ወንድ ልጅ ተባብሎ ወንድነትም ተለባብሶ አያድግም!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር 

ከእናቱ ጀርባ ወርዶ በስሜት አንቀልባ ግን ታዝሎ የሚያድግ ወንድ በቁሙ ይሞት ዘንድ በአስተዳደግ በደል የተፈረደበት ዕድለቢስ ነው!

ወንድ ልጅ በአባቱ መልክ የተፈጠረ እርሱን ወደ መምሰል ግን ማደግ ያለበት(በኦሪት ዘፍጥረት ያለውን አሰላስል)፣ እንዲያ በማደጉም ሰውነቱ በእውነት የሚበየንበት ነው።

ስለኾነም እንዲያ በሚያሳድገው የአባቱ፣ የአባቶቹ፣ የጎበዛዝቱ መንገድ እየወደቀ እየተነሳ እንዲሄድ ይመሩታል እንጂ አያዝሉትም!

በዚያ የሕይወት መንገድ ላይ ለሚሄደው ለሚያድገውም ወንድ ፈጣሪው አባቱ ያለ ትጥቅና ስንቅ አልሰደደውም። ነገር ግን ወንዱ በተሰጠው ትጥቅና ስንቁ (ወንድነት መክሊቱ) “ጽድቅ ልፈጽምበት፣ ፍትሕ ላስፍንበት” ከማለቱ በፊት እንዲያውቀው፣ እንዲሠለጥንበት፣ እንዲያበለጽገውና እንዲያይልበትም ይጠበቃል እንጂ!

አንድም ባልሠለጠነበት እንዳይበድል፤ አንድም ደግሞ ቢሠለጥንበት፣ በጣም ቢበለጽግበትና እጅግም ቢያይልበት ሊሠራው ያለውን ጽድቅ በቂ ኹኔታ ይፈጽመዋልና!

የማሠልጠኑን ኃላፊነት ደግሞ በዋነኛነትና በቀዳሚነት ወላጅ አባቱ፣ የእድሜ ታላላቆቹ፣ የተገኘበት ማኅበረሰብ ባህልና እምነትና እሴቱ በተወራድ የሚወስዱት ይኾናል።

እነርሱም በንባብ፣ በተረት፣ በትርክት ብቻ የሚያሳድጉት አይደለም፤ ይበለጡንም በተግባር፣ በሥራ፣ በመከራም ቀድመው እየሄዱ ዳና ፈለጋቸውን እየተዉለት ያንጹታል እንጂ!

እርሱ ለዚያ ማኅበረሰብ ከእርሱ እኩዮች ጋር በአንድነት ተጋምዶ፣ እሴቱን ከቀዳሚዎ፦ ተረክቦ፣ ጠብቆ፣ ተንከባክቦ፣ አበልጽጎ ደግሞ ለተከታዩ የማቀበል ኃላፊነት አለበት!

ለዚህ ኃላፊነቱ ይበቃ ዘንድ ታዲያ ከእናቱ ጀርባ ወርዶ፣ ድክድክ እያለ ሮጦ ያደገውን፣ እየጎረመሰ የሚመጣውን ወንድ “እወደዋለሁ፣ እንወደዋለን” በሚል ፈሊጥ ደግሞ “በስሜት አንቅልባ” እያባበሉ አያዝሉትም!

ስሜቱን የሚረብሽ፣ “ደስ የሚለውን” የሚያደፈርስ፣ “ምቾት ድሎቱን” የሚያሳጣን ግጭት እንዲጋፈጥ በዚያም ሥነ-ልቡናዊ ጥንካሬ እንዲኖረው ያሳድጉታል።

ስለኾነም እንዲህ ከሚያደርጉት ክስተቶች አይሰውሩትም ያጋልጡታል እንጂ። “ቢረበሽስ?” ይረበሻ! “ቢያለቅስስ?” ያልቅሳ! “ቢደነግጥስ?” ይደንግጣ! ባይኾን እንዲህ ሲፈጠር እርሱም እንደዚህ ሲኾን ክስተቱን እንዴት ማስተናገድ እንዳለበት ይጠቁሙታል፤ በተለይ ግን በራስ ኖረው ያሳዩታል እንጂ “ሳስተውና ባብተው” “በስሜት አንቀልባ አያዝሉትም”!

በልጅነቱ እያባበሉ ያሳደጉት ወንድ አድጎ ምን ማስትሬትና ዶክትሬት ቢይዝም የምታባብለው እናቱን፣ ወይም የሚያባብለው ወዳጁን፣ ወይም የሚያባብል ራሱን ይፈልጋል፣ በዚያም ይደበቃል!

ስለዚህም “እውቀት” ምን አስፈላጊ ነው ብንልም ለወንድ ልጅ ግን በተግባር ተፈትኖበት በራሱ ልቡና ተተርጉሞ የሚቀመጥ ጥበብ ግድ ይለዋል!

እነዚህ ኢምንት እየኾነ አልያም በጠላትና በሆደሮቹ እየተበረዙ ሲመጡ ግን እንደዚህ ያለው የእኛ “የአባወራ ገጽ” እና በዙሪያውም ያሉ አባወራዎች ክፍተቱን በመሙላትና ትውልዱ ላይ የተጋረጠውን የጥፋት አደጋ በመቀልበሱ ደረጃ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

ፈተና እንዴት፣ በየትም በኩል የሸሸው ሲሸሽ ለኖረው እርሱ እንደ Hard Disk ወይም SSD ወይም እንደ Flash Disk የመረጃ (”የእውቀት”) ቋት እንጂ እንዴት ሊኖረው እንዳለው አያውቅበትም!

ስለኾነም የምታነቡትን ዝም ብላችሁ አትጋቱ! ወደ ተግባር ቀይሩት ለአረቄ መጠጫ ወሬ፣ ለቡና ማንቃረሪያ ጨዋታ ብቻ “አውቃለሁ፣ አንብቤዋለሁ፣ ይህ ማለት ይሄ ያ ማለትስ ያ አይደለም እንዴ” ለማለት አትቸኩሉ!

ወደ አባወራነቱ ማማ የሚወጣው ብዙ ስለወንድነት ያነበበው፣ የተረከው፣ የተናገረው፣ የሳለው፣ የሞገተው ሳይኾን ባወቀው ኖሮ፣ ተፈትኖ፣ ወድቆና ተነስቶ ነጥሮም የወጣበት ብቻ ነው።

በዚህም መንገድ ሄደው ለሚገለጹት ምንም እንኳ የተፈጠሩበት መልክ (structure) በመጠኑ ቢለያይም እየመሰሉ የሚመጡት አንድ ማዕከላዊ ገጽን መቃረባቸው አይቀርም!

በወንድሞች ማኅበር ስትቀመጡ፣ በተለይም የአባወራዎቹን ዳና ስትከተሉ ወደ ተጠራችሁበት ልዕልና ማደግ ዋናችሁ፣ አንድ ወደሚያደርጋችሁ ምስል መምጣት ትርፋችሁ ይኾናል! ይህ ከትውልዱ ኾን ተብሎ እንዲርቅ ተደርጓል!

ገጻችንን የማያውቀው አለ ብዬ ለማሰብ እቸገራለሁ! ነገር ግን “ማንበብ ደስ የማይለው ብዙ አለ” በሚለው ደግሞ እስማማለሁ! እርሱም ልክ ነው!

የአባወራ ገጽ ሰዎች ሲያነቡት “ደስ እንዲላቸው” አይጻፍም! ደስ ያላቸውም ያላላቸውም እርሱ እነርሱ እንዲሰማቸው የመረጡት እንጂ የገጹ መልዕክትም ኾነ ተጽዕኖ አይደለም!

ኾኖም ግን የእነርሱንም ኾነ የማንንም ስሜት ሳይጠብቅ በትውልዳችን ላይ በተለይም የእናቶቻቸው፣ የሚስቶቻቸው፣ የልጆቻቸው የቤተሰባቸው ጠባቂና መሪ በኾኑት ወንዶቻችን ላይ የተቃጣውን የአባታቸውን መልክ የማሳጣት እርሱንም ወደ መምሰል እንዳያድጉ የመጋፋቱን ክፉ ዓላማ ያፈርሳል!

ይህንንም ደግሞ ደፋር፣ ጠንካራ፣ ሥልጡን የኾኑ፦ ኃይለኛ፣ ቆራጥ፣ ቆፍጣና፣ ጽኑ፣ ልበሙሉ፣ ወኔያም፣ ልባም፣ ተዋጊ ወንዶችን ልክ እንደ አባቶቻችንና አባታችን በማነጽ ወደ ተፈጠሩለት መልካቸው ወደ’ሚሳሉት ምሳሌያቸው ያንጻቸዋል!

ይኹን እንጂ ዓለም ዛሬም የ”አባወራ” ገጻችንን መልዕክት “ይጠጥራል፣ ይጠነክራል” ስትል ዛሬም ልጆቻችንን (ወንዶቻችንን) “በለስላሳና ደሳስ በሚሉ የስሜት አንቀልባዎች” አዝላ ምስኪን አድርጋ ታቀልጣቸዋለች(ቀላጭ)!

ሰምተሃል! እኔን እንቅልፍ በሚነሳኝ ጉዳይ ግዴታዬን እየተወጣሁ ነው! አንተስ? ክፉው ሥራ “በራሱ ጊዜ እስኪጠፋ” ቁጭ ብለህ እየጠበቅከው ነውን?

ብታስተውል ራስህንም ኾነ ትውልድን ታተርፋለህ!

🚨 ትውልድ እያጣን ነው!

🚨 ቤተሰብ እየፈረሰ ነው!

🚨 ልጆቻችን እየተበተኑ ነው!

🚨 ጋብቻ ትዳራችን መጠቋቆሚያ እየኾነ ነው!

🚨 ትዳርን ታናናሾቻችን እየፈሩት እየጠሉትም ነው!

🚨 ምን ቢማር ዶክተርና ኢንጂነር፣ ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት ቢባል አልጫና አስመሳይ አድርባይ ሆዳደርም ትውልድ እያፈራን ነው!

🚨 የጠላቶቻችን መሳቂያና መሳለቂያም እየኾንን ነው!

🚨 ማኅበረሰባችንም እየመከነ ነው!

.... ብለን እንወያይበት ዘንድ የብዙዎችን በር አንኳኳን አብዛኞቹ ግን ፈቃደኛ አይደሉም! የትውልዱ ችግር አሳስቧቸው በመፍትሔው ላይ የሚሠሩበት ሳይኾኑ የሚሸቅሉበት፤

አንድም ደግሞ “ተከታዮቻችንን ያስቀይምብናል” ሲሉ “የሚያስቡለት” ናቸው! ፈቃደኛ የኾኑትም የሰጠናቸውን ሰው ከማይደርስበት አርቀው አስቀመጡት!

ግን ለምን?

ትውልዱ ሲጠፋ እያወቅን በገፋነው ባልሠራነውም ጽድቁ ተጠያቂዎች እኛ ነን! ጣታችሁን ሌሎች ላይ አትጠቁሙ!


Post a Comment

0 Comments