የፌስቡክ እና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ፣ ተጠቃሚዎች ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላም ቢሆን የእነሱን ድምፅ፣ የአጻጻፍ ስልት እና ጠቅላላ ባህሪ በመኮረጅ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ "በህይወት" እንዲቆዩ የሚያደርግ አዲስ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሆኗል።
ቴክኖሎጂው እንዴት ይሰራል?
እ.ኤ.አ. በ2023 የተመዘገበውና በቅርቡ የፈጠራ መብት (Patent) የተሰጠው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በመጠቀም የግለሰቡን ዲጂታል አምሳያ ይፈጥራል። ቴክኖሎጂው፦
ግለሰቡ በህይወት እያለ የጻፋቸውን ጽሁፎች፣ አስተያየቶች እና የግል መልዕክቶች ያጠናል፤
የተጠቃሚውን ልዩ የቋንቋ አጠቃቀም የሚከተል የቋንቋ ሞዴል ይቀርጻል፤
ተጠቃሚው በሌለበት አዳዲስ ጽሁፎችን ማጋራት፣ ለጓደኞች ምላሽ መስጠት እና በውስጥ መስመር ማውራት ይችላል፤
ከዚህም ባለፈ፣ የሟቹን ድምፅና ምስል በመጠቀም የቪዲዮ ጥሪዎችን የማድረግ አቅም እንዳለው በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።
የሜታ ምላሽ፦ "ለጥንቃቄ እንጂ ለትግበራ አይደለም"
የኩባንያው የቴክኖሎጂ ዋና ኦፊሰር አንድሪው ቦስዎርዝ በፈጣሪነት የተመዘገቡበት ይህ ፕሮጀክት፣ በብዙዎች ዘንድ ስጋትን ቢፈጥርም ሜታ ግን ጉዳዩን አረጋጋ ለማድረግ ሞክሯል።
የኩባንያው ቃል አቀባይ ለቢዝነስ ኢንሳይደር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ ስራ የማስገባት ምንም አይነት እቅድ የለውም። የፈጠራ መብቱ የተመዘገበው ሃሳቡ በሌሎች እንዳይወሰድ ጥበቃ ለማድረግ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
የስነ-ምግባር አጣብቂኝ እና የ"ዲጂታል መቃብር" ስጋት
ቴክኖሎጂው ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከሊቃውንትና ከስነ-ልቦና ባለሙያዎች ጠንካራ ትችት እየቀረበበት ይገኛል። ዋና ዋናዎቹ ስጋቶች የሚከተሉት ናቸው፦
የሀዘን ሂደት መስተጓጎል፦ ቤተሰቦች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ ሊያልፉበት የሚገባውን የተፈጥሮ የሀዘን ሂደት ቴክኖሎጂው ሊያሰናክል ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ትርፍ Vs ሰብአዊነት፦ ሜታ ተጠቃሚዎች ከሞቱም በኋላ እንኳ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚኖረውን የሰዎች እንቅስቃሴ (Engagement) ላለማቀዝቀዝ ሲል የሰውን ልጅ ሞት ለንግድ መጠቀሚያ ሊያደርገው ነው የሚል ወቀሳ እየቀረበበት ነው።
ይህ "ዲጂታል መቃብር" ተብሎ የተፈረጀው ቴክኖሎጂ፣ ወደፊት የሰውን ልጅ ህይወት እና ሞት ትርጉም ምን ሊያደርገው እንደሚችል አሁንም አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።
0 Comments