በእሴት የደለበውን ልብ-አልባነት ያወራርደዋል!



ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር 

በእምነት፣ በባህልና በታሪክ የዳበረን ትውልድ እነርሱን ቢበርዙበት፣ ቢደልዙበትና ቢሰርዙበት፤ ልብ-አልባ ኾኖ ማንነቱን ያሳጣዋል፤ ያጠፋዋልም!

በእምነት፣ በባህልና በታሪክ የዳበረን ትውልድ እነርሱን ቢበርዙበት፣ ቢደልዙበትና ቢሰርዙበት፤ ልብ-አልባ ኾኖ ማንነቱን ያሳጣዋል፤ ያጠፋዋልም!

ይህ ዛሬ ላይ የምናየው እውነት፣ በነባር እሴቶች “ደልቦ” (በልጽጎ) የነበረን ትውልድ፣ በልሂቃንና በሊቃውንቱ መርዘኛ ሃሳብ ማንነቱን ሲያጣ የሚተርፈው ጥፋት ነው።

ሀገርን በአብዮት፣ ትውልድን በነውጥ ማሸነፍ ያቃታቸው እኩያን ማርክሳውያን፤ ምሰሶና ማገር የሆኑትን የማኅበረሰቡን እሴት መበረዝ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ግራምሺ ተናግሯል። ዛሬ በልሂቃኑና በሊቃውንቱ እየሆነብን ያለው በትክክል ይህ ነው።

ትውልዱ በውስጡ አከማችቶት የነበረው፣ ለዘመናት የቆየው የሞራል ልዕልና እና የሰብአዊነት ሀብት (Wealth of Values) ዛሬ በደረቅ ንድፈ-ሐሳቦች እየተመታ ነው። ልሂቃኑም ኾነ ሊቃውንቱ የሚግቱት “እውቀትም” ኾነ “ስሜታዊነት” ብቻውን የቆመ በመኾኑ፣ ትውልዱን ከነበረበት “የእሴት ሙላት” አውጥቶ ወደ “ልብ-አልባነት” እየከተተው ይገኛል።

ነባር ሥርዓቶች፣ ማኅበረሰብ የገነቡና ትውልድ ያነጹ እሴቶች “የአንባገነኑ አባወራዊ ሥርዓት መዋቅር ናቸው” እየተባሉ በአስኳላው ብቻ ሳይኾን በመንፈሳዊ ተቋማት ጭምር መኮነናቸውን እናያለን። ይህ ስያሜ እሴቶቹን ለማፍረስ የሚሰጥ የሸፍጥ ስም ነው።

አንድ ትውልድ ለዘመናት የኖረበትንና ማንነቱን የቀረጸለትን እሴት “ጨቋኝ ነው” ተብሎ ሲነገረው፣ ያንኑ እሴት ጥሎ ባዶነትን ይላበሳል።

አስተዋይና ሚዛናዊው ልብ የሚገኘው ደግሞ በነባር እሴቶች ውስጥ እንጂ በወረቀት ላይ በሚሰበኩ ንድፈ-ሃሳቦች ውስጥ አይደለም።

በዚህ የተነሳ ትውልዱ “የሰለጠነ” እና “ነፃ የወጣ” ቢመስለውም፣ በተግባር ግን ርህራሄና ሰውነት የጎደለው ልብ-አልባ ሆኗል።

“ያወራርደዋል” ስል፣ ትውልዱ በእሴት ደልቦ የነበረውን ስብዕናውን ለባዕድ ሃሳባዊነት አሳልፎ ሲሰጥ፣ ከመጣበት መንገድ ሲወጣና የሚሄድበትንም ሲስት የሚከተለውን ውድቀት ነው።

የሰውነት መጥፋት፦ እሴቱ ሲሰረዝ፣ ሰው የመኾን ትርጉሙ፣ “ሰው” የመባል ስሙ፣ እንደ “ሰው” የመኖር ወጉ አብሮ ይጠፋል።

በእሴት የደለበውን ያንን ትልቅ ማንነት፣ ዛሬ በሊቃውንቱ “ኋላቀር፣ አካባጅና ጨቋኝ” ይሉት ፍረጃ ምክንያት ከትውልዳችን በተለይም ከወንዶቻችን ዘንድ እያጣነው ነው።

ይህ የባዶነት ጉዞ ደግሞ መጨረሻው የታሪክ ኪሳራን ማወራረድ ነው። ስሩን በጥልቁና በሰፊው ያልሰደደን ዛፍ ነፋስ እንደሚያወዛውዘው ሁሉ፣ እሴቱን የጣለ ትውልድም የገዛ ማንነቱን ጥሎ፣ አጥቶ፣ አውድሞ ይጠፋል!

ልሂቃኑም ኾነ ሊቃውንቱ ተባብረው “ዐዲስ ማንነት እንፈጥራለን” እያሉ ነባሩን “ልባሙን ሰው” (ልባምነትን) “ከአንባገነንነት” እየቆጠሩ እያስተማሩም እየገደሉት ነው።

በእሴት የደለበውን ማንነታችንን ከልብ-አልባነት ለመታደግ፣ ወደ ቀደሙት የሰውነትና የሞራል መሠረቶቻችን መመለስ ምርጫ ሳይኾን የህልውና ግዴታ ነው!

ምዕራባውያንን ያጠፋቸው ይኸው በሊቃውንቱ እየተበጠበጠ፣ በልሂቃኑ እየተጠለቀ ተቀድቶም ትውልዱ የተጋተው ባህልን፣ ነባር ወግን፣ እሴትን ጠልነት ነበር።

በወቅቱ “ከተኙበት ሲቀሰቀሱ” ነቅተውም ጉዳዩን እንዲመለከቱትና ልጆቻቸውን እንዲታደጉ ቢጠቆሙም እነርሱ ግን “ክፉ ሃሳብ ‘ክፉ’ ነውና በራሱ ጊዜ ይጠፋል” ብለው ናቁት!

ዛረረ የራሳቸው ልጆች “የራሳቸው” እስካይመስሏቸው ድረስ ራሳቸውን ጠልተው፣ ማንነት ታሪካቸውን፣ ማንነት ተፈጥሮአቸውን ጠልተው ሲጠፉና ሲያጠፉ ማየት እንደ እግር ውስጥ እሳት ያቃጥላቸዋል።

ሰሚ ያጣው የአባወራ ገጽም ሩጫ ይህ ቀን ደርሶ፣ ማጣፊያ መመለሻው አጥሮ፣ ትውልድ በመቀጠልና በመጥፋት ቅርቃር ገብቶ ከማየት በፊት ከማንቃትም አልፎ የጠፋውን እሴት ለመመለስ ማሠልጠንም ነው!

ብዙዎች ይቀኑበት የነበረ፣ በእሴት የደለበ ኢትዮጵያዊ ማንነት ዛሬ እነዚያን እሴቶች በመበረዝ፣ በመደለዝ እና በመሰረዝ ትውልዱ ልብ አልባ እንዲኾን ባፍጢም በተደፉ ሆዳደር ሊቃውንቱና ልሂቃኑ ይፈጸማል!

ይህም ትውልድን የሚያጠፋ፣ ማኅበረሰብን የሚያመክን ኾኖ ይጠናቀቃል!


Post a Comment

0 Comments