ባልጮች ዓለም "አልጫ" ከቶ የለም!





✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር 

እውነትን መመስከር በፈሩት፤ እርሱንም በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም አጽድቀው በኾኑት መካከል "አልጫ" ትርጉም የለውም! በዚያ አልጫነት እንደ ብልህነት፣ ዝምታም እንደ "መንፈሳዊ ጥበብ" ይቆጠራልና።

በአባወራው ዐውድ የአልጫን ትርጉም አስታውስ

🚨 አልጫ(1)፦ coward, ፈሪ፣

🚨 አልጫ(2)፦
✨ demoralized, ወኔው የተሰለበ፣ ሞራል ያጣ፣ ጽድቅን ለመሥራት መስዕዋትነትን ለመክፈል(ቤዛ ለመኾን) ተነሳሽነት የጎደለው፤
✨ ማንነቱን(ታሪኩን፣ ተፈጥሮውን) የጣለ(የካደ)፣ ግራገብ፣ ዐለም የሰጠችውን ሳይመረምር የሚቀበል፤
✨ ጎስቋላ (በአካልም ኾነ በሥነ-ልቦና)፣ በስሜቱ በሰውነቱ ላይ መሠልጠን የተሳነው ድኩም፤
✨ ባርነት የተስማማው፣ የሚስማማው ከዚህም የተነሳ ዕጣ ክፍሉ የኾነ፣ ወዶ-ገብ ባርያ።

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ጥፋት የሚጀምረው ክፋት ሲነግስ ብቻ ሳይኾን፣ "መልካም ሰው ነን" ባዮች ለጽድቅ መቆም አቅቷቸው "ዝምታን" እንደ ጥበብ ሲቆጥሩት ነው።

እነርሱ ሁሉም ጽድቅ የሚፈጸምበትን ድፍረት አይፈልጉም! አይፈልጉምና ጽድቅን የሚፈጽሙ፣ ስለ እውነት የሚቆሙ፣ ፍትሕ የሚያሰፍኑ ደፋር ወንዶችን አያሳድጉም፤ አያፈሩም፣ አይወጣቸውምም!

ከዚህ ፍርሃት የሚገኘው ውጤቱ ግን እጅግ ዘግናኝ ነው፦ ፍትሕ አልባነት፣ ጥራዝ-ነጠቅነት፣ መንግሥታዊ ማጅራት መቺነት፣ የጅምላ ወዶ-ገብ ባርነት፣ የትውልድ ጥፋትና ማኅበራዊ ምክነት ይኾናል!

ለጽድቅ የጨከነ፣ መከራን የጨለጠ፣ ለአልጫዋ ዓለም ጨውነትን የመረጠ ስብዕና አልገነቡምና፣ በባርነት ተስማምቶ ለማደር፣ ትውልዱንም ወደ ሞራል ሙስናና ሞቱ ለማውረድ ይፋጠናሉ።

የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን የአልጫነት፣ የተፈጥሮና የፈጣሪን ክህደት ተግባራቸውን በ"መንፈሳዊነት" ስም ለማጽደቅ፣ ለማስቀደስና ለትውልዱ ለማውረስ የሚሄዱበት ርቀት ነው።

በእነርሱ ዘንድ፣ ሁሉም ተያይዘው አልጫ በኾኑበትም ዓለም ለንጽጽር የሚቀርብ ጀግና፣ ቆፍጣና፣ ልበ-ሙሉና እውነትን የሚሻ፣ ጽድቅን የሚራብ፣ ፍትሕን የሚያሰፍን ሰው በሌለበት መንደር "አልጫ" ቦታ ያጣል።

አንድ ዓይነት፣ አልጫም ኾነዋልና!

በቄያቸው አልጫው ሁሉ እንደ እስስት መልኩን አመሳስሎ፣ እንደ ድመት ጨዋ መስሎ አጎንብሶ፣ እንደ እባብ ቀዝቅዞ ተለሳልሶ በአድርባይነት በሚኖርበት ስብስብ ውስጥ፦

💪 ጥንካሬ "ይጨቁናል"፤

💪 ድፍረት "ይበድላል"፤

💪 በራስ ላይ መሠልጠን ደግሞ "ያካብዳል" ተብለው ይወረፋሉ።

አባወራዊ ንቅናቄያችን ግን ትውልድን ለማትረፍ ይቸኩላል! "በነቀርሳ አምጪ ተውሳክ" ጽንሰ-ሐሳቦች የልጆቻችን ልብ እንዳይበከል እረፍትን እንቢ ብሎ ይዘረጋል!

ምንም እንኳ በሰፊው መድረክ ወጥተን ለሕዝብ የመናገር ዕድል ብናጣም፣ በእጃችን ባለው አነስተኛ አጥርና ቁጥር ውስጥ ኾነን እውነቱን ለትውልዱ መጠቆማችንን መርጦ ለመጣው ደግሞ ማሠልጠናችንን አናቆምም።

ትውልዱ ከተፈጠረበት ማንነቱና ከመጣበት ትውፊቱ ርቆ አልጫ (Demoralized) እንዲኾን የሚደረገው በጠላት በሚነዱ "ሊቃውንት" ስባሪ ሳንቲም ተሸጦ ነው።

በዚያም በጅምላ አልጫ እየተደረገ ባለው ትውልድ መካከል አልጫነት "ወግ" ኾኗልና፤ ተራማጅነትና ዘመናዊነትም ተብሎ ይጠራልና "አልጫ" መኾኑን እንኳ አያውቀውም።

አባወራነት ለባርነት በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ከሚግቱን "ነቀርሳን አስከታይ ተውሳክ" እንቢ ብሎ መራቅ ነው።

ባርነትን አምኖ "ምንም ማድረግ አይቻልም" ብሎ ከመቀበል እና እርሱንም አውርሳ የታሪክ ተወቃሽ ትውልድ ከመኾን ይልቅ፤

የትውልዱ ልብ ለማትረፍ "ለነፃነት" መጋደል፣ በስሜት ከመነዳት ይልቅ በልብ መመራት ነው። እውነትን መመስከር ባልቻሉበት፣ ፍርሃትን በመንፈሳዊነት ካባ በሸፈኑበት በዚህ ዘመን፣ እኛ ግን ለአባቶቻችን ዳና ታማኝ ኾነን በወንድነታችን በልጽገን በአባወራነቱም ልዕልና ሰፍነን እንቀጥላለን።


Post a Comment

0 Comments