ጋብቻህን መንግሥት ሲያዝበት ባርነትህን እያመንክለት

 
✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር 

ሕግን ማቅለል፣ ቀንበርን ማለዘብ የነበረባቸው "ሊቃውንት" ትውልዱ ላይ ሕግን ሲያጠብቁ፤ ሆዳደር አድርባዮች ለባርነት "በሠላሳ ዲናር" እየሸጡን እንደኾነ አስተውል!

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሊቃውንቱ በተለይም በኢኦተቤ “ሊቃውንት” አቅራቢነት የጋብቻ ሥልጠና አስገዳጅ እንዲኾን በተለያዩ ሚዲያዎች መነገሩን ተከትሎ፦ ሳላቋርጥ በዚህ ጉዳይ ላይ መጻፌን አንተም ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትክን አትርሳ፤

እነዚሁ አካላት ከምዕራባውያን፣ በተለይም ከኢትዮጵያውያን እሴት፣ ባህልና እምነት ጋር የሚቃረን፣ በተለይም ደግሞ በወንዱና በሴቷ መካከል ከፍተኛ ጥላቻን በሚዘራ፦ ቤተሰብ በታኝ፣ ትውልድ አጥፊና ማኅበረሰብ አምካኝ፤ ጽንሰ ሃሳብ የቀረጹትን “የጋብቻ ሥልጠና” ለመስጠት ማሰፍሰፋቸውን ተከትሎ፤

በርካታ እንዲህ ዓይነት “የጋብቻ አማካሪ፣ አሠልጣኝ፣ የትዳር ሐኪም” ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ በቤተክርስትያኗ ስር የተጠለሉ፣ “እርሷም” እውቅና ሰጥታ ደጋግማ መድረክ የሰጠቻቸው ሸቃላዎች ትውልዱን ከትውልዱም በተለይም ወንዱን ስልብ፣ አልጫ፣ ጃንደርባና ወኔቢስ ሊያደርጉ ቋምጠው በጉጉት በተሰለፉበት ማግስት፤

“ጋብቻ ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ተጋቢዎች ቅድመ ጋብቻ ሥልጠና ይውሰዱ” ሲባል ጠርጥር!

🌟 የሚያሳዝነው ነገር ከትውልዱ፦

👉 የበዛ ሸክሙን፣

👉 የደረቀ ቀንበሩን፣

👉 “ለሞት አምጪ ኃጢያት ኃይሉ” የኾነ ሕጉን ሊያቀሉለት በሚገባቸው ሊቃውንት ሊጠብቋቸው፣ በለምለም መስክ ሊያሰማሯቸው ባሏቸው ልጆቻቸው ላይ ይህ መፈጸሙ ከፍተኛ ክህደት ነው!

ይህም አልበቃ ብሏቸው ለእርሱ “ሥልጠና ብቻውን በቂ አይደለም፤ COCም ሊኖረው ይገባል” ብለው ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ሕግ(ደረቅ ቀንበር) የሚለምኑ፣ የሚለምኑትን የማያውቁ፣ ግራ ቀኛቸውን የማይለዩ እንከፎች እና የሚሠሩትን የሚያውቁ ምንደኞች መጥተዋል።

የኾነው ኾኖ ጉዳዩን ለማጥናት ይጠቅም ዘንድ እስከዛሬ የጻፍኩትን ተመልከት! ከአሁን በኋላ የሚቀረን ይህንን የሚቀለብስ ልበሙሉ የኾነ “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ እንዳልሰጠው...” የተረዳ በዚያም የሚኖር ትውልድን ማነጽ ነው!

🎯🚨🎯🚨🎯 የጋብቻችንን ነገር ልንመክርበት ይገባል!

በተለይ የኢኦተቤ ከልጆቿ ቀንበርን ከማቅለል ይልቅ ከዓለማዊው መንግሥት ጋር ተሻርካ ቀንበር የምታከብድባቸው፣ ደረቁንም የምትጭንባቸው እንደኾነ እየተመለከትን ነው።

🚨 የ1992 ዓ.ም. ያለ ምንም ምክንያት ፍቺን መፍቀድ ተከትሎ ያሉ የፍርድቤት አፈጻጸሞች በዋናነት የጎዱት የራሷን ልጆች መኾኑ እየታወቀ፤

በወቅቱ “የፍቺ ሰደድ” ወይም “የፍቺ ወረርሺኝ” ተነስቶ የብዙዎችን ቤት አፍርሶ፣ ልጆችን በትኖ የስንቱን ወኔ እንዳደቀቀ፣ መረን ትውልድም እንዳፈለቀ በታሪክ ተመዝግቦ ሲታወቅ፤

ይኸውም ደግሞ በተለይ ክርስስተያኑ ላይ ይበልጡንም ኦርቶዶክሳዊውን ማኅበረሰብ እንዲያጠቃ የተነጣጠረ እንደኾነ ላስተዋለው ግልጽ ኾኖ ሳለ (የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ፍቺን የሚያስተናግድበት ከመንግሥት የተለየ የራሱ ፍርድ ቤት በመኖሩ ማኅበረሰቡን ከዚህ አደጋ ተብቆበታል)፤

🚨 አሁን ደግሞ ከእርሱ በተጨማሪ “በሁለት ወገን በተሳሉት ሊቃውንትና ተቋማት” መካሪና አማካሪነት መንግሥት የትውልዱን ጋብቻ ፈቃጅና ነሺ እንዲኾን “በሊቃውንቷ” አማካኝነት አስተያየት ስትሰጥ መክረሟ እጅግ ያሳዝናል!

ይኸውም እንደቀደመው ሁሉ ኢላማ የተደረገው የማኅበረሰብ ክፍል የራሱን ቤት፣ ቤተሰብና ማኅበረሰብ፤ እናትና ሚስቱን፣ ልጅና ልጆቹን ለመሸጥ የተሰለፈ “የእናት ጡት ነካሽ” ሊቃውንት የበዛበት ይኸው የኦርቶዶክሱ ማኅበረሰብ ነው።

ስለኾነም ትውልዳችንን በመታደጉ፣ ማኅበረሰባችንን በመጠበቁ ረገድ “ሚና፣ ኃላፊነት፣ ግዴታም አለብን” የምንል እኛ አባወራዎች “ጋብቻችን ምን መምሰል አለበት? ከማን ጋር? እንዴትስ?” በሚለው ጉዳይ ሳንውል ሳናድር መምከር አለብን!

🎯 ከመጋባት እየራቀ፣

🎯 ቢጋባም ከመውለድ እየዘገየ፣

🎯 ቢወልድም ከአንድና ከሁለት መዝለል እየተቸገረ፣

🎯 ትዳሩም ለፍቺ እየቸኮለ፤

🎯🎯 ከዚህም የተነሳ ወኔቢስ፣ አልጫ አስመሳይ አድርባይ፣ ስልብ-ጃንደርባ ትውልድ እያፈራ፣ ወደ ባርነት እየገሰገሰ ላለ ማኅበረሰብ በተለይም ኦርቶዶክሳዊያኑ “በእንቅርቱ ላይ ጆሮ ደግፍ” መስጠቱ ለምን አስፈለገ?

ይህንንስ አንስቶ የሚያወራለት፣ የሚላክለት፣ የሚሞግትለት፣ የሚያሳስብለት፣ የሚወቅስለት፤ የሚመክረው፣ የሚያንጸው፣ ቀናውን የሚያሳየውስ... “ሰው” እንዴት ያጣል?

☀️ እጅግ አሳፋሪ እኮ ነው!

🚨🚨🚨 ይህ ትውልድን በጠራራ ፀሐይ ለጠላት አሳልፎ የመስጠት ባንዳነት ነውና!

ወንድምዓለም! በምንም ዓይነት መልኩ ትዳርህ ውስጥ፣ ከምንጣፍህም ላይ፣ በልጆችህም ሕልውና መንግሥትም ኾነ እነዚህ ሆዳደር ሊቃውንት በሕግም ኾነ በመካሪና አማካሪነት ሰበብ ገብተው እንዲፈተፍቱ አትፍቀድ!

ከዚያ በፊት ግን ወንድ ከወንድም አባወራ፤ የተፈጠረበትን፣ የተሰጠውንና የሚሄድበትን ያወቀና የተረዳ መኾንክን እርግጠኛ ኹን!

ይህ የእኔ የመሃይሙ “እንምከር” የሚል መልዕክቴ በወንድነት ተፈጥረው፣ እርሱን ተቀብለውና በእርሱ በልጽገው ጽድቁን ሊፈጽሙበት ላላቸው እንጂ፤

በአጉል መንፈሳዊነትና ዘመናዊነት “እውቀት” ብለው በታበዩበት እብሪት ታጅረው ለሚያላዝኑና ለሚነፋረቁት፣ ለሚንጠባረሩትም “ሊቃውንት” አይደለም!

ጋብቻችንን፣ ትዳራችንን ከሆዳደሮቹ ሊቃውንት መዳፍ ስር ልንታደገው ይገባል! ለታናናሾቻችንም ኾነ ለልጆቻችን “አግቡ!” ብቻ ሳይኾን በራሳቸው “እረኞች” ሳይኾኑ ምንደኞች የተጠመደላቸውን ወጥመድና ማክሸፊያም ኾነ ማምለጪያ ጥበቡንም እንሰጣቸዋለን ባይኾንም እናሳስባቸዋለን!

በሕጉ ብዛት ተመክቶ ከሚያስከትልበት ጥፋት ሙስናው የዳነ (ድኅነት ያገኘ) ትውልድ የለም! ይልቁንስ በሕጉ ብዛት፣ ጥብቀቱ ባርነትና ጥፋቱ፣ ሞትና መቃብሩ ቢጸናበት እንጂ!


Post a Comment

0 Comments