” ኾነህ ራስክን አግኝተኸዋልን?

👉 ፍርሃትህንስ ለመሰወር አይደለምን?

👉ወይንስ እውነትን መመስከር፣ ከእውነት ጎን መቆም፣ ስለፍትሕ መጮህ ስትፈራ የምትሸልላት ጽድቅ መሳይ ያልጫ ቀርረቶ አይደለችምን?

በእኔ አትበሳጭ! ራስህን ከወደቅክበት ያልጫነት አዘቅት ፈልገህ የምታገኝበትን መርማሪ ጥያቄዎች እያቀበልኩህ እንጂ! እውነቱን ለመመለስ ጨክን!

“ዝምታ ጥበብ ነው” የምትለውም እንዲሁ ኃላፊነትን ለመሸሽ ከኾነስ፡- ሊቃውንቱ ኾን ብለው ትውልዱ ያልተረከበውን፣ ያልመጣበትን፣ ማኅበረሰብ ያልተገነባበትን ነገር ግን የሚጠፋበትን “እሴት” እንደመንፈሳዊነት ሲያስተምሩ፣ ብዙዎችም ተታለው ሲጠፉ፣ እነዚያን ብዙዎች ተከትለው ሌሎችም ለጥፋት ሲሰለፉ፤ ያን ጊዜ፣ ያን ጊዜ “ዝምታ” ላንተ “ወርቅ፣ ጥበብ፣ ብልሃትም” ነውን?

እኔ ደግሞ ልንገርህ አይደለህም!

አንተ እንደምትለው “ትዕግሥተኛም ዝምተኛም” አይደለህም! ልጆችህ ሲያድጉ፣ ታሪክም ሲጻፍ የሚያስታውሱህ፣ ሲያስታውሱህም የሚያፍሩብህ፣ ሲያፍሩብህም የሚደብቁህ፣ ሲደብቁህም ራሳቸውን የማይቀበሉ ከንቱዎች የሚኾኑብህ፡- አልጫ እንጂ ነህ!

በዚህም በእብሪት ታጅረህ በጠፋህበት ለትውልድ ጥፋት፣ ለማኅበረሰብ ምክነት፣ ለሀገርም መፍረስ መዶሻ እያማረጥክ መራጃም እያቀበልክ ነው።

አንድም ትውልድን ያጠፉበት፣ ማኅበረሰብን ያመክኑበት፣ ሀገርንም ያፈርሱበት ዘንድ የሚያገለግላቸውን ሥልጣን ለሚሹት እያቀበልክ ነው፡፡

ብዙ ምስኪኖች ሥልጣን ለሚገባቸውና ለሚያገባቸው የሚሰጥ ይመስላቸዋል። ይኹን እንጂ የሥልጣን ጅረት ካለበት ክምችቱ፦ ጽድቅ ይሠራበት ዘንድ ባባቱ ተሰጥቶት በእብሪት ከተናቀበት ግምጃቤት-ልቡ (ከእንዳንተ ዓይነት “ትዕግሥተኛና ዝምተኛ ነን” ባይ “ጎበዛዝት”) ቀልጠው ወዳራቆቱት ባዶ ቦታ አዘቅቱ ይፈሳል።

ያ አንተ ንቀህ፣ ይበልጡንም በእብሪትህ ተመጻድቀህ በተሰጠህ ወንድነት መክሊትህ፣ በዚያም ባለህ ሥልጣን ጽድቅ ልትሠራበት፣ ልብህን፣ ትውልድን፣ ማኅበረሰብን፣ ቤተክርስትያንን፣ ሀገርን፤ ልትጠብቅ ሲገባ፤

ኦና ያደረግከውን የሥልጣን ጅረት ከረባዳው ካዘቅቱ ፈሶ ሲንፎለፎል ሲያገኘው ጠላት ይናጠቀዋል፣ ይሠለጥንበታል፣ ይሠለጥንብሃል፤ ጽድቅ ይሠራበታል? በጭራሽ በግፍ ይፋንንበታል እንጂ!

ይኹን እንጂ ለዘመናት በዘመናዊነት ይበልጡንም በመንፈሳዊነት ሰበብ ራስህን፣ ተፈጥሮህን፣ ወንድነትህን እስክትጠላ ድረስ የተጋትከውና የተጣባህ አልጫነት እጅግ ጥብቅ ጥልቅም ነውና፤ ለስንፍናህ “እግዚአብሄር የፈቀደው ይኹን” ስትል ያንተን፣ የትውልድንና የሀገርን ባርነ፣ ጥፋት፣ ምክነታቸውንም ታጸናለህ፡፡

አንባገነን መሪዎችና በሥነ-ምግባር የበሰበሱ(የማሰኑ) ተከታዮቻቸውም መንበረ ሥልጣኑን የሚቆጣጠሩት፣ ትውልድን በግፍና በበደል የሚነዱት እነሱ ኃያል ስለሆኑ ሳይሆን፤ አንተ ባልጫነትህ ተመጻድቀህ ዳር ስትቆም ባለቤት አልባ ኾኖ “ሥልጣንን” ስላገኙት እንጂ ነው።

“ሥርዓቱ ይጠብቀናል፣ ተቋማት ይዳኙናል፣ ማኅበራቱ ይጮሁልኛል” እያልክ ራስህንም አትሸንግል።

ተቋም ማለት ስሜትም ስሌትም የሌለው ደረቅ መዋቅር ነው። ሕያውና ፍትሐዊ የሚያደርገው ተዓምር መሥራት የሚችለው የአንተ ወኔ፣ ልበሙሉነትህና የግል ተጠያቂነትህ ብቻ ነው።

እኛ ወንዶች በተለይም አባወራዎች እውነትን፣ ሴቶችን፣ ሕፃናትንና ብሔራዊ(ማኅበራዊ) ክብራችንን መከላከል ስናቆም፤ በምድር ላይ ላሉ ነጣቂ አውሬዎችም(ጠላት) ኾነ ለሆዳደር ምንደኞች(ባንዳ ሊቃውነት) ለዓላማቸው መሳካት መንገዱን እንለቅላቸዋለን፡፡

ከዚያ በኋላ ግን አንተን “አክራሪ፣ አካባጅ፣ አንባገነን፣ በዝባዥ፣ ጨቋኝ፣ በዳይ፣ ደፋሪ፣ አጥቂ...፡-አባወራ” ብለው ጥንካሬህን፣ ጀግንነትህን፣ ቆራጥነትህን፣ ቆፍጣናተህን፣ ኃይለኝነትህን ... የሚፈርጁት፣ በዓለም አደባባይ ጭምር ተፈጥሮህን የሚኮንኑት፤

እነዚሁ የልጆችህን አእምሮ-በሩን የከፈትክላቸው፣ በልጆቻችን ልብ ላይም እንደፈለጉ እንዲፈነጩ በ”ትዕግሥትህና በዝምታህ” የፈቀድክላቸው አድርባይ ቀማኞች “ልሂቃንና ሊቃውንቱ” ናቸው።

መጪው ትውልድ በታሪክ መነጽር አነጣጥሮ ዛሬ አንተ በጓዳህ የምታጉተመትመውን ቅሬታ፣ በመኝታህ የምታብሰለስለውን ጸጸት፣ በልብህ የምታመላልሰውን ቁጭት ወይም “ጥሩ ሐሳብ ነበረኝ” የሚለውን ሰበብህን ዓያይም አያደምጥምም።

(ይህቺን ሐሳቤን ይዤ የምቀርባቸው ሰዎች ገና አፌ ሲከፈት “አንተ ጋር ብቻ አይደለም እኮ እውነት ያለው፣ እኛም ጋር ይህና ያ አለ” ለማለት መቸኮላቸው ይገርመኛል።

ሀሳባቸውን የት አደረሱት እንደ እኔ ጻፉበት፣ አሠለጠኑበት፣ ከታሪክና ከባህል፣ ከጊዜዐውድ ጋርስ አስማምተው ፈትለውና ገምደው ስጋጃ ሰፉበት? ከዚያ ሁሉ ይልቅ ግን በተሰጣቸው ጸጋ ሠልጥነውና በልጽገው ታዩ ተገኑበት፣ ጽድቅ ፈጸሙበት ወይ? የታለ?)

ኧረ ተዉ! አትቀልዱ!

ትውልድ እያጣን ነው!

🚨 ቤተሰብ እየፈረሰ ነው!

🚨 ልጆቻችን እየተበተኑ ነው!

🚨 ጋብቻ ትዳራችን መቧለቻ የቡና ቁርስ እየኾነ ነው!

🚨 ትዳርን ታናናሾቻችን እየፈሩት እየጠሉትም ነው!

🚨 ምን ቢማር “ዶክተርና ኢንጂነር፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት” ቢባልም አልጫና አስመሳይ አድርባይና ሆዳደርም ትውልድ እያፈራን ነው!

🚨 የጠላቶቻችን መሳቂያና መሳለቂያም እየኾንን ነው!

🚨 ማኅበረሰባችን እየመከነ ነው!

🌟 የመገናኛ ብዙኃን (ማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ጨምሮ) ትውልድን ከምንታደግበት ቁምነገር ይልቅ ፌዝና ቧልት አልያም ፋይዳ ቢስ ጉንጭ አልፋ ወሬ ላይ አተኩረው የአድማጭ ተመልካቾቻቸውን ቁጥር ያበዛሉ።

ወንድምዓለም! በታሪክ ተመዝግቦ ትውልድ ይማርበትና ይታነጽበት ዘንድ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፈው(ትውፊት) ትውልዱ ውስጥ ያለው ምንም ዓይነት ጽድቅ ያልሠራው ልቅሶ፣ ሮሮ፣ ብሶት፣ ሐሜት ሳይኾን፦ ከፋም ለማም፣ አሳዛኝም ኾነ አስደሳች ኾኖ፣ ተሠርቶ የተገኘው ነው።

የእኛ የዛሬ ዝምታ ዋጋ፣ ነገ ለልጆቻችን የሚመነዘረው፣ የሚዘረዘረው፣ የሚተርፈው የባርነት ቀንበር ነው። ይህንን ደግሞ እንግሊዝን፣ ደቡብ ኮርያን፣ ጃፓንን ጠቅሼ በማስረጃ ነገርኳችሁ!

እኛ “አፋችንን ለጉመን” ጥበብ እያልን ስንመጻደቅ የነገውን ትውልድ ዕርባና ቢስ የቲክቶክ ቅራቅንቦ “ሰው እንዳይኾን” አድርጎ ከታሪክም ከተፈጥሮም ለይቶ ያሳድገዋል፤

ክፉዎችም “ትዕግሥትና ብልሃት” ብለን የተመጻደቅንበትን ጥበብ “አዎ ጥበብ ነው፣ በርቱ ፣ ተበራቱ፣ ምን እናግዛችሁ” እያለ እያጨበጨቡልን ወደ መቀበሪያችን ይቀይሩታል።

አባወራው በ”ወ” በተወከለው ወንድነት ሚናው ጠባቂ ነው!

ይህንን እወቅ፦ ትውልዳችን የሚጠፋው፣ ማኅበረሰባችን የሚመክነው በጠላት የጥቃት ኃይል ሳይሆን፣ አልጮች ያለማቋረጥ እየተቀባበሉ፣ እየተወዳደሱ፣ እየተበረታቱ በሚመጻደቁበት እብሪት ነው።

ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል!

ትዕቢት ጥፋትን የእብሪትም መንፈስ ውድቀትን ይቀድማል!

ኃላፊነትን ለሌላ ለማንም አትግፋ—ኃላፊነቱ ያንተ ነው!

ታናሼ! ለ2030 ግብ “የተመድ” (UN) ቤተሰብን የማፍረስ ተልዕኮውን በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ለማቀጣጠል ሽር ጉዱን አጧጡፏል።

ይህም ደግሞ በሴቶቻችን ስም የሚነገድ ነው!

ይህንንም እንዲያጧጡፍና እንዲያቀላጥፍ ያስገደደው ደግሞ ሰሜን አሜሪካ በመሪዋ አማካኝነት በሀገሯም ኾነ ከእርሷ ግብር ከፋይ የተሰበሰበ ገንዘብ በሚደርስበት ቦታ ሁሉ ከሚሠራ ቤተሰብን አፍራሽ፣ ሰውን አጥፊ፣ ማኅበረሰብን አምካኝ የተመድ ዓላማ ራሷን ማግለሏ ነው።

የተመድ፣ ከአፍሪካ ሕብረትና “ግብረሰናይ” ተብለው ትውልዳቸውን “ለበላተኛው ተኩላ” በብልት በብልት ሊያወራርዱ የተቋረጡ ተቋማት ይህንኑ ቤተሰብ በታኝ ዘርፈ ብዙ መርሐ ግብር ተጫርተውታል።

ማን ያውራበት? ማንም?

“ኑ እሺ እናውራበት?”

“እስኪ ሃሳብህን እናየውና፣

ስናየው ከጣመን፣

ጥሞንም ጊዜ ካለን፣

‘ታውቃለህ እጅግ ሲበዛ busy ነን’፣

ጊዜ ኖሮንም ካልረሳነው ....

እንጠራሃለን” ይሏችኋል።

እነማ?

ማይክ ጨባጮቹ!

መብታቸው አይደለም እንዴ?

እንዴታ ግጥም አድርጎ እንጂ!

እንኳን አለማቅረብ አቅርበውኝስ ሰው ያሸሽብናል፣ ከመንግሥት ያጣላናል፣ ገቢ ያቀዘቅዝብናል ሲሉ የቀረጹትን አልጋ ስር የወረወሩት አሉ አይደል! መብታቸው ነው!

መብት ግን ምን ነበር?

ምን ይሻለናል?

የምር እውነቴን ነው የምጠይቃችሁ!

ም…ን… ይ…ሻ…ለ…ና…ል…?

መልሱልኝ እንጂ?


Post a Comment

0 Comments