አብዶ ማሳበድ "መብቱ"፤ ልብ አልባነቱ


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር 

ሰውነትን የሚበይነው አስተዋዩ "ልብ" በሆዳደር ሊቃውንቱ "ነቀርሳ አምጪ ተውሳክ ሃሳብ" ሲበከል ትውልዱ እብደት-መረንነቱን "መብቱ" ያደርገዋል!

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ውድቀት የሚጀምረው ቁሳዊ ድህነት ሲከሰት ሳይኾን፣ የሰውነት መለኪያ የኾኑት እሴቶችና ተፈጥሮአዊ ሕጎች ሲጣሱ ነው።

ዛሬ ላይ “ተራማጅነት፣ ዘመኒዊነት” በሚል ስም የሚነገዱ ዐዳዲስ ርዕዮተ ዓለሞች፣ የሰውን ልጅ ከራሱ ተፈጥሮ ጋር እያጣሉት ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ትውልዱን “ልብ አልባ” ወይም ማስተዋል የራቀው እያደረገው ነው።

ዓለማችን ላይ የሚታዩ፦

🚨 የጾታን ሥርዓትን “የአንባገነኑ አባወራ ፍረጃ” ብሎ መኮነን፣ ፅንስ ማቋረጥ (ውርጃ)፣

🚨 ግብረሰዶማዊነት እና የጾታ ለውጥ (Gender Transitioning) ያሉ ተግባራት “የግል መብት” እና “ነፃነት” በሚሉ ካባዎች ተሸፍነው ሰዎቹን ስለ ጤንነታቸው ከመመርመር ይልቅ ተቀባይነት እንዲያገኙ “በእኩልነት” እንዲታዩ ይደረጋል።

🚨 ሕይወትን የማስቀጠል የተፈጥሮ ግዴታን ጥሎ፣ በራስ ወዳድነት ስሜት የሌላን ንፁህ ፍጡር በመርዝና በመቀስ በጣጥሶ የመኖር መብቱን መንጠቅ (ውርጃ) ያውም በእናቱ “መብት” አልያም “የሥነ-ተዋልዶ ጤና” ሊባል አይችልም።

🚨 በፈጣሪ የተወሰነውን ጾታዊ ማንነት በሰው ሠራሽ ቀዶ ጥገናም ኾነ በሌላ ለመቀየር፣ እድገቱንም ለማስተጓጎል መሞከር ከፈጣሪ ጋር መጣላት ነው።

እነዚህ ድርጊቶች “መብት” ሳይሆኑ፣ የሰው ልጅ በራሱ ላይ ያወጃቸው፣ በተፈጥሮው ላይ ያመጸባቸው፣ ከፈጣሪው ጋርም የሚጣላባቸው የማያዋጡትና የማይጠቅሙትም ጦርነቶች ናቸው።

ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት “ሊቅ” ነን ባዮቹ ናቸው። የጥቅም ምርኮኛ የኾኑት እነዚህ ግለሰቦች፣ የተፈጥሮን እውነት በመቀየር “ነቀርሳ አምጪ ተውሳክ ትምህርት” በትውልዱ አእምሮ ውስጥ እየረጩ ይገኛሉ።

ትውልዱም ይህንን መርዝ እንደ ዘመናዊነት በመቁጠር፣ የራሱን ማንነት በሌላ በማንም አይደለም በገዛ እጁ እንዲያጠፋ እየተደረገ ነው።

ልብ ማስተዋል ሲያጣ፣ እብደት እንደ ሥልጣኔ ሲቆጠር፣ ማበድም “መብት ነው” ተብሎ በሃሳብ ገበያ የትውልዱን ልብ ያጠፋ ዘንድ ይሸጣል።

እንዲህ አቅሉንና ማንነቱን ያጣ ትውልድ ለባርነት የተመቸ ነውና ባርነቱን የሚፈልጉት አካላት ይህንኑ “እብደቱን” በ”መብት” ስም እንዲኖረው ያበረታቱታል።

ዛሬ ይህ ዓይነቱን እብደት የተመድ UN በበላይነት፣ የአውሮፖ ሕብረት በቀጣይነት፣ የአፍሪካውም በተባባሪነት እያስፈጸሙት ይገኛሉ።

የሰውን ልጅ ወደ ልቡ፣ ወደ አስተውሎቱ እንዲመለስ በዚያም ሰውነቱ ተጠብቆ እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ እነርሱ ለሚያስቡት ዓለምአቀፍ ባርነት (Globalization) ልቡን እስከዛሬ ከመጣበት እውነቱ፦ ወግና እሴቱ፣ ባህልና እምነቱ በርዘው፣ ደልዘውና ሰርዘው ያጠፉታል።

🚨 ይህንን ደጋግሜ ነገርኳችሁ በምቾት ቀጠና ውስጥ ኾኜም አይደል፤ ነገር ግን በገባኝ ልክ መናገር፣ መምከርና ማሠልጠን ግዴታዬ ስለኾነ እንጂ!

🚨 ይህ በመብትና ነፃነት ስም የሚሸጥልን ሸፍጥ ከፋፋይነቱ በዘርና በነገድ፣ በብሔርና በዘርሃረግ ከላይ ቀርቶ ማኅበረሰቡን በቡድን የሚከፍል አይደለም!

🚨 ይልቁንስ ታች የማኅበረሰቡ ሥሪት፣ የቤተሰቡ መሠረት ወደ ኾኑት ሁለቱ አካላት ወንዱና ሴቷ መካከል ገብቶ ጥላቻን በእኩልነት መብት፣ ነፃነትና ጸረ-ጾታዊ ጥቃት ስም ይዘራዋል እንጂ!

ልብ አድርጉ! ሁለቱ ቤተሰብ ሊመሰርቱ፣ ልጆች ሊወልዱ፣ በዝተውም ማኅበረሰብ ሊገነቡ፣ ትውልድ ሊያንጹ፣ ድንበር ከልለው ሀገር ሊሰይሙ ያላቸው ወንዱና ሴቷ በጥላቻ ሲለያዩ ለጠላት ሰርግና ምላሹ ነው።

ስለ ጾታ እኩልነት፣ መብትና ነፃነት እንዲሁም ጸረ-ጾታዊ ጥቃት ሲነግሯችሁ ስትሰሙትም “ቅን ሀሳብ” ይመስላችኋል፤ ውስጡ ግን በማር የተለወሰ መርዝ ነው። በዚህ ማር ከተበጠበጠው ለጠጡት ልባቸውን የሚያጠፋ፣ የጠፋው ልባቸውም ጥፋታቸውን የሚያስከትል ኾኖባቸዋል።

ሰውነትን የሚበየነው በልብ ውስጥ ባለው እውነትና በተፈጥሮአዊ ሥርዓትም ነው። ከነዚህ እሴቶች የተፋታ ትውልድ መጨረሻው ጥፋት ነው። (ስለ እንግሊዝ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ጃፓን የጻፍኩትን ተመልከት)

እብደቱን “መብቴ ነው” ብሎ እንዲቀበል፣ ተቀብሎም እንዲያምነው፣ አምኖም እንዲኖረው የተበረታታ ትውልድ፣ እውነትን የሚያይበት አስተዋይ ዐይኑና መዝኖ የሚይዝበት ልቡ ስለጠፋ ማንም ሊታደገው አይችልም።

ስለኾነም፣ ከዚህ “የአስተሳሰብ ነቀርሳ” ለመዳን ወደ ተፈጥሮአዊው ማንነታችን፣ ወደ ቀደመው ማስተዋላችን እና ወደ “ልባምነታችን” መመለስ ብቸኛው አማራጭ ነው። ማስተዋል ለተለየው ተሰውልድ “ነፃነት” ባርነት ነው፤ ተፈጥሮን የካደ “መብት” ደግሞ እብደት!

ይኹን እንጂ በምዕራባውያን ዘንድ ልባቸው ጠፍቶ ያበዱ፣ አብደውም ሰውነታቸውን ተልትለው ጾታ የቀየሩ፣ ይህንንም ደግሞ የሚያስተምሩ ሰዎች “እብድ” አይባሉም!

እንዲህ የሚላቸው ማንምም የዚያ የ”አንባገነኑ ጾታና ሥርዓተ-ጾታ እንዲህና እንዲያ ነው” ባየለ አባወራዊ ሥርዓት አራማጅ ብለው ይወርፉታል እንጂ!

ይህ ዓይነቱ ልብን አጥፍቶ ትውልድን የማሳበድ “መብት” በእኛም ዘንድ ስር እየሰደደ ነው!


Post a Comment

0 Comments