✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ስጋ ቢታሰር ለነፃነት በጨከነ ልባም ነፃ ይወጣል። ልብ በታሰረበት፣ በጠፋበት፣ ባለጨበት ግን የስጋ "ነፃነቱም" ባርነት ኾኖ ያጠፋል።
አልጫ በእኛ ዐውድ ያለውን ትርጉም እናስታውስ?
🚨 አልጫ(1)፦ coward, ፈሪ፣
🚨 አልጫ(2)፦
✨ Demoralized, ወኔው የተሰለበ፣ ሞራል ያጣ፣ ጽድቅን ለመሥራት መስዕዋትነት ለመክፈል(ቤዛ ለመኾን) ተነሳሽነት የጎደለው፤
✨ ማንነቱን(ታሪኩን፣ ተፈጥሮውን) የጣለ(የካደ)፣ ግራገብ፣ ዐለም የሰጠችውን ሳይመረምር የሚቀበል፤
✨ ጎስቋላ (በአካልም ኾነ በሥነ-ልቦና)፣ በስሜቱ በሰውነቱ ላይ መሠልጠን የተሳነው ድኩም፤
✨ ባርነት የተስማማው፣ የሚስማማው ከዚህም የተነሳ ዕጣ ክፍሉ የኾነ፣ ወዶ-ገብ ባርያ።
ትውልድን ከተፈጠረበት እውነቱ፣ ከመጣበት ትውፊቱ፣ ከታነጸበት እሴቱ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም መለየት ለልሂቃኑና ለሊቃውንቱ እጅግ ቀላል ነው።
በዚህም ማስተዋል የተሳነው፣ ግራና ቀኙን የማይለይ፣ የመጣው ማንም ልጓም እየቀያየረ ወደ ፈቀደው የሚጎትተው፣ በባርነት የሚያሳድረው ትውልድ ይፈጠራል።
በዚያ ዘመንም ከእውነት ይልቅ ሐሰት፣ ከታማኝነት ይልቅ አስመሳይነት፣ ከእረኝነት ይልቅ ምንደኝነት፣ ከአባትነት ይልቅ ሌብነት፣ ከመሪነት ይልቅ ነጂነት፣ ከታማኝነት ይልቅ መሰሪነት፣ ከመስዕዋትነት ይልቅ ሆዳደርነት፣ ከቤዛነትም ይልቅ ባንዳነት ወግ ይኾናል።
እውነት አትሻርም አትጠፋምም! እንደውም በየገበያው ትቆማለች እንጂ። ነገር ግን ሻጯም ኾነ ገዢዎቿ እርሷን ገዝተው፣ ለብሰውና ተጫምተው ሊገለጡባት አይደለም። በስሟ “የትውልዱ ልብ” የሚጠፋበት ሐሰቱ ሊሞሸርበት ሊሸፈንበት እንጂ።
ከእውነት ነጋዴዎቹ (ከነጋድራሶቹም፦ከሆዳደሮቹ ሊቃውንት) አፍ ጣፍጣ እንደ ማር ወለላ በንባብና በዜማ ሳታቋርጥ ትዘንባለች። ይኹን እንጂ ከተዘራችበት ወድቃ ፍሬ አታፈራም። ከእነርሱም ኾነ ከሰሚዎቹ እርሷን ከመስማት የተነሳ ሕይወቱ የሚቀየር አይገኝም፤ ዓለምም ከመምረሯ አትጣፍጥም!
የማይኖሯትን እውነት፣ የሚኖሩትን ሐሰት ለመለበጫ ተደርጋ የምትቀርብ ነችና ከሰሚው ስትደርስም ፍሬ አይኖራትም። ይልቁንስ በሐሰቱ ሊኖር ትጣላለች፤ በሚኖረውም አሳሳች-ሐሰት ትዋጣለች፤ ትውልድም በዚያ አስመሳይ፣ አድርባይ፣ ሆዳደር ይኾናል። እውነትን አውርቶ፣ ሐሰትን ግን አርብቶ ያድራል!
ለምን?
በእውነት የሚሸቅሉት ነጋድራሶች ያልሠሩበትን፣ ያልፈጸሙትን፣ ያልቀየራቸውን፣ የማይቀየሩበትን፣ ሊቀየሩበትም የማይፈቅዱትን የሰውን ጆሮ ይማርኩበት ዘንድ፣ በዚያም ከኪሱ ያደርሳቸው ዘንድ ይጮሁታልና!
ልብን ትቶ ስጋችንን ለመያዝ ለሚመጣው ጠላት ድካሙ ብዙ ነው። ልብ እስካልተማረከ ድረስ የስጋ ምርኮ አንድ ቀን በጨከነ፣ በቆረጠ፣ ልባም ነፃ ይወጣልና።
ስለኾነም ጠላት ትልቁ ጦርነቱ ከትውልዱ ልብ ላይ ነው። የትውልዱ ልብ በስጋዊ መብል ሳይኾን በእውነት፣ በባህልና በእምነት የሚታነጽ ሲኾን እርሱን በሐሰት በርዞ፣ ደልዞና ሰርዞ ካጠፋው የስጋው ነገር ቀላል ነው።
ከመቶ ዓመታት በላይ ውጤታማ የኾነውን፤ እያደር እንደ ጠጅ እየጠነከረ የመጣውን የማርክሳውያንን አታላይ ሸፍጥ፤ በተለይም ደግሞ ትውልዱን እንደ ምሰሶና ማገር የሠሩትን፣ እንደ ድርና ማግ የሰፉትን ባህሎች፣ እሴቶች ማጥፋት ለትውልዱ ጥፋት ዓይነተኛ ወሳኝ መኾኑን የተናገረውን አንቶኒዮ ግራምሺን አስብ!
የትውልዱን ሰውነት የሚበይነውን ወይም የሚበየንበትን ወይም ሲበየንበት የመጣውን፦ ልብ ሚዛን-ልኩን በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ቢያጠፉት ያ ትውልድ ምን ተምሮ ባለ ማስትሬትና ዶክትሬት፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ቢባል “ሰው” መኾን ግን ይሳነዋል።
ስለዚህም ጠላት የትውልዱን ባህል፣ እምነት፣ እውነት፣ እሴት፣ ወግ የሚያውቁ ነጋድራሶችን(እውነትን የሚያውቁ ነገር ግን በእርሷ የሚነግዱ የነጋዴ ራሶችን መሪዎችን) ተጠቅሞ “የትውልዱን ልብ” አሳልፈው ይሸጡለት ዘንድ፣ አልያም ያጠፉለት ዘንድ፦ እንዲበርዙት፣ እንዲደልዙትና እንዲሰርዙት ይልካቸዋል።
ትውልዱም እነዚህኑ ነጋድራሶች አምኖና ፈቅዶ፣ አወድሶና አሞግሶ፣ ከወቀሳና ከከሰሳ ጠብቆ፣ ለሕልውናቸው ወድቆ፤ ልቡን ሰጥቷቸዋልና እርሱኑ በሚያጠፋው፣ ከአባቶቹ በሚለየው፣ ከአባቱም በሚያርቀው፣ በትውፊት ከተቀበለው፦ እውነቱ፣ እሴቱ፣ ባህሉ፣ እምነቱ ነጥለው አልጫ (demoralize) ያደርጉታል።
የትውልዱም መልክ ይቀየራል! ሆሜርና ሄሮዶተስ ቢመጡ “ይህ እኛ የምናውቀው፣ የመሰከርነው፣ የጻፍነውም ኢትዮጵያዊ አይደለም” እስኪሉ ድረስ ከእሴቱ ያርቁታል።
ይህንን ሁሉ ግን በእውነት ለብጠው፣ ሞሽረውና አሳምረው ይሰጡታልና፤ ትውልዱ ያለምንም ጥርጣሬ የሚጋተው፣ ሲኖረው ግን ለባርነት የሚሰጠው፣ ባርነቱንም የሚፈቅደው፣ አልፎ ተርፎም የሚያጸድቀው ይኾናል።
ታናሼ! ወንድነት ተፈጥሮህ፣ አባወራዊ ልዕልናህ እውነትን የሚሻ፣ የሚመረምር፣ ሲያገኘውም ከማውራት ይልቅ የሚኖር የሚገለጥበት መኾን አለበት።
አለበለዚያ ግን በአስመሳይነት ስትኖር፣ በአድርባይነት ስታድር የራስክን ተፈጥሮ እየተቃረንክ ከፈጣሪህም እየተለየህ እንደኾነ አስተውል።
አባቶችህ የሄዱበትን፣ ሰውነታቸው የተበየነበትን እሴት፣ እውነት፣ ባህል፣ ወግ ስትጥል ከእነርሱ፣ ከአባትህም መልክ እራቅህ እንደምትሄድ በዚያም ከተሰጠህ ባንተ ዘንድ ካለህ ተፈጥሮአዊ ነፃነት፣ ራስነት፣ ንጉሥነት ይልቅ ለባርነት ተላልፈህ እንደምትሰጥ እወቅ!
ወንድነት ጽድቅ የምትሠራበት፣ አንድም ጽድቅ ትሠራበት ዘንድ የተሰጠህ መክሊትህ ነው! አባወራነት ደግሞ በእርሱ በተሰጠህ የምትወጣው ሚናህ! ይህ እውነት ነው፤ የምትኖረው(የምታወራው አላልኩም)፣ ልትኖረውም የሚገባህ!
በዚህ እውነት ሳይኖሩ ነገር ግን ከሚነግዱበት ነጋድራሶች ተለይ! እነርሱ በአስመሳይነት ከቆሙበት መድረክ፣ በእውነት ያሸበረቀ ሐሰትን ግተውህ ልብህን ያጠፉታልና!
ልብህ በጠፋበት ደግሞ “ሰውነትህ” ሰው መኾንህ ያበቃል!
0 Comments