ለዘመናት የተኮነነው መልካሙ ተፈጥሮ “ወንድነት”




ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   
ዘመናችን የረሳቸው ወንዶቻችን፣ እየጠፋ የመጣው ወንድነታቸው፤ እንደ መፍትሔ የሚቀርብላቸውም የምስኪን እና የአልጫ አርአያ!

ወንዶቻችን ምንም በማያውቁት፣ ባላሰቡትም ጥፋት ገና ከልጅነታቸው ወንድነታቸው በዝባዥ፣ ጨቋኝና በዳይ እንደኾነ ደጋግመው በመስማት ያድጋሉ።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ወንድነታቸውን፣ ወንድ መኾናቸውን፣ በዚያም የተሰጣቸውን ሊያውቁበት ከተሰጣቸው አባት በስሜት(emotionally) ከመኮነኑ የተነሳ ወይንም በአካል በፍቺ ሊያውቁት ሲጀምሩ እንዲለዩ ይደረጋሉ።

የተረሳ፣ ያለጥፋቱም የተጠላ ትውልድ!

በዚህም በተፈጥሮ በውስጣቸው የተቀመጠው የወንዴ እድገ ንጥር(testosterone) ተፈጥሮአዊና ጤናማ መልካምም በኾነው ጎኑ ሲጨምር እንዴት ሊገለጡበት እንደሚገባ የሚያሳያቸው በማጣት ይቅበዘበዛሉ።

ከእናታቸው፣ ከመምህራኖቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ተጋጭተው በሚገለሉበት ወቅት ሲሰሙ የኖሩትን፣ የዋሉትን፣ አሁንም የሚሰሙትን፣ እናታቸው ቤተሰቡና ማኅበረሰቡ የሚደግመውን “ወንዶች አስቸጋሪዎች ናቸው፣ በዳይ ጨቋኞች፣ ደፋሪዎችም እንጂ...” የሚለው በጆሮዋቸው ያቃጭላል።

“ግን ለምን በዝባዥ፣ ጨቋኝ፣ ደፋሪና አስቸጋሪ አድርገህ ፈጠርከን...?” ጥያቄያቸው ነው።

እኔ ግን ወላጅ አባታቸው እንዲህ እላቸዋለሁ “ልጆቼ እንዲያ አልተፈጠራችሁም! በውስጣችሁ ያለ ጥንካሬያችሁ፣ ድፍረታችሁ፣ ፍጥነታችሁ፣ ጀብደኝነታችሁ፣ ኃይለኝነታችሁ... ሁሉ በራሳቸው መልካም የኾኑ፣ ጽድቅም ልትሠሩባቸው ተሰጧችሁ እንጂ...”

ልጆቻችን አስታዋሽ የላቸውም! የወንድም የሴትም ልጅ አባት ነኝና የአጉል እኩልነት፣ መብትና ነፃነት ጾታዊ ጥቃትም የጥፋት ፍላጻ ከልጆቼ አርቆኛልና ሕመማቸውን በመጠኑ አውቀዋለሁ ያሳዝኑኛል!

እነርሱ ብቻ አይደሉም በየቦታው፣ በየመንደሩ፣ በየትምህርት ቤቱ የማያቸው በቅርብ ወንድነትን የሚስልላቸው ታላቅ እንደሌላቸው የተረዳኋቸውን ወንዶች ሳይም ጭምር እንጂ!

ማንም እያዘነላቸው አይይደለም!

ወደ ቤተክርስትያንማ ጠጋ ካሉ መንፈሳዊ ለመኾን ሴት መኾን ወይም የሴት ጠባይ መያዝ እንዳለባቸው በግልጥ እየተነገራቸው እንከፍ፣ ንክር ምስኪን፣ ጃንደርባና አልጫ የሚኾኑትን ቤት ይቁጠራቸው።

ከዚህም የተነሳ ቤተክርስትያን (የኢኦተቤ) ወንዶቿን አልጫ በማድረጉ ሂደት ጠላት ከጠበቀው በላይና በሰፊው ሄዳበታለች አድርጋቸዋለችም!

ስለወንድነት የሚናገር፣ የሚነግረን ማንም የለም! ያሉትም ሸቃላ ሚዲያዎች “መቆም ያቃታቸው ሊወድቁ አንድ ሐሙስ የቀራቸውን ለራሳቸው መኖር አቁመው ለሌሎች የሚኖሩትን” አልያም ምንም የወንድ አቋምና አቅም፣ ወኔና ደም የሌላቸውን ምስኪኖች ያመጡላቸዋል!

ለምን?

እውነተኛው ወንድነት፦ ቆራጡ፣ ቆፍጣናው፣ ጀብደኛው፣ ጠንካራው፣ ኃይለኛው፣ ደፋሩ... ወንድ ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት በዝባዥ፣ ጨቋኝና በዳይ ተብሎ ተኮንኗልና፤ አንድም ሴታቆርቋዦቹን (feminists) የሚፈሯቸው አልጮች ናቸውና።

በዚህ ውስጥ ታዲያ በሰዎች፣ በዘመድ አዝማድ ተከበው፣ ነገር ግን እነርሱን የሚመስል፣ በውስጣቸው የሚፈላውን አባታቸው ያስቀመጠላቸውን ወንድነት ወኔያቸውን የሚያጸድቅላቸውን አባት ያጡ፣ የሚናፍቁ፣ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ልጆቼ ድምጽ ይሰማኛል!

ብቻቸውን መኾን የፈሩ! በክስና በመኮነን የደከሙ የሀገሬ ልጆች ድምጽ! እናንተስ አይሰማችሁም? እንዳይጠሏቸው በጥቅም የያዙዋቸው እንዳይወዷቸው መልክ ምሳሌያቸውን (አባታቸውን፣ ወንድነታቸውን) የቀሟቸው ሰዎች መካከል ኾነው ሲቃ እየተናነቃቸው የሚጮኹ ድምጻቸው ግን የማይሰማ የልጆቻችን ድምጽ!

እንዲህም ይላል፦አባ የት ነህ? አለህ?

እኔ፦አለሁ ልጆቼ! እየመጣሁ ነው! “እርሱ ቢፈቅድ ብንኖር አያችኋለሁ” ወንድነትንም አሳያችኋለሁ!

አደራ የተባሉት “ሊቃውንት” በጥቅም ለውጠውን ቢተዉን፣ ለተኩላ ቢጥሉንም፤ መቼም የማይተወን አባት አለንና ደስ ይበላችሁ!

(ይህን ስጽፍ የሚሰማኝን ስሜት ገምቱ!)

Post a Comment

0 Comments