የአልጫ የእውቀት ጥጉ፤ "ሕግ ይጥበቅብን" ነው ወጉ!

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ

አልጫ ሕግ ሲጠብቅ "ደኅንነት" ይሰማዋል፤ ባርነቱን ማጽደቁን፣ "ገመድ ማሳጠሩን" ግን ይዘነጋዋል!

በአባወራው ዐውድ የአልጫን ትርጉም አስታውስ

🚨 አልጫ(1)፦ coward, ፈሪ፣

🚨 አልጫ(2)፦

✨ Demoralized, ወኔው የተሰለበ፣ ሞራል ያጣ፣ ጽድቅን ለመሥራት መስዕዋትነትን ለመክፈል(ቤዛ ለመኾን) ተነሳሽነት የጎደለው፤

✨ ማንነቱን(ታሪኩን፣ ተፈጥሮውን) የጣለ(የካደ)፣ ግራገብ፣ ዐለም የሰጠችውን ሳይመረምር የሚቀበል፤

✨ ጎስቋላ (በአካልም ኾነ በሥነ-ልቦና)፣ በስሜቱ በሰውነቱ ላይ መሠልጠን የተሳነው ድኩም፤

✨ ባርነት የተስማማው፣ የሚስማማው ከዚህም የተነሳ ዕጣ ክፍሉ የኾነ፣ ወዶ-ገብ ባርያ።

ትውልድ ተሰልቧል! አዎ! አባወራነትን በደም፣ በኃላፊነትና በሥነ-ምግባር መገንባት ያቃታቸው “አልጮች” የሕግን መጥበቅ እንደ ድኅንነት ሲቆጥሩት ይታያልና።

የውስጥ ጽድቅ የሌለው፣ በራሱ መቆም የማይችል፣ በወንድነት ቁና ልኩ ያልተሰፈረ፣ በአባወራነቱ ልዕልና ያልሰፈፈ ስብዕና ሁልጊዜም አባቱ ከሰጠው ጽድቅን ከሚፈጽምበት ነፃነቱ ይልቅ የሚነዳው “ጌታ” ይፈልጋል። ያ “ጌታ” ደግሞ ዛሬ “ሕግ” ተብሎ መጥቷል።

እነዚህ አልጮች (Demoralized) በሰሞኑ ከያዙት አጀንዳቸው በትዳር ቅድመ-ጋብቻ ሥልጠና “አስገዳጅነት” ብቻ አልረኩም። እንዲያውም የብቃት ማረጋገጫ (COC) ያስፈልጋል እያሉ ይጮኻሉ እንጂ።

እነዚህ ሰዎች እንደ እኔ ዓይንት “መሃይም” አልያም ብዙም የማይታወቁ አይደሉም! ይህቁንስ ማስትሬትና ዶክትሬት ጨብጠው እንኳን ጽሑፋቸው ንጥሻቸው ሳይቀር ላይክና ሼር የሚያገኙ “ተጽዕኖ ፈታሪዎች” መኾናቸውን እናያለን።

በዚህም ምን ቢማር የትውልዳችንን ማለጭ (demoralization) አልፎ ተርፎም በ”ጽድቅ” ስም ቅዱሱን ትዳር (ቤተሰብ) ለማፍረስ ከጠላት ጋር የተሻረኩ እጆችን እንታዘባለን!

ለምን?

ምክንያቱም የቤተሰብ መሪነትን አባወራነት (Patriarchy) ከፈጣሪና ከባህል የተቀበሉት ክብር አድርገው ስለማይረዱት፣ በመንግሥት ማኅተም የሚሰጥ-የሚነጠቅ “ፈቃድ” ይመስላቸዋልና።

አንድም የቅድመ ጋብቻው ሥልጠና አስገዳጅነት አልፎ ተርፎም የብቃት መመዘኛ ፈተናውን አስፈላጊነት የሚወተውቱት ራሳቸውን በወንድነት ልኩ ያላነሱ፣ የሚጠበቅባቸውን አባወራዊ ግዴታ ከመኝታ ቤት እስከ አደባባይ መወጣት ያልቻሉ አልጮች ለመኾናቸወሰ ምንም ጥርጥር የለኝም!

አንድም ይህንን ሕግ በትውልዱ ጫንቃ(ትከሻ) ላይ በመጫን ሕዝቡን የሚያስጨንቁ፣ ቀንበሩንም የሚያጠብቁቱ ለጠላት ያደሩት አስመሳይ፣ አድርባይ ሆዳደር ሊቃውንቱ እንደኾኑ አይጠፋንም!

እውን ሕግ ማጥበቁ ጥቅም አለውን?

ታሪክ ብናናግር፤ መጻሕፍትንም ብንጠይቅ ግን ሁለቱም ከዚህ በተቃራኒ ይመሰክራሉ። በሕግ ብዛት የዳነ ትውልድ የለም!

ምዕራባውያን ዛሬ የደረሱበት የማኅበራዊ ቀውስና የሞራል ዝቅጠት ምንጩ ይኸው መንግሥት፦

👉 የቤተሰቡን መሪነት ከአባወራው ነጥቆ፣

👉 ከቤተሰቡ ከቤታቸው እስከ መኝታ ምንጣፋቸው ዘልቆ፣

👉 በተራክቧቸው ፈቃድ ተሳትፎ፣

👉 በ”እኩልነት፣በሕግ መብትና ነፃነት” ስር ሸምቆ፣

👉 ትዳሩ ውስጥ ከሁለቱ(ባልና ሚስቱ) በተጨማሪ በሦስተኛነት ተሸንቅሮ

👉 ቅዱሱን ትዳር እርሱ ለሚፈልገው አልጫ፣ መረን፣ ባርያ ትውልድ ማምረቻ አድርጎት

👉 ሕግ በሚባል መስፈሪያ እቆነነ በመፈትፈቱ ነው።

ለ”እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” በሚል ሕግን አጠበቁ፤ ወንዶቻቸውን ሰለቡ፣ አባወራዎቻቸውን አሳደዱ መጨረሻቸው ግን የቤተሰባቸው መፍረስና የትውልዳቸው የማንነት መጥፋት ኾነ።

ሕግ በበዛ ቁጥር ጽድቅ የሚፈጸምባት ተፈጥሮአዊዋ ነፃነት ትሞታለች። ሕግ በበዛ ቁጥር አባወራነት ሚናው፣ ሰውነት ተፈጥሮም ይሸረሸራል።

አልጫ ሰው የራሱን ድክመት የሚደብቅበት፣ ተጠያቂነቱን የሚሸሽግበት ካባ ይፈልጋል። እንደ አባወራው ሃሳቡን፣ ቃሉን፣ ድርጊቱን አይገዛም፤ ተጠያቂነትን የሚፈራ አልጫ ነውና “የእኔ ናቸው” ብሎ አያውጅም!

በራሱ ሕሊና (ልቡና) መመራት ያቃተው፣ ሚስቱንና ልጆቹን በቅድስና በወንድነት ግርማ መምራት የማይችል ስልብ፣ መንግሥት መጥቶ “ሥልጠና ውሰድ” ሲለው እንደ ትልቅ ዕድል ጮቤ ይረግጣል።

“አባቴ የሰጠኝን ወንድነት መክሊቴን ቀብሬ፣ አባቶቼ ለዘመናት ከተገኙበት ከሚናዬ ተለይቼ፣ ዓላማዬንም ስቼ የትም የምባትል ሰነፍ ነኝና መሪ መኾንም አልቻልኩምና መንግሥት መሪ አድርጎ ይቅረጸኝ፤ እንደውም ይምራኝ” የሚል የባሪያ አስተሳሰብ አለው።

ራሱን ወደ መሪነት ልዕልና በአባቱ ጸጋ፣ በአባቶቹ ትውፊት ከማንሳት ይልቅ ዘወትር ምሪትና ስምሪትን ከሌሎች በተለይም በአስገዳጅ ሕግ መልክ ከመንግሥት የሚፈልግ ባርነትን ጠሪ ነው።

በዚህም የባርያ አስተሳሰቡ ራሱንም ኾነ ትውልድን በባርነት ቀንበር፣ “በእርጥብ እንጨት” አስጨንቆ ለሚገዛ ጠላት አሳልፎ የሚሰጥ ነው።

እርሱ ከመኝታ ቤት እስከ መስሪያ ቤቱ ሊወጣ(ጠብቆ ይነበብ) ባልቻለው፣ በዚያም ንቀትንና ጥላቻን በሴቷ ዘንድ ያተረፈለትን አሰስነቱን(አልጫ፣ ሰነፍ፣ ሰበበኛና ስሜታዊነቱን) በእንዲህ ዓይነት ሕጎች ፊት በማሽቃበጥ “ለእኩልነት፣ መብትና ነፃነት” የቆመ “ቅን፣ መልካም..ሰው” ለመባል በዚያም ያጣውን ክብርና መውደድ ለማግኘት ይዳክራል፤ ኾኖም ግን አያገኘውም!

ይኹን እንጂ ምስኪንነትም ኾነ አልጫነት መጨረሻቸው በአስመሳይነት የተጀመረ፣ በአድርባይነት የተጠናከረ፣ በሆዳደርነት ተለብጦ ያደገ ማንነታቸው በባንዳነት ሳይጠናቀቅ አይቀርም የምለው ለዚህ ነው።

የኢትዮጵያዊነት የመጨረሻው መሸሸጊያ ምሽጋችን “ቤተሰብ” ነው። ይህ ምሽግ ደግሞ የሚጠበቀው በቢሮክራሲና በሰርተፊኬት ሳይሆን በአባወራው ልዕልና ነው።

አባወራነት ደግሞ በሦስት ሺህና ከዚያም በላይ ባለፉ ዘመናት ባህልና እምነት የተገነባ እንጂ፣ በምዕራባውያን የፖሊሲ ኮፒ-ፔስት የሚገኝ አይደለም።

አልጫ ሕግ ሲጠብቅ ደኅንነት ያገኘ ይመስለዋል። ነገር ግን እያጸደቀ ያለው የገዛ ባርነቱን፣ ከአባቱ አንስቶ ለመንግሥሥተ የሚሰጠው መገረፊያ የእሾህ ጅራፉን እንደኾነ አያስተውልም።

ለትዳርህ፣ ለቤትህና ለሕይወትህ ከመንግሥት “የብቃት ማረጋገጫ” የምትጠብቅ ከሆነ፣ አንተ ገና ሳታገባ ተሰልበሃል!

ቤተሰብን ሕግ አያድነውም፤ በጽኑ ስብዕና የተገነባው አባወራ መሪነት እንጂ! ይህ ደግሞ አባታችን በአዋቂ ባሕርይው የሠራልን ሥርዓት ነው! ከዚህ ወዲያ መካሪ ጠላት፣ የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ እንጂ ማን ሊኾን ይችላል?


Post a Comment

0 Comments