ሐሜትን የምንጠላ ሐሜተኞች!



✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ሐሜት ጥሩ አለመኾኑን ከልጅ እስከ አዋቂው ቢመሰክርም፣ በአንደበቱ ቢጠየፍም፤ ትውልዴ ግን ሐሜት ወዳድ መኾኑን ራሱን ከሚለውጥበት ይልቅ የሌሎችን ሐሜት የሚሰማበት ጊዜ መብለጡ ያሳያል።

ይህ የተገላቢጦሽ ጉዞ የዛሬው ትውልድ ትልቁ መቅሰፍት ነው። “አልወድም” የሚለውን ነገር በተግባር ሲያመልከው፣ “እጠላዋለሁ” የሚለውን ሐሰት እንደ ማር ሲልሰው ማየት ደግሞ ልብ ይሰብራል።

በመድረኮቻችን ራስን ስለመለወጥ፣ በተፈጠርንበት ወንድነት ወደ አባወራዊ ልዕልና ስለመውጣትና ትውልድን ከውድቀት ስለመታደግ የምንዘራው እውነት የሰሚ ያለህ ሲያሰኝ፤ የሰውን ገመና የሚዘከዝኩ የሐሜት መድረኮች ግን በአድናቂ ይጨናነቃሉ።

ሰዎች ስለ ሐሜት መጥፎነት እንዲሰብኩ ቢጠየቁ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅስ እየመዘዙ ሊያስተምሩን ይችላሉ። ይሁን እንጂ ስልካቸውን ሲከፍቱ ቀድሞ የሚስባቸው “እንቶኔ እንዲህ ኾነ/፣ እንዲህ አደረጋት/ አደረገችው፣ እንዲህ አላት/አለችው የሚሉትን፣ የሚያጋሩትም የሌሎችን ውድቀትና ጥፋት ነው።

ራስክን ታዘብ!

ራሳቸውን ከሚቀይራቸው መልእክት ጋር ከመጣበቅ ይልቅ፤ የሰዎችን የግል ሕይወት የሚበረብር፣ የሚያማና አሉባልታ የሚነፋውን መርጠው ይከተላሉ። ለሐሜተኛው እጅ መንሻ “በመስጠትም” የጥፋት ድግሱን ያደምቁታል።

ትውልዱ ራሱን የሚቀይርበትን እውነት የማይሰማው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እውነት “ተነሳ፣ በራስህ ላይ ሠልጥን፣ ኃላፊነትህን ተወጣ፣ ተጠያቂነትን ተቀበል፦ አባፈራ ኹን” የሚል መራራ መመሪያ ስላላት ነው።

ይህ ደግሞ ከመስዋዕትነት ይልቅ ምቾትን፣ ከመታነጽ ይልቅ መላሸቅን፣ መቅለጥንና መቅበጥን ለሚመርጥ፣ እንዲመርጥም ለፈዘዘ “አልጫ” ትውልድ ይከብደዋል።

ሐሜት ግን ምንም ጥረት አይጠይቅም፤ የሌላውን ጉድ እያዩ ራስን እያመጻደቁ መኖር ስለሚያስችል፣ አሰሶች ራሳቸውን የሚያደነዝዙበት መርዝ ኾኖላቸዋል።

ራሱን ለመለወጥ ወኔ የሌለው ሰው፣ የሌላውን ውድቀት በመስማት የውስጥ ውድቀቱን ለመርሳት ይሞክራል። ይህም ራሱን መመልከት የማይፈልግ፣ ራሱን ይመለከትበት ዘንድ የሚያስችለውን እውነት-መስታወትን መቅረብ መቀበልም የማይፈልግ ያደርገዋል።

በአፉ “እድገት፣ ለውጥ፣ ነፃነት ናፈቀኝ” እያለ በተግባሩ ግን የሰውን አሉባልታ የሚጋት ትውልድ፣ ለውጥን ከየት ያገኛታል?

አባወራነት ወደ ውስጥ(ወደ ራስ) መመልከትና የገዛ ቤትን ቅጥር በጠንካራ የማይናቅና የማይደፈር ስብዕና ማጠርን ይጠይቃል።

ሐሜት ግን ወደ ውጭ ማየትና የሌላውን ጉድፍ መፈለግን፣ በእነርሱ ድካምና ጉስቁልና ራስን ማጽናናትን ሲያስከትል እርሱም ከእነርሱ ውድቀት የእኛን ልበጥፉነት ያብሳል።

ጆሮው በታዋቂዎች አሉባልታ ለተደፈነ፣ ዓይኑ በ”ምን ተባለ?” ለታወረ፣ ልቡ በእውነት ለሚመጣ ለውጥ ለሸፈተ ትውልድ—ድህነት እንጂ ብልጽግና፣ ውድቀት እንጂ ልዕልና የራቀው ሕልምም እንደኾነ የሚቀርበት ነው።

ራሳቸውን ከመቀየር ይልቅ የሰውን አሉባልታ ሰምተው በሚያድሩት ቤት ውስጥ ትውልድ ልቡ ሲቆሽሽ ይኖራልና ሰውነቱ በሥልጣኔው አይበለጽግም፤ ልጆች አይታነጹም፤ አባወራዊ ልዕልናም አይመለስም።

ሐሜት የሚጠላው በአንደበት ሳይኾን በድርጊት ነው። ራስህን የሚቀይር እውነት ስታገኝ ጆሮህን ስጥ፣ በልብህ አድምጥ፣ በሕይወትም ግለጥ፤ የሰውን ገመና ስታይ ግን ፊትህን አዙር! ለሐሜተኛው ትኩረት በመስጠት የትውልድ መጥፊያ ተባባሪ አትኹን።

ወንድምዓለም! ራስህን ታዘብ!

በዚህ ዓመት ብቻ የስንቱን አሉባልታና ሐሜት ሰማህ? አለመስማት ባንተ ሥልጣን ስር አልነበረምን?

Post a Comment

0 Comments