ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

"የጾታ እኩልነት" ዘመቻው ስር የሰደደባት ጎረቤት ሀገር ኬንያ ከደቡብ ኮሪያ መማር አቅቷት፣ በጃፓን መመከርንም ንቃ፤ ትውልድ አጥፊ፣ ማኅበረሰብ አምካኙን መንገድ ተቀላቅላለች! ኢትዮጵያስ ትከተላት ይኾን ወይስ እንደ ማራቶኑ ትቀድማት?

ዛሬ "በእኩልነት" ስም "ሴቶችን ለማብቃት" የሚነገረው ስብከት፣ ዘመቻ፣ ንቅናቄ ተፈጥሮአዊውን የሴትነት ጸጋ ሚናም የሚንቅ፣ የሚጠላና የሚጥል ነው።

ሴቶቻችን ትምህርት፣ ሥራና ዝናን ብቻ እንዲያሳድዱ በዚህም "ከወንዱ እኩል" እንደሚኾኑ ተመክረው፣ በስተመጨረሻ የሕይወት አጋርና ልጅ አጥተው ብቻቸውን ሲቀሩ ደግሞ "ወንድ ያስፈልጋቸዋል፣ ብቻቸውን ሊሆኑ አይገባም" የሚል "ያዛኝ ቅቤ አንጓች" አስተያየት ማቅረብ ታዛቢ ማጣት ነው።

ይህ ተፈጥሮን ካለመረዳትና አርቆ ካለማሰብ፣ ማሰብም ካለመቻልና ካለመፈለግ የሚመጣ፣ ትውልድን የሚያጠፋ፣ ማኅበረሰብን የሚያመክን በሽታ ነው።

ኬንያ በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ የወሊድ መጠኗ በከፍተኛ ኹኔታ በማሽቆልቆሉ ቀዳሚነቱን ይዛለች። ለዚህ ውድቀት የዳረጓት ዋና ዋና ምክንያቶች ደግሞ፦

1ኛ የ"ቤተሰብ ዕቅድ"፦ በምዕራባውያን የሚረጨው የሥነ-ተዋልዶ ጤና ፕሮግራም እጅግ የተስፋፋባት መኾናኑ ትውልድን በማጥፋቱ፣ ማኅበረሰቡን በማምከኑ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶት አለው።

2ኛ የትምህርትና የሥራ ቅድሚያ፦ ሴቶች በለጋና በለምለም እድሜያቸው ትዳር መስርተው፣ ልጆችን ወልደው ሀገርን ከመገንባት ይልቅ "ትምህርትን ሥራንና ዝናን" እንዲያስቀድሙ በመገፋፋታቸው የወሊድ ዕድሜያቸው እንዲያልፍ ኾኗል።

3ኛ የወንድ ልጅ መዘንጋት፦ ማኅበረሰቡ "ሴትን ማብቃት" ላይ ብቻ በማተኮሩ፣ ቤተሰብ የሚመሠርት፣ የሚመራና የሚጠብቅ ጠንካራ በኢኮኖሚም የበለጸገ ወንድ እንዲጠፋ በመደረጉ የወሊድ መጠኑ ወደ ታች እንዲወርድ አድርጎታል።

ኬንያ ዛሬ ላይ የደረሰችበት የዝቅጠት ደረጃ ለኢትዮጵያ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው! በቅርቡ የኬንያ የጾታ ጉዳይ ሚኒስትር ዕጩ ስቴላ ሶይ (Stella Soi) እንደተናገሩት፦

👉 የበቁ ሴቶች ባል አጥተዋል! ዛሬ በኬንያ ቤቶች ውስጥ "የበቁ" (Empowered Women) የሚባሉ (ብዙ የተማሩ፣ ማስትሬትና ዶክትሬት የሠሩ፣ ነግደው ያተረፉ) ሴቶች የሕይወት አጋር (ባል) በማጣት ብቻቸውን እየቀሩ ነው፤

👉 ወንድ ልጅም ተዘንግቷል! ስለኾነም ለወንድ ልጅ ትኩረት የሚሰጡና ቤተሰብ እንዲመሠርቱ የሚያበረታቱ ፕሮግራሞች መቅረጽ የግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ ብለዋል።

ይህን ማለት "ድስት ጥዶ ማልቀስ" ነው። ወንድነትን ከከሰሱ፣ አባወራነትን ካንኳሰሱ፣ ቤተሰብን ካፈረሱና፣ ሴትነትን ካረከሱ፣ ሴቷን "ብቻሽን በቂ ነሽ" ብለው ካታለሉ፣ ውርጃና የወሊድ መከላከያን እንደምግብና መጠጥ ካለማመዱ በኋላ ማኅበረሰቡ ሲመክን "ባል ያስፈልጋታል፣ ወንድ ያስፈልጋል" ማለት ምን ያደርጋል? ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ!

"ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ" እንዲሉ!

እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ይህን የባዕድ አጀንዳ እኛም ሀገር እየተስፋፋ ሲመጣ ትወናው በ"ግብረ-ሰናይ" ተቋማት ብቻ ተወስኖ ሳይቀር፣ በቤተክርስቲያን ሊቃውንትም ጭምር እንደ መልካም ስብከት መቆጠሩ ነው።

"መብትና ነፃነት" በሚል ሽፋን የሚሰበከው በጾታ እኩልነት ተበርዞ የሚረጨው የቅድመጋብቻ ሥልጠና በክርስቲያናዊ የቤተሰብ አስተዳደር ውስጥ አባወራነትን የሚንድና ራስነቱን የሚሰርዝ እንክርዳድ፣ ነቀርሳ አምጪም ተውሳክ ነው!

አባቶቻችን በባህል፣ በእምነት፣ በትውፊት ያስረከቡንን የትውልድ "ራስነትን፣ ጠባቂነትን፣ እረኝነትን" ትርጉም በማጣመም፣ ቤተሰብን የመንግሥት ተቋም ልጆቻችንንም የመንግሥት ንብረት እየተደረጉ ነው።

በ"ግብረ-ሰናይ" ስም በተቋቋሙ ተቋማት የሚነዛው ይህ ተውሳክ ውጤቱ የታወቀ ነው፦

ልጅ-አልባ ማኅበረሰብ፦ ሴቶች በሥራና በዝና ተጠምደው የወሊድ ዕድሜያቸው እንዲያልፍ፣ እንዲመክኑ ማድረግ፤

የአሉላ ፓንክረስቱ ያንግ ላይቭስና መሰል ኁልቁ መሳፍርት የሌላቸው "የእኩልነት" አቀንቃኞች ልጆች ለጋ እድሜያቸውን ለትምህርት፣ ብሎም ለቅጥር ሥራ የሚያውሉበት ፖሊሲ እንዲቀረጽ መምከርና ማማከር፤

ወንድ ልጅ ሚናው እንዲጠፋና በሴቶች "ስኬት" ጥላ ሥር እንዲደበቅ በማድረግ የቤተሰብ መሪነትን ማጥፋት፤ አባት አልባ ትውልድ ማምጣት፤ አልፎ ተርፎም በውሃ ቀጠነ-ፍቺ ከቤቱ ማራቅ፤ በዚያም አባቱን የማያውቅ፣ የማይፈልግ፣ የማይናፍቅ፣ የማይወድ፣ ፈለጉንም የማይከተል ለባርነት የተመቸ መረን ትውልድ መፍጠር።

ጎረቤት ሀገር ኬንያ ዛሬ በጾታ እኩልነት፣ መብትና ነፃነት ሰበብ ሴቶቿ፦
👉 ተፈጥሮአዊ ጸጋቸውን ተጠይፈው፣
👉 የእናትነት ሚናቸውን ጠልተው፣
👉 የሚስትነት ወጉን ኮንነው
"ከወንድ እኩል ለመኾን" በተሰጣቸው ማብቂያ (empowerment) ትዳርን፣ ቤተሰብን፣ ልጆችን ጥለው ቢኼዱ የነገ ተስፋ ልጆቿን እያጠፋች፣ ማኅበረሰቧን እያመከነች መጣች!

ለኢትዮጵያም ንገሯት ከደቡብ ኮሪያና ከጃፓን አሁን ደግሞ ለቅሶና ዋይታው ጥርስ ማፋጨቱም ከቀረባት በቅርብም ከሚሰማት ኬንያ ትማር።

ሴቶችንም ኾነ ወንዶችን በተሰጣቸው ጸጋ፣ ሰውነታቸውን በሚበይነው እውነት እሴትም ማብቃት፣ ቤተሰብን ማጠንከር፣ ተፈጥሮአዊ ሚናዎችን ክብር መስጠት ብቻ ትውልድን ያድናል!

የመገናኛ ብዙኃኑ፣ የዩቲዩብ ሸቃላው፣ የመንፈሳዊ ሊቃውንቱ ይህንን ማንሳት አይፈልግም! እርሱ ባያነሳው እንኳ የሚያነሳውን ጋብዞ ትውልድ ይማርበት ዘንድ አይፈቅድም!

ያለጭንበት፣ አልጫ (demoralize) የኾንበት ጥግ፣ ባፍጢም የተደፋንበት ጥልቅ አእምሮ ከሚያስበው፣ ኢትዮጵያዊ ከትውፊቱ የተነሳ ይደርስበታል ተብሎ ከሚገመተው በላይ፣ ሩቅ፣ ረቂቅም እየኾነ ነው!


Post a Comment

0 Comments