አስማት ከየት መጣ! እንዴትስ ተጀመረ!


✍ ቲና በቀለ | ኢትዮጵያ አውታር       

(ክፍል-ሁለት)

የጥንቱ አለም እውቀት በግልቡ አለም እንቶ ፈንቶ ተቀብሩዋል። የጥንቱን አለም ስልጣኔ ቆፍሮ ለማውጣት አያሌ ሳይንቲስቶች ቆላ ደጋውን በመቆፈር ላይ ናቸው። ከጥልቅ ባህሮች በታች አያሌ ጥንታዊ ከተማዎች ተገኝተዋል። የሰው ዘር ይኖርባቸዋል ተብለው በማይገመተው እልም ባለ በረሀ ውስጥ በቁፋሮ አያሌ ረቂቅ ህንጻዎች  እየተገኙ ናቸው።

ከነዚ ቁሳዊ ስልጣኔዎች ጀርባ የነበሩ አእምሮዋዊ ስልጣኔዎች ግን ሊደረስባቸው አልተቻለም። ለምን ቢባል ፈላጊዎች ጥቂት ብቻ ስለሆኑ ነው።

በመላው_ዩኒቨርስ ውስጥ እጅግ ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ወይም ጥቂቶች ብቻ የሚያተኩሩበት ወይም የሚያጋጥማቸው ግራ አጋቢ ነገር አለ። 1% ለሆኑ የአለማችን ክፍሎች ብቻ የሚያጋጥማቸው እንግዳ ነገር እንዳለ ሊቃውንቶቻችን ደርሰውበታል።

ሁሉም እንደየ አቅሙ እየጠለቀ በሄደ ቁጥር የሚያጋጥመው እንቆቅልሽ ሞልቱዋል። በተለይም አሁን ሰለጠንኩ በሚለውና በየቀኑ የሚለዋወጠው ቴክኖሎጂ አእምሮውን አዝሎ ናላውን ያዞረው ትውልድ ቀደም ባሉት ጊዜያት ቀደም ባሉት ጊዜያት ተወግዘው የተለዩትን እውቀቶች ገብቶትም ሳይገባውም አውግዞ እርሱም ከተለያቸው ቆይቱዋል። ጥቂቶች ግን ጠልቀው ከመቆፈር አልተቆጠቡም። ከእነዚ ውጉዝ እውቀቶች ውስጥ አስማት አንዱ እና ዋንኛው ነው።

ከምናየው አለም ጀርባ ባለው ድብቅ አለም ውስጥ ያለው ድብቅ ሀይል አስማት ነው-ቃል። ድብቁ ሀይል በቁጥጥር ስር ሲውል አስደናቂ ተአምራቶች ይሰራል። ይህም ሀይል በቃላት ውስጥ ይገኛል።

ክርስትያን ለሆነ ሰው  "ቃል ስጋ ሆነ" እና 'የከንፈርህን ፍሬ ትበላለህ" የሚሉትን ቃላት አይረሳም። ሰማይና ምድር ከሰው ልጅ በቀር የሚታየውን የማይታየው የተፈጠረው በቃል ነው።

አስማት ሌላ ምንም አይደለም ይሄው ነው። የስሞች ጥርቅም። የስም ብዜት። የቃላት ስድር። ነገር ግን ክሌሽ ያልሆኑ ለብዙዎች ያልተሰጡ ቃላት።

አስማት በመጸሀፍ ቅዱስ ውስጥ ለማን እንደተሰጠ ተብራርቶ ተቀምጡዋል። አዳምና ሄዋን አቤልና ቃኤልን ወለዱ። ቃኤልም አቤልን ገደለው። በአቤልም ምትክ ሴት ተወለደ። ከዚህም በዋላ የአዳም ልጆች በሁለት ተከፈሉ። ሴታውያንና ቃኤላውያን ተብለው። ሴታውያን ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ መሰዋዕት እያቀረቡ ሲኖሩ ቃኤላውያን ግን ወደ ሌላ ሀገር ተሰደዱ።

ቃኤላውያን ሂወታቸውን ለማሰንበት ሲሉ ተፈጥሮን በመመራመር ለቁስላቸው እጽዋትን ቀመሙ። ለጠላቶቻቸው ሰይፍን እና ጎራዴን፣ ቢላዋና ሳንጃን፣ ቀስትና ፍላጻን አበጁ። ለሰብላቸው ዩኒቨርስን ክዋክብትን ተመራመሩ። የሴቶቻቸውን እጆች ሳይቀር እንሶስላ መቀባት የጀመሩት እነርሱ ናቸው። ለአንገታቸው ጥቁራትን ንቅሳትንም።

በዚህ ጊዜ ሴታውያን በቃኤላውያን ስልጣኔ ተሳቡ። ቀስ በቀስም ተደባለቁ። በዚህም ፈጣሪ ተቆጣ። የጥፋትንም ውሀ አመጣ። በጥፋት ውሀ ጊዜ ኖህ ልጆቹን ሰብስቦ ወደ መርከቡ ሲጭን የኖህ ልጆች ሚስቶች ጥበቡን ደብቀው ይዘው ወደ መርከቡ ገብተው ነበር። ከጥፋት ውሀ በኋላ የቀጠለውም በዚሁ ምክንያት ነው።

ከቃኤል ዘሮች ውስጥ ተፈጥሮን በመመራመር የአስማትና የምድር እውቀት ባለቤት የሆኑት ሊቃውንት ረኦይት የተባሉት ዘሮች ናቸው። በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ስለነዚህ ረአይት ስለተባሉት ህዝቦች አኑዋኑዋር  ተተርኳል። በጥንቱ ኢትዮጲያ ሰሜናዊ ክፍል ይኖሩ የነበሩ የኩሽ ግንዶች ናቸው።

የመጸሀፍ ቅዱሱ ሙሴ ከነሱ ሰዎች ጥበብን እንደተማረ ይነገራል። የግብጽ አስማተኞች ብትራቸውን ወደ እባብ ሲለውጡ እሱም ለውጡዋል። ሌሎች ታላላቅ አስማቶችን ሲያደርጉም አድርጉዋል። ልዩነቱ የእርሱ ጥበብ ከፈጣሪ እነሱ ጥበብ ከምድር መሆኑ ነው።

ስለዚህ ቁሳዊው አለም የቃኤላውያን ነው። ማለትም ህንጻ መገንባት ጦር መሳሪያ መስራት፣ ስእል መሳል፣ ጽሁፍ መጻፍ፣ ሽመና እና ብረት መቀጥቀጥ አሁን የምናያቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጭምር የቃኤላዊያን ጥበብ ነው/ናቸው። እንደ ማስረጃም መጸሀፍ ቅዱስ ይነግረናል።

እነዚህን እወቀቶች አሁን ያለው ዓለም ይጠቀምባቸዋል። ሌላውን እውቀት ግን፣ገሚሱን አቃጥሎታል፣ ገሚሱን አውግዞታል። ከዚህ ውስጥ አስማት አንዱ ነው። በተለይ የክርስትና እምነት ከመጣ በኋላ አያሌ የአስማት መጸሀፍት ተቃጥለዋል። ይህንንም በክፍል አንድ አውርተናል። በዛን ጊዜ በነበረው የገንዘብ ተመንም አንድ የአስማት ጥቀል 50 ሺህ ዲናር ይሸጥም ነበር፣ ይህ ማለት እንዲህ አስሉት ክርስቶስ እንኳን የተሸጠው በ30 ዲናር ነው!

ከዛ ጊዜ ጀምሮ በየሀገሩ ከግብጽ እስከ ኢትዮጲያ የተቃጠሉትን መጸሀፍ መቁጠር ያዳግታል። ነገሩን በጥልቅ የመረመረ ግን አንድ ነገር ይገነዘባል። አሁን የምናየው አለም ሁሉ የተሞላው በቃኤላውያን እውቀት መሆኑን ነው። ከትንሹ የህክምና  ጥበብ እስከ ግዙፉ የህዋ-ምርምር የተወገዘው እውቀት ቱርፋቶች ናቸው።

ነገሩን ከስሩ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ይህን በቀላሉ መገንዘብ አይከብዳቸው።

አስማት ጥቁር ነጭ እና የተፈጥሮ በመባል በሶስት ፈርጅ አለው። ነጩ ለመልካም ጥቁሩ ለክፋት የሚውል ነው። እሳትን እና ውሀን ለበጎም ለመጥፎም እንደምንጠቀመው ሁሉ አስማትንም እንዲሁ መጠቀም ይቻላል።

ይቀጥላል!
            
ማጣቀሻ፦ መፀሀፈ-ሄኖክ


Post a Comment

0 Comments