✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ትውልድ የሚመጣበት፣ እርሱም የሚታንጽበት ጊዜና "ዕድገትህ" ዛሬ፣ አሁን ተያይዘው ይሄዳሉ እንጂ ከተጠባበቁ የቀደመህ ይወርስሃል!
ዛሬ በዓለማችን ላይ “ሕይወትን በዕድሜ መቆያዎች ማቀድ” የሚል አደገኛ ፈሊጥ ነግሧል። “በ30 ዓመቴ አገባለሁ፣ በ32 የመጀመሪያ ልጄን እወልዳለሁ፣ በ35 ቤት እሠራለሁ” የሚለው ስሌት ዛሬ ለውጤት የሚያበቃ አይደለም።
መልካሙን፣ ልኩን፣ ተገቢዉን፣ ውቡን እንሠራበት ዘንድ የተሰጠን ጊዜ፣ ዕድሜያችን ከሄደ እንደማይመለሰው ወራጅ ውሃ፣ እንደ ጥላም ኾኖ ሳለ፤ “እቆያለሁ” ማለት “እጠፋ ዘንድ መርጫለሁ” ማለት ነው።
“ገና አልተመቻቸሁም፣ አልረጋሁም” የሚለው ሰበብ በዚህ ዘመን የሚያዋጣ አይደለም። ዛሬ በመኪናና በአውሮፕላን ሮጠህ በሰዓታት ውስጥ በምትደርስበት ዓለም ላይ ኾነህ “አልረጋሁም” ማለት ልክ አይደለም!
ትናንት አባቶችህ እኮ በፈረስና በበቅሎ፣ ከወራት ጉዞና ከመንፈቅ መንገድ በኋላ ጉዳይ ፈጽመው፣ በዚያው መካከል ልጆችን ወልደውና ኮትኩተው አሳድገዋል። ያንተ “አለመረጋጋት” የኑሮ ሳይሆን የውሳኔና የወንድነት ወኔ ማጣት፣ የአባወራነት ልዕልና መጥፋት፣ የመጣህበትን ዓላማ መሳት ነው!
ይህ ችግር በተለይ በክርስትያኑ ማኅበረሰብ ዘንድ እንደ ወረርሺኝ እየተስፋፋ ይገኛል። ይህም በአጋጣሚ ሳይኾን አስቀድመው ማርክሳዊ በኾነው ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ በተለይም አባወራ ጠል “ነቀርሳ” የኾነ ጽንሰሃሳብ የተበረዙቱ “መምህራን” ትውልዱን መርዘውታልና ነው።
“ኑሮዬን ሳልመሠርት፣ ሀብቴን ሳላደራጅ አልወልድም” የሚለው የሰነፎች ሰበብ፣ ትውልድን እያጠፋና ማኅበረሰቡን እያመከነ ነው።
አባቶቻችን ባገኙት ኑሮ “ተመስገን” ብለው፣ ዘራቸውን እያስቀጠሉና እያሳደጉ ኑሮአቸውንም ያደራጁ ነበር። ዛሬ ግን ኑሮን “ለማጥራትና ለማሻሻል” በሚል ሰበብ ትውልዱ ዘር-አልባ፣ ልጅ-አልባና ትውልድ-አልባ ጉዞ ላይ ይገኛል።
በሠላሳ ዓመቱም፣ በሠላሳ አምስቱም፣ በአርባውም ስታገኙት በስጋትና በጥርጣሬ፣ በፍርሃትና በ”ወይኔ ወይኔ” ተተብትቦ የሚኖር ሃይማኖት እንጂ እምነት የሌለው ጎስቋላ አልጫ ኾኗል።
እርሱ እንዲህ በኾነበት እርሱን ልታይ፣ ልትከተል፣ ልትታዘዝ የመጣችው ሴቷ እንዴት ከእርሱ አትብስ! ስለኾነም ማግባትና ማርገዝ፣ መውለድና ማሳደግ ያለበትን “ሕይወት” ትፈራዋለች፣ ትሰጋዋለች!
በገንዘቡ ብዛት አይደለም፤ በልቡናው ጽናት፣ እምነትና ልበሙሉነት የሚያሳርፋት ወንድ አይደለምና። አንተም አልጨሃልና፣ ስጋቷን አንረኸዋልና ልታምንህ ልትወልድልህም አትፈልግም!
ለዚህም ነው ትናንት ቢኾን አስር ልጅ ሊያድግበት የሚችል ሀብትና ንብረት ይዘው እየኖሩ፤ ነገር ግን ምግብ የሚያጠሩ፣ ጠረጴዛና ሳህን የሚቀያይሩ፣ ቤትና መኪና የሚያበዙ፣ ቁምሳጥናቸውን በልብስ የሚያስጨንቁ፣ ውሻና ድመት የሚያረቡ፣ በፎቅ ላይ ፎቅ ለመከመር እንቅልፍ የሚያጡ የትውልድ ኪሳራዎችን የምንታዘበው!
ትሰማኛለህ! የምታባክነው ጊዜ ያንተ ብቻ አይደለም፤ የቤተሰብህና የሃገርህም ጭምር ነው። አባቶችህ በብዙ በሽታና አስጊ ከባቢ ውስጥ እንኳ እያሉ አንተንና ወንድም እህቶችህን ለማምጣት ከተፈጥሮ ጋር፣ ከበሽታ ጋር፣ ከወራሪ ጠላት ጋር ገጥመው ከዚህ አድርሰውሃል።
አንተ ግን “ሳልሻሻል አልወልድም” በሚል ሰበብ ልጆችህ ውሃ እንዲወስዳቸው ስታደርግ ተፈጥሯዊ ኃላፊነትህን እየካድክ፣ የአባቶችህንም ድካም፣ የሰዉትንም ሕይወት ዋጋቢስ እያደረግክ ነው!
እንቢ ብለህ “ቤትና ገንዘብ፣ ምቹ ጊዜም” ስትጠባበቅ ከኖርክ፣ መጨረሻህ የታወቀ ነው፦ የጊዜ ሰሌዳን ያልጠበቀው፣ የማይጠብቀው በጊዜ ውስጥ ግን የሚሠራው ጊዜውን ተጠቅሞ የዘራውና የበዛው ሌላው ወገን ይወርስሃል!
ሃብትህ፣ ታሪክህ፣ ንብረትህና እምነትህም ጭምር ባለቤት አልባ ኾነው ለቀደመህ፣ ካንተ ይልቅ ለበዛው ምርኮ ይኾናሉ፤ ይወሰዳሉም።
አንተም ምንም ማድረግ አትችልም!
ሁሉንም ነገር እንደአመጣጡ በጊዜው አስተናግድ፤ በተለይም ትውልድን ማምጣቱን ዘርህን ማስቀጠሉን ዛሬ አሁን ጀምረህ አድርገው።
አሁን ውለድ፣ ልጅህም ሲያድግ ያንተም የገንዘብ፣ የጥበብ፣ የንብረት፣ የሰው ሀብትና አቅምህ አብሮ ያድጋል። እርሱም እድገት ምን እንደኾነ በተግባር እያየ፣ በልቡ ሰሌዳ ላይ እየተሳለ ይመጣል፤ ይህንንም ይደግማል።
“ሳይመቸኝ አልወልድም” አትበል! “ምቾትህ” በአንተ አእምሮ ካለው፣ ጠፍንጎ ካሰረህም ገዳቢ፣ የብሶትና የእጦት የስጋትም ሃሳብ የወጣ እንጂ ልበሙሉ ከኾነ፣ ባባቱ እምነት ካረፈ፣ በተስፋና ከሞላ ፍቅሩ ለማካፈል ከጓጓ ልብ አይደለም።
ትውልድ የማስቀጠል ሥራህና ኑሮህን የማደራጀት ትግልህ ጎን ለጎን፣ ትይዩ ኾነው መሄድ ያለባቸው የሕይወት መንገዶች ናቸው።
ጊዜ፦ በተሰጣቸው ዕድሜ ጽድቁን የሚፈጽሙ ልባሞችን እንጂ ብሶተኛ፣ ችጋረኛ፣ ሰበበኛ፣ ለቀስተኛ የኾኑ ታካቾችን እነርሱ ማንም፣ ከየትም ቢኾኑ ቆሞ አይጠብቅም!
ታናሼ! ጊዜ ውሃ ነው፣ ካለፈ አይመለስም። በቆጠርከው ዕድሜ ሳይሆን በሠራኸው ትውልድና ባሳረፍከው አሻራ ትመዘናለህ፣ ትታወሳለህ ያውምየሚያስታውስህን ትውልድ ካመጣህ፤ አለበለዚያ ግን ትረሳለህ፣ ትጠፋለህም።
በደረስክባት፣ ባየሃትም ዛሬ፣ በቆምክባት አሁን ራስህን ድገምበት፣ ደጋግምበት፤ በምታውቃት ዛሬ ካልኖርክባት፣ ዘርህንም ካላቆየህባት በማታውቃትና ባልደረስክባት ነገ የመውለድህ ነገር ኢምንት ነው።
በአንጻሩ ደግሞ “ነገ ሲመቸኝ” ስትል የስጋት፣ የብሶት፣ የእጦትና የችጋርም ሃሳብህ እጥፍ ድርብ እየኾነ ጭራሽ እያሳቀቀህና እያመከነህ ይቀጥላል።
ለመሥራት ለመለወጥና የምታደርገውን ጥረት ባደንቅም አንተን የመሰሉ፣ በአባትህ ቃልና በአባቶችህ መንገድ የሚሄዱ ልጆችን ማብዛትን ግን የሚስተካክል ከጥረትህ ውስጥ አንዳች አይኖርም!
በእርግጥ ራስህን ለመድገም፤ ያንን “ራስህን” መውደድ ይፈልጋል! ይኹን እንጂ ትውልዴ እንኳን ራሱን ሊወድ እርቃኑን እንኳ በመስታወት ማየት የማይፈልግ፣ ልቦናውንም በእውነት መስታየት መመርመር የማይመርጥ እንዲኾን ተደርጓል!
“እወደዋለሁ” የሚለውም ተፈጥሮውን በሚቃረን፣ ሰውነቱን በሚያፈርስ፣ ማንነቱን በሚያጠፋ ይህንንም በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም አጽድቆ በታጀረበት እብሪቱ የሚጥለው ነው!
ወንድምዓለም! ትውልድ የሌለው ሃብት፣ ንብረት፣ ሀገር፤ በማንም በቀላሉ ለመወረስ፣ ለመጥፋትና ለመደምሰስ የተጋለጠ ባለቤት-አልባ ባዶ ቤት፣ መንደር፣ ሀገርም ነው!
0 Comments