✍ እስራኤል ዘነፍስ | ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን
ለጤናዎት እንደምን አሉ? እኔ በመድኀኔዓለም ቸርነት ደህና ነኝ። እርስዎ ካስተላለፉትና ካስተማሩት ትምህርት አንፃር ከአንድ ሰው ጋር ችግር ገጥሞኝ ምን አልባት ከተቻለ በአንድ ትምህርተዎ ማስተካከያ ቢያደርጉበት ከሚል አንፃር ነው። ጉዳዩም አዲስ አበባ ውስጥ በታክሲ በአንድ ወንበር ከአንድ ሰው ጋር ተቀምጠን ስንጓዝ አብሮኝ የተቀመጠው ሰው ጉንጩ ተወጥሮ በመስኮት ልብስ ፊቱን ደብቆ እንደፍየል ጫት እየበላ ነበር።እኔም መንገዱ ረዥም ስለነበረ ሰላም ወንድሜ እንዴት ነህ? አልኩት ወሬ ለመጀመር ያክል ብዬ! እሱም ደስ በማይል ሰላምታ ከመለሰልኝ በኋላ የሆነ ነገሩ ሲናደድ አየሁት! እኔም እንብላ እኮ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው እንብላ አይባልም እንዴ? ስለው የታፈነ ብስጭቱ ገነፈለና አሁን አንተ ጫት ትቅማለህ? እ..እንዲ የምትለኝ ነው ወይስ እያሾፍከኝ ነው! ሲለኝ ታክሲ የተሳፈረው ሁሉ በድንጋጤ ዞሮ አየን!ጫት እንደማልበላ እንዴት እንዳወቀ ግን እኔ እጃ ያናገረኝ ርኩስ መንፈሱ ሳይሆን አይቀርም(መቼም ጫት የሚያስበላ አጋንንት ነው)!! እኔም ቀጠልኩና ኧረ ወንድሜ ተረጋጋ ሺ አልኩት የሆነ ብሶት በውስጡ ያለው ስለመሰለኝ! ከቆይታ ዝምታ በኋላ እኔ ግን እንዴት ጫት እንደማልበላ አወቅክ አልኩት? እሱም እንዴ! ዛሬ ቀኔ አይደለም እንዴ!? አለና አዎ አንተ እንዲሁ ታስታውቃለክ አይደለም ጫት ልትቅም የጫት ተቃዋሚ ፓርቲ ነው የምትመስለው! ሲቀጥል ደግሞ ጫት እንቃም እንጂ እንብላ አይባልም አለኝ!! እኔም ሁሉም ያው ነው አዘልክም አቀፍክም ያው ተሸከምክ ነው! ብትበላውም ብትቅመውም ያው በአፍህ ውስጥ በጥርስህ ነው የምታኝከው ስለው ታክሲ ውስጥ ያለው ሰው አብዛኛው ሳቀ አንዳንዶች ደግሞ እኔን "ለምን የሰውየውን ምቾት ትረብሻለህ"? በማለት ሊጣሉኝ ዙሩን አከረሩብኝ (መንፈሳቸው ሊያጠቃኝ ተባበረብኝ ማለት ነው)። የተወሰነ ፀጥ ብዬ መዝሙር 90ን ባልጠራበት ኑሮ ከባድ ነበር!! የምለውን ከጨረስኩ በኋላ ጫት እየበላ ያለውን ሰው በዚህ ሁኔታ ማውራቱ ጥሩ እንዳልሆነ በማሰብ በሌላ ቀን ጫትና ሱስ ጥሩ እንዳልሆነ እንድንመማር በማሰብ የስልክ ቁጥርህን ልትሰጠኝ ትችላለህ? ስለው ተናዶ ፎከረና ከመቀመጫው ተነሳ! በቃ ዛሬ ቀኔ በዚህ ሰው ምክንያት ተበላሸ አለና ከአሰበው ቦታ ሳይደርስ ወራጅ አለ አለ! አሁን እዚህ ጋ ነው አባ ገብረ ኪዳንን የጠቀሰልኝ! "ሲጀመር እናንተ የዘመኑ ወጣት አስተማሪ ነኝ ባዮች ታካብዳላችሁ! እኔ የምከተላቸው እውነተኛ መምህሬ አባ ገብረ ኪዳን ናቸው።እሳቸውም ስለቡና ተጠይቀው መልስ ሲሰጡ እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉም መልካም ነው ብለው አስተምረዋል። አሁንም አንተን ልጠይቅክ! ጫትን የፈጠረው ማን ነው?" አለኝ! እኔም ፀጥ አልኩኝ! እ..መልስልኛ? አለ በድጋሜ! እኔም ከመቅፅትበት ትምህርቱን እንዴት እንደተረዳው ግራ ገብቶኝ ወደ አባ ገብረኪዳን ሀሳቤን በመላክ ዝም አልኩት!! "አየህ መልስ የለክም አለኝ።ቀጠለና እኛ እናንተን ወጣት ወጠጤዎቹን አንከተልም! እሳቸው ቡና ይጠጣል ካሉ ጫትም ይቃማል period!" አለኝና ቅጠል የወጠረውን ጉንጩን አሳይቶኝ እኔን እየተራገመ መድረስ ያለበት ቦታ ሳይደርስ ወረደ!
አሁን የእኔ ጥያቄዎች፦
1ኛ ይሄን ልጅ እና መሠሎችን ከእርስዎ ትምህርት አንፃር ምን አድረገን ምን ብለን ነው የምንመልሳቸው?
2ኛ በዚያው ስለቡና ባስተማሩበት video ላይ እርስዎ ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር "ቡና አይጠጣም የሚለው ድርሳነ ጽዮን ላይ እና ዜና ሥላሴ ላይ ተጽፏል! አዎ ተጽፏል" አሉና ቀጥለው ደግሞ " ለምሳሌ አሉና አንድ ሰው በእንጀራ ቢስትና እንጀራ አሳሳተኝ ቢል እኛ እንጀራ አንበላም ልንል ነው? አንድ መነኩሴ በሴት ምንኩስናውን ቢያፈርስ ሴት ሀጢያት ናት ልንል ነው? አንድ ሴት መነኩሴስ በወንድ ብትሳሳት ወንድ ሀጢያት ነውና አንነካም ልንል ነው? እንደዚህ ማድረግ አይገባም " ብለው አስተምረዋል። አሁን ከእርስዎ ትምህርት አንፃር እኔ የሚገባኝ ድርሳነ ጽዮንን የደረሱት አባት ቡና አይጠጣም ያሉት እርሳቸው በቡና ስለተሳሳቱ ነው እያሉን ነው!! ዜና ሥላሴን የደረሱት አቡነ ዘርዓ ብሩክና አባ ጊዮርጊስም ለስም መጠራታቸው ምስጋና ይሁንና እነሱም ቡና አይጠጣም ያሉ በቡና ስለሳቱ ነው እያሉን ነው ማለት ነው!!! እንግዲህ እኔ ቀጥታ እርስዎ የተናገሩትን ነው የፃፍኩት! ማረጋገጫ video አለኝ! ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? እሺ እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የደረሱት ድርሳነ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ላይ ቡና እንደማይጠጣ ድርሳነ ጽዮንን ጠቅሰው በእለተ ሰንበተክርስቲያን የሚነበበው ላይ ጽፈዋል።እና አሁን አባ ጊዮርጊስ የፃፉት በቡና ስለሳቱ ነው ማለት ነው? ኧረ በፍፁም አይደለም! ቡና መጠጣት የሌለበት ርኩስ ስለሆነ እንጂ!! ሌላም ቅዱስ ልጨምር ንዑድ ክቡር ቅዱስ አባታችን አቡነ ዘርዓ ብሩክ በቅዱስ ገድላቸው ላይ የትንባሆ ቅጠል በጭስ መልክም ይሁን አፍልቶም ይሁን የሚጠጣ ቢኖር እርሱ የተረገመ እንደሆነና እጣ ፈንታውም ከአጋንንት ጋር የገሀነም እሳት እንደሆነ ተጽፏል።ይህንንም ቃለ ውግዘት ያስተላለፉት እራሳቸው አቡነ ዘርዓ ብሩክ ናቸው። እና ከእርስዎ ትምህርት አንፃር አባታችን ይህንን የተናገሩት ሲጃራ ትንባሆ አጭሰው ስለተሳሳቱ ነው ማለት ነው?? በዜና ሥላሴ መጽሐፋቸው ላይም ቡና ማንም እንዳይጠጣ አውግዘዋል።እና አባታችን ይህንን ያሉት በቡና ስለሳቱ ነው? ከእርስዎ ትምህርት አንፃር? እሺ! መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል በድርሳነ ራጉኤል ላይ ለንጉሡ ልብነ ድንግል ሲናገርና ሲያስረዳ ቡናን የዲያቢሎስ መርዝ ያለበት ርኩስ የረከሰ እያለ ቡናን በተደጋጋሚ ይጠራዋል። ማስረጃ በፎቶ ድርሳነ ራጉኤልን ከታች በቀይ ቀለም ያደረግኩትን ይመልከቱ! እሺ! ቅዱስ ራጉኤል አሁን በቡና ስቷል ልንል ነው? ከእርስዎ ትምህርት አንፃር? ቅዱስ ራጉኤል መልአክ ነው መንፈስ ነው ሥጋና ደም የለውም አይበላም አይጠጣም ስለዚህ ቡና አሳሳተው ልንለው አንችልም። እና ይሄን ትምህርተዎን ተመልሰው ማስተካከያ ቢሰጡበት አይሻልም ወይ? ሰው እየጠፋበት ስለሆነ ለማለት ነው!! በነገራችን ላይ ምዕመናን ማወቅ ያለባችሁ ቡና አይጠጣም የሚለው ተዓምረ ማርያም ላይም ተጽፏል! (ከትልቁ ተዓምረ ማርያም ወይም ባለ402ቱ ላይ ነው ታዲያ!! ትንንሾችን አይተህ የለም አልተፃፈም ውሸታም እንዳትለኝ ብዬ ነው!)
3ኛ/ እንዲህ ብሎ መናገርስ ድርሳነ ጽዮንን ዜና ሥላሴን ድርሳነ ራጉኤልን ሌሎችንም ቅዱሳን የቤተክርስቲያን መጽሐፍቶችን የደረሱትን ቅዱሳን አባቶቻችንን መሳደብ አይሆንም ወይ? ቡና አይጠጣም ብለው ያወገዙትን መጽሐፍትስ ዜና ሥላሴን: ድርሳነ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስን: ድርሳነ ራጉኤልን : ተዓምረ ማርያምን ከእርስዎ ትምህርት አንፃር እነዚህን መጽሐፍት ምን ሊያደርጓቸው አስበዋል?
4ኛ) እርስዎ እንግዲህ እንደ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖታችን በሕዝቡ ዘንድ እንደመጨረሻ ተጠያቂ ነዎት ተብሎ ይታሰባል! ስለዚህ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖታችን በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ የሥርዓት ጥሰት እየተካሄደባት እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ችግር ውስጥ ስትገባና ሥርዓቷ ሲጣስ የማይገስፁና እውነተኛውን የማይናገሩ ለምንድን ነው? ለምሳሌ በትግራይ መንበረ ሰላማ ብለው ሲተክሉ በኦሮሚያ ደግሞ መንበረ ጴጥሮስ ተብሎ ሲተከልና ምዕመኑ ግራ ሲገባውና ሲጨንቀው መሄጃ ሲያጣ እንደአንድ የቤተክርስቲያን ሊቅ ለምን እውነቱን ለምዕመኑ አይናገሩም? ለምንስ አይገስፁም? ፍራቻ ነው እንዳልል እርስዎ መንኩሰዋል ዓለምን ንቀው በቃኝ ብለዋል ስለዚህ ምን ያስፈራዎታል??
ማስታወሻ: እዚህ ላይ የተዋህዶ አርበኛውን አባታችን አለቃ አያሌውን ማስታወስ ግድ ይለናል! እሳቸው እኮ በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ጊዜ ነበር እንደ ሊቅነታቸውና እንደሀላፊነታቸው ክፉዎችን ሳይፈሩ ለቤተክርስቲያን ሲሟገቱ ኑረው በክብር ወደ አምላካቸው የተጠሩት!! እና የአሁኑዎችስ እሳቸውን አብነት ማድረግ አይገባችሁም ነበር ወይ?? በዚህ ዘመን ካሉት ረዥም የክብር መጠርያ ስም ከተቀጠለላቸው የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሚሟገትላት ማን ነው? አንድም አለመኖሩ እጅግ ይገርማል ብቻ ሳይሆን ያስለቅሳል ጭምር!! ሁሉም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከጳጳስ እስከ ምዕመን ሁሉም የራሳቸውን መሸቀያ ዩቱዩብ /youtube ከፍተው ሰብስክራይብና follow አድርጉ ማለታቸው የዘመናችን አሳዛኝ ድራማዊ ክስተት ሆኗል! ያሳዝናል እረኛ መጥፋቱ!
ነገር ግን ምዕመናን ቤተሰቦቼ አይዟችሁ ተፅናኑ! ለቤተክርስቲያን ከአምላኳ ፍርድ ስለተፈረደላት እነሆ መከራው ዓለምን እያበጠራት ነው!!
የተዋህዶ ልጇ እስራኤል ዘነፍስ ነኝ!
0 Comments