ለእውነት ስንሸማቀቅ በሐሰት እንሸመቅ





ሔኖክ ኃይለገብርኤል 

እውነትን መግለጥና መጋፈጥ ያልፈለገ ትውልድ ምን "መንፈሳዊ ነኝ" ቢል መኖሪያ፣ ማደሪያ፣ መሸሸጊያው ከሐሰት መኾኑ አይቀርም!

ሰሞኑን እየጻፍኩላችሁ ያለሁት የመገናኛ ብዙኃኑ፣ የማትገጹ ሊያነሳው፣ ሊሰማው፣ ሊያወራው፣ የማይወደው እውነት ነው!

እኛ እውነትን ለመስማት፣ ለማውራትና ለመወያየት ዳተኛ በኾንን ቁጥር፤ ትውልዳችን የሚጠፋበትን መንገድ እየሰማን "ጆሮ ዳባ ልበስ" ብለን የተወዘትን አልጮች መኾናችንን ማወቅ አለብን!

ትውልዳችን ሲጠፋ፣ ያውም ራሱ በራሱ ሲያመክን ጣታችንን በሌሎች ላይ የመቀሰር ምንም ዓይነት አግባብ የለንም! ምክንያቱም እኛ የዛሬ፦ ውሎ አዳራችን፣ ሆድ መኝታችን በልጦብን ክፉ እንዲሠለጥን በዝምታችን ተባብረናልና ነው!

ውርድ ከራሴ!

አባወራው ሆይ!
ምን እየሠራህ ነው? ትውልድ እየጠፋ ነው? ያንተ መልስስ "ምን አገባኝ" ነው?

ቤተሰብህ በዓይንህ ፊት ሲፈርስ፣ ልጆችህ በባዕድ ርዕዮተ-ዓለም ሲበከሉ፣ ሲበተኑና ሲጠፉ "እኔ ምን አውቃለሁ፣ ምንም ማድረግ አልችልም" ብለህ ልትሸሸግ ነውን?

ከዚህ በላይ ምን እስኪኾን እየጠበቅክ ነው! ቤቱ በእሳት እየነደደ እንደማይሰማው ሰው መተኛት ምን ዓይነት መርገም ነው?

መልኩን አሳምሮ፣ ድምጹን አለስልሶ፣ በልሂቅና ሊቃውንት ተስቦ፣ የዝና ካባ ደርቦ፣ ሀብትና ገንዘብ እየረጨ፣ "ለእናንተ እኩልነትና መብት" እያለ ልጆቻችንን ከወላጆቻቸው፣ በተለይም ከጠባቂ አባታቸው እየለየ አንድ በአንድ ለሚያጠፋቸው ጠላት በዝምታችን እየሰጠናቸው ነው!

በእርግጥ ይህ ጠላት ልጆቻችንን በእጁ አያጠፋቸውም! ይልቁንስ እነርሱ ራሳቸው ራሳቸውን በእጃቸው ባገኙትም "መብትና ነፃነት" ተጠቅመው ያጠፉ ዘንድ አስቀድሞ ልባቸውን በሐሰት ያጠፋዋል እንጂ!

በ"ሥነ-ተዋልዶ ጤና" ስም ማኅፀናቸውን እንዲያመክኑ፣ በ"ነፃነት" ስም ጾታቸውን እንዲጠራጠሩና እንዲጠሉ፣ በ"እኩልነት" ስም ደግሞ አባታቸውን እንዲንቁ በማድረግ ራሳቸው የገዛ ቤተሰባቸውን፣ ማኅበረሰባቸውንና ሕይወታቸውን እንዲያጠፉ ያደርጋቸዋል።

ይህም ደግሞ ሰውነት ተፈጥሮአቸውን የሚበይን፣ መልካምና ክፉን የሚለዩበትን፣ እውነትን ከሐሰት መዝነው የሚወስዱበትን የልባቸውን ሚዛን በማዛባት ነው።

ልባቸውን ለማዛባት ደግሞ ደግሞ አሁን እንደምታዩት በሚዲያ/በማትገጽ ላይ ይህንኑ ከነባሩ፣ ከጥንታዊው እሴት የሚያርቃቸውን ብቻ እንዲተላለፍ ያደርጋል!

ስለኾነም ሰውነት ተፈጥሮአቸውን የሚወስን፣ የሚበይን፣ የሚገልጥም እሴትን ከማስተላለፍ ይልቅ በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ሰበብ ለመጣው ዕድል ይሰጣል!

በዚያም ትውልዱ ማንነቱ እንዲለወጥ፣ ከተፈጥሮአዊው ባሕሪው እንዲለይ፣ ራሱን እንዲጠላና ሰውነቱን እንዲያጠፋ ይማራል።

ይህንን የሚተላለፉትን፣ ተላልፈውም እውነቱን የሚሹትን፣ ሽተውም የሚያስተላልፉትን ያስፈራራል! ማስፈራራት የጠላት ትልቁ መሣሪያው ነው! ምክንያቱም ለጽድቅ በጨከነ በደፋርና በልበሙሉ ልብ ይረታልና አስቀድሞ ያስፈራራል!

ዛሬ "ቻናልህን ይዘጉታል"፣ "ስምህን ያጠፉታል" በሚል ፍርሃት እውነትን የዋጥህ ሁሉ ነገ አንተም ኾንክ ልጆችህ ለሚጠፉበት ሐሰት ተገዢ መኾንህን እወቅ።

በአንድ ወቅት ፈርቶ የነበረው፣ ኋላ ግን ስለ ጽድቅ መከራን መጨለጥን የተለማመደው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ መክሯል፦

"...ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም!"

እውነትን መሸከም ያቃታችሁ፣ ለሆዳችሁና ለዝናችሁ ስትሉ የትውልድ መጥፋት የማይቆረቁራችሁ ሁሉ፤ ነገ ልጆቻችሁ መክነው ሲቀሩ፣ ትዳራችሁ ሲፈርስና ቤተሰባችሁ የባዕድ ርዕዮተ-ዓለም መጫወቻ ሲሆን ዋጋውን ትከፍላላችሁ።

አንተ ደግሞ ወኔ ይኑርህ!
አባወራነት "ዝምታ" በሚሉት ያልጮች "ጽድቅ"መደበቅ ሳይኾን በድፍረት፣ በጥንካሬና በቁርጠኝነት የሚቆም ጠበቃ ጥበቃም ነው!

እውነትን መጋፈጥ ባልፈቀድከው ልክ በሐሰት መሸመቅ (መደበቅ) ዕጣ ክፍልህ ነው! ከዚህ በላይ ዝምታ አገርንና ትውልድን ከጠላት ጋር አብሮ ተባብሮ ማጥፋት ነው!

እውነትን መናገር "ጽንፈኝነት"፣ ክፉን ማጋለጥ ደግሞ "ፍቅር ማጣት" በሚመስልበት በዚህ ዘመን፣ "ዝምተኛው" ትውልዱ ጥፋቱ ተባባሪ መኾኑን ሊረዳ ይገባል።

ዓለም ትውልዱ እንዲሰማባት የማትፈልገውን እውነት "ጽንፍ የረገጠ ነው" ትለዋለች። ያንን እውነት መናገር፣ መመስከርና መኖር የሚፈራው አልጫም እንዲሁ የዓለምን ወስዶ "ጽንፍ የረገጠ ነው" ብሎ ይሸሸዋል፤

ሽሽቱም በአስመሳዮች አምሮና ጣፍጦ ከተለበጠው ቡዙኃኑ ከሚተምበት ውሸት ያደርሰዋል፤ ማደሪያ መኖሪያውም ከዚያው ይኾናል።

በበግ ለምድ የመጣውን ተኩላ "እኩልነት፣ መብትና ነፃነት" በሚል ስም ስናስተናግድ፣ ነጣቂው መንጋችንን (ልጆቻችንን) አንድ በአንድ እየለቀማቸው፣ ሀገር መገንቢያ ጡቡ ቤተሰብን እያፈረሰው ነው።

ለዚህ ደግሞ በቂ ማስረጃ ሰጠሁህ! አንተ ግን እንቢ አልህ! እውነትን ከመስማት፣ በእውነት ተሠርተህ ከመውጣት ይልቅ አፈርክበት፤ ሐሰትም መደበቂያ መሰወሪያህ ኾነ!

ውርድ ከራሴ!


Post a Comment

0 Comments