(ክፍል ፪ ጠያቂ ትምህርት)
✍ ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ
በጳውሎስ መልዕክቶች ውስጥ በአንድ ወቅት ስሙ ከታላላቆቹ ጋር አብሮ ይጠራ ነበር። "አብሮኝ የሚሠራ ዴማስ" ይለው ነበር ሐዋርያው። ዴማስ የሰማያዊውን መንገድ ቃና የሚያውቅ፣ የቅዱሳኑን ፍቅር የቀመሰ፣ ምናልባትም ከተአምራቱ ማዕድ የተቋደሰ ሰው ነበር።
ነገር ግን፣ ታሪክ በአንድ አሳዛኝ ዓረፍተ ነገር ይደመድመዋል፦ "ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና።" (፪ ጢሞ. ፬፥፲)
ይህ ቃል ዛሬም ድረስ በቤተክርስቲያን ቅጥሮች ውስጥ እንደ ሰይፍ የሚቆርጥ ድምፅ ነው። ጳውሎስ የተናገረው የቤተክርስቲያንን ጩኸት ነው። ዴማስ የተለየው ጳውሎስን ብቻ አልነበረም፤ ዴማስ የተለየው ሰማያዊውን ተስፋ፣ የዘላለም ሕይወቱንና ያንን ያልተዘመረለትን የድል አክሊል ነበር።
ግን ቆይ ዴማስ ለምን ሄደ? ዓለም በአሁኑ ገጽታዋ አጓጓችው። የሮም ድምቀት፣ የሥጋ ምቾት፣ የሰዎች ጭብጨባና የጊዜያዊው ዓለም ሰላም ከእስር ቤቱ ቅዝቃዜና ከመከራው መንገድ ይልቅ ጣፈጠው።
ቤተሰቦቼ!! ዴማስ እኮ የእኛ መስታወት ነው።
▫ ስንቶቻችን ነን በፈተና ወቅት "አልቻልኩም" ብለን ወደ ኋላ የተመለስን?
▫ ስንቶቻችንስ ነን የጽድቅን መንገድ ጀምረን፣ በሰዎች ንቀትና ሽሙጥ፤ በድህነት መከራ ምክንያት የዓለምን "አሁናዊ" ጥቅምና ክብር የመረጥን?
ዴማስ ማለትኮ በነፍሱ ውስጥ የተከፈተውን የገነት በር ዘግቶ፣ ወደሚጠፋው ከተማ የተመለሰ ምስኪን ተጓዥ ነው።
ክርስቶስ በደሙ የጠራው ዴማስ፣ አሁን በጨለማው ዓለም ውስጥ ጠፍቷል። ጳውሎስ "ትቶኛል" ሲል በውስጡ ያለውን ሐዘን እንረዳለን። ነገር ግን ከጳውሎስ በላይ ያዘነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዴማስ የዓለምን አላፊ ወርቅ መርጦ፣ የክርስቶስን የማይጠፋ ጥበብ ጣለው።
ለመሆኑ እህቴ ለመሆኑ ወንድሜ ሆይ፤
▫ዛሬ አንተ ባለህበት የሕይወት ጎዳና ላይ ከማን ጋር ነህ?
ከጳውሎስ ጋር በመከራ ውስጥ ሆነህ ወደ ሰማይ እያየህ ነው? ወይስ እንደ ዴማስ "የአሁኑ ዓለም" አጓጉቶህ ወደ ኋላ እያፈገፈግክ?
የዴማስ ታሪክ ክፍል ፪ ትምህርታችን ነው—መጀመር ብቻ ድል አይደለም፣ እስከ መጨረሻው መጽናት እንጂ። የዓለም ብልጭልጭ ውበት እንዳያታልለን እንጠንቀቅ። እውነተኛው ባለድል የጀመረውን የሚጨርስ እንጂ፣ በበረሃ ላይ ተስፋ ቆርጦ ወደ ግብፅ ባርነት የሚመለስ አይደለም።
▫ አንተስ... ዛሬ ዴማስን ሆነህ ለዓለም ሰላምታ እየሰጠህ ይሆን? ወይስ ጳውሎስን ሆነህ "መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ" ለማለት እየተዘጋጀህ? ራስህን እየጠየቅኽ መልሱንም እያሰላሰልክ በክፍል ፫ አገኝሃለውና ጠብቀኝ።
0 Comments