የUN እና ግብርአበሮቹ ቤተሰባችንን የማፍረስ የ2030 ርብርብ


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል

ነባር እሴትን በመናድ የሚፈርስ እንጂ የሚታነጽ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሀገርም የለም!

ሁሉም የጥፋት ሥራ፦
👉 ለትውልዱ፣
👉በተለይም ለተጎዱት፣
👉 ይበልጡንም ለሴቶችና ለሕጻናት፤ መብትና ነፃነት ተብሎ ይፈጸማል።

🚨 ነገር ግን መደምደሚያና ማሳረጊያው፦ ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን ከምንም በላይ ግን በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሰው(ሰውነት) ማጥፋት ነው።

ጩኸታችን እንደቀጠለ ነው!
ድምጻችንን ሰምተው መታነጽ ለሚፈልጉት ደግሞ ሥልጠናችን!

ብዙዎቻችሁ ዝምታን መርጣችኋል ታሪክ በዘመኑ የተነሱ “ግድየለሽ፣ አቅመቢስ፣ አስመሳይ አልጮች” ብሎ እንዲያስታውሰን መርጣችኋል።!

ይህ በጠራራ ጸሐይ፣ በግልጥ በአደባባይ ትውልድን ከነባር እሴቱ የመለየት፣ ከማንነቱ የመነጠል፣ በዚያም ሰውነት ተፈጥሮውን፣ ቤተሰብ ተቋሙን፣ ማኅበረሰብ ሕንጻውን የማፍረስ ሥራ ሲፈጸም “ምን እናድርግ?” ብሎ መምከር የተገባ ነበር።

ነገር ግን “ጊዜው አልደረሰ ይኾን” ለዚያ አልታደልንም! አሁንም ለሕዝቡ መረጃን ማቅረብ የሚችሉት በዚያው ሕዝብ አደንዝዝ፣ አእምሮ አፍዝዝ፣ ዐይን አደንግዝ ገንዘብና ዝና በሚያገኙበት መርሐግብራቸው ቀጥለዋል።

አንተስ?

ዝም! ጭጭ!

ልጆቻችን ኾን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ትዳርን እንዲጠሉት፣ መዳራት ወግ እንዲኾንባቸው፣ ከማንም የትም፣ መቼም መንጠላጠል ጀብድ እንዲመስላቸው እየተደረገ ነው።

ይህ ሁሉ ሲኾን ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት ያሉት ልሂቃንና ሊቃውንት ያያሉ፣ ይሰማሉ፣ ያውቃሉ ነገር ግን ሆዳቸው ተችሏልና፣ ጥቅማቸው ተጠብቋልና ትውልዱ ሲጠፋ ዝም....!

“...ሌላ ስንት አንገብጋቢ ጉዳይ አለብን...” የችግሩንም ጥልቀት ለመስማት ለመማርም አይፈልጉም ሁሉ “አዋቂ” ነውና ሚዲያውን የያዙትም የቀደሙትም ይህንኑ ይሏችኋል።

በዚህ መካከል ግን፦
🚨 ትውልድ እያጣን ነው!
🚨 ቤተሰብ እየፈረሰ ነው!
🚨 ልጆቻችን እየተበተኑ ነው!
🚨 ጋብቻ ትዳራችን መቧለቻ የቡና ቁርስ እየኾነ ነው!
🚨 ትዳርን ታናናሾቻችን እየፈሩት እየጠሉትም ነው!
🚨 ምን ቢማር “ዶክተርና ኢንጂነር፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት” ቢባልም አልጫ፣ አስመሳይ፣ አድርባይና ሆዳደርም ትውልድ እያፈራን ነው!
🚨 የጠላቶቻችን መሳቂያና መሳለቂያም እየኾንን ነው!
🚨 ማኅበረሰባችን እየመከነ ነው!

ህም!

አንተስ?
አንተም ያው ነህ!
እነዚያን ስወቅስ፤ ተደርበህ አትክሰስ!
እንዳውም አንተም ራስህ ተወቀስ ተከሰስ እንጂ!

በዘመናችን “የሴቶች መብት”፣ “እኩልነት” እና “እንክብካቤ” በሚሉ ማራኪ ቃላት የታጀቡ “ዓለም አቀፍ ስምምነቶች” የእያንዳንዳችንን ቤት ደጃፍ እያንኳኩ ነው። የጎረቤትህ ሲንኳኳ “ጉዳቸው” ወይም “እሰይ ይበላቸው” የምትል ከኾነ ነገ አንተም ቤት በተለያየ መልክ ይመጣል።

ጦርነቱ የታወጀው እኔ “ሄኖክ” ላይ አይደለም! ትውልድ የሚታነጽበት እሴት፣ ትውፊት ላይ እንጂ! በርህን ዘግተህ፣ ቀዳዳውን ወትፈህ የምታመልጠው አይደለም!

በእነዚያ ቃላት ሽፋን ተለብጦ የሚካሄደው ስልታዊ እንቅስቃሴ የሴቶቻችንን፦ የእናቶቻችንን፣ የእህቶቻችን፣ የሚስቶቻችንን፣ የልጆቻችንን ሕይወት አላሻሻለም! ሁሉም ውሸት ነው!

ይልቁንስ የማኅበረሰባችን መሠረት የኾነው፣ ሰውነትም የሚበየንበት ጥንታዊና ተፈጥሯዊ የቤተሰብ መዋቅር ተኮነነ፣ አባታችንን የምናይበት አባታዊ ሥርዓት ፈረሰ እንጂ!

ከትውልዱ ግን ይህን ማን አስተዋለ!

ይህንን ደግሞ ከእኛ ቀድመው የኑሮ ዘዬያቸውን “ያሻሻሉ”፤ ከእኛ ቀድመው በዚሁ መንገድ የተጓዙ፣ ማደግና መበልጸግ ሽተው የቀደሙ፤

ነገር ግን ትውልድ ያንጹበት የነበረ ነባር እሴታቸውን ከብያኔው ጀምረው ጥለው ትዳር አልባ፣ ትውልድ አልባ፣ ቤተሰብ አልባ እየኾኑ የመጡትን ምዕራባውያንን ተመልከቱ!

የዚህን የጥፋት ማዕበል ታሪካዊ ዳራ ብናየው ጣልያናዊውን አንቶኒዮ ግራምሺን እናገኘዋለን። ከግራምሺ በፊት ግን ይህንን ለማፍረስ ኪዳን የገባውን ካርል ማርክስን፤ ከሰይጣን ጋር ውል ያሰረውን ያሻረከውን ስምምነት፤ ከእርሱም በፊት “በእኩልነትና በነፃነት” ሰበብ ሔዋንን ያታለለ ሰይጣንን እናገኛለን!

ግራምሺ ማርክሳዊ አብዮት በምዕራባውያን ዘንድ(እንደ ራሽያ) ሊሳካ ያልቻለው ማኅበረሰቡን ደግፈው የያዙ ጠንካራ ማኅበራዊ እሴቶች፦ ቤተሰብ፣ እምነትና ባህል...፤ ስላሉ መኾኑን አስተውሏል።

ምንም እንኳ በካርል ማርክስ የኮሚኒስት እሳቤ ላይ ጥርጥር ባይኖርበትም ነገር ግን የመንግሥት ግልበጣ አብዮቱ የታለመውን ማሳካት እንደማይችል አጽንዖት በመስጠት፤ ከእርሱ ይልቅ ባህልን፣ እምነትን፣ እሴትን መሸርሸርና በሌላ መተካቱ ተገቢ እንደኾነ ጠቁሟል።

ስለኾነም ሚስትነትን እንደ ግርድና፣ እናትነትን እንደ ስቃይ፣ አባትነትን እንደ ጨቋኝነት በመሳል ማኅበረሰቡ በገዛ እጁ የቆመባቸውን፣ የተተከለባቸውን “መሠረቶቹን” እንዲንድ፣ ማንነቱን ያቆሙለትን “ምሰሶዎች” እንዲነቅል ማድረግ ከሀንጋርያዊው ጓዱ ጋር የተስማሙበት ነበር(“በገዛ እጁ” ማለቴን ልብ በል)።

ነባር እሴቶቹ የተናዱበት፤ በተለይ ደግሞ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ሰበብ ራሱ ማኅበረሰቡ እየተጣደፈ፣ እየተቻኮለ እንዲንዳቸው በተደረገበት፤ ማኅበረሰብ ደግሞ ምን ቢማርና በቁስ ቢበለጽግ እንደ UN ላሉ ዓለም አቀፍ ኃይሎች በቀላሉ የሚገዛ “የአልጮችና የሆዳደሮች ስብስብ” ይኾናል።

🌟 ውርድ ከራሴ!
🚨 መስማትን እንቢ ብላችኋል!
🚨 ባርነትና የቁም ሞትን ለልጆቻችሁ አቆያችሁ!

የግራምሺ ስልታዊ ሥራ ወይም በፋብሪካ ያለው የአሠሪና የሠራተኛ ሙግት ሰተት ብሎ ወደ ቤት-ቤተሰባችን ገባ።

በተለይም ይህንን ትንታኔ፣ “ለቤት እመቤቷም የቤት ውስጥ ሥራ ክፍያ ይገባል” ንቅናቄ ከእርሱ በኋላ ያራገበችው ያገሩ ልጅ ሲልቪያ ፍሬድሪቺ በተለይ በUN እና ግብርአበሮቹ ተቋማት ውስጥ አቀጣጥላዋለች።

ከዚህ በፊት ማርክሳዊው የብሶት አብዮት “ማቆሚያ መቋጫ የሌለው ሰደድ እሳት፤ ግፋ ሲልም ያደረበትን ሁሉ ሳያጠፋ መራባቱን የማያቆም ነቀርሳ ነው” ያልኳችሁን አትርሱ።

ሁሉ ጊዜ ግን ይህ ነቀርሳ ሲመጣ ራሱን የሚሰውርበት “ካባ” (camouflage) ደርቦ ነው። ለዚያ ነው በተገኘበት ጊዜና ዘመን ያሉትን፣ የተማሩትንም ጭምር ከማሳት የማይነጥፈው።

የካርል ማርክስ የኮሚኒስት አብዮት ከፋብሪካ፣ ከቤተመንግሥት ወደ ባህል(እሴት) በግራምሺ ሲመጣ፣ በሲልቪያ ፍሬድሪቺ ደግሞ ከባህልና እሴት ከተባለው ሰፊ ዐውድ ወደ ጠባቧ ቤት ገባ።

የዘመናችን አፍቃሬ ማርክስ ሶፊ ሌዊስ (Sophie Lewis)፣ “Abolish the Family” በሚለው መጽሐፏ ደግሞ ቤተሰብ “የጭቆናችን ማዕከል ነው” ብላ ግልጽ ጦርነት አወጀችበት።

ለእሷ ቤተሰብ በአባታችን የተመሰረተ፣ አባታዊ ፍቅሩ የሚፈስበት፣ የፍቅር ማዕከል ሳይሆን፣ ሴቶችን ቀፍዶ፣ ቆንድዶ የያዘ “እስር ቤት ነው” ባይ ነች።

ይህ ብቻ አይደለም! ሲልቪያ ፍሬድሪቺ የቤት ውስጥ ሥራ ከ”ሥራ” ተቆጥሮ ደመወዝ ይከፈለው ብትልም ሶፊ ግን ያ “ቤት(ቤተሰብ) ራሱ የሴቷ የጭቆና የብዝበዛ ማዕከል” አደረገችው!

ስለኾነም ሥራ የኾነው ሁሉ በክፍያ፣ በሙያ ተወዳድረው ተቀጥረውና ለሚሠሩት መተላለፍ አለበት፤ ይህም የሥራ እድል ለሀገሪቷ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት (Care Economy) ያበርክት የሚለው እየጎላ መጣ!

አልፋ ተርፋም እርግዝናም “ሥራ” ነውና በክፍያ ለሌሎች መተላለፍ ይገባዋል (surrogacy)! በተፈጥሮአችን ተገደን፣ በማኅጸናችን ተሳበን፣ በፍቅር ተስበን “ባርነት፣ ግርድና መግባት ማደር የለብንም” ባይ ናት!

እንደምትመለከቱት ይህ ከጅምሩ በተውሳክ የተጠቃ ሃሳብ፣ ነቀርሳዊ እርባታው እየከፋ እየከፋ መምጣቱንና ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በዚያም ማደሪያውን “ሰው”-ሰውነት ለመጥፋት መቃረቡን ትረዳላችሁ!

ሊውስ የፍሬድሪቺን “ልጅ መውለድም ሥራ ነው” ትንተና በመጠቀም፣ “ከሥራ” እስከተቆጠረ ድረስ ልጆችን ማሳደግ እና እንክብካቤ መስጠት በአንድ ጠባብና በዘርና በደም በተሳሰረ የግል ቤተሰብ ውስጥ ብቻ መታጠር የለበትም” ትላለች።

“ይልቁንም “የጋራ እንክብካቤ፣ ማኅበረሰብ አቀፍ እንክብካቤ፦ እንደ የሕጻናት ማቆያ (Collective Care, Communal Care) መኾን አለበት” በማለት ትከራከራለች።

ይህ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጥቃት ዛሬ በ UN Women እና በግብርአበሮቹ የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች በኩል ተግባራዊ እንዲኾን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው።

በተለይ ደግሞ የትራምፕ አሜሪካ በእነዚህና መሰል በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ስም ከሚፈጸሙ ክፉ ተግባራት ራሷንና የገንዝብ ድጋፏን ማግለሏን ተከትሎ፤ እርሱን የሚክስ ሥራ ለመሥራት፣ ያቀዱትን ለማሳካት፣ ሳይሳካም ትውልዱ የአሜሪካንን ጥቂቶች ተከትሎ እንዳይነቃባቸው ውክቢያው ከፍቷል።

እኛስ?
እኛ እየተባበርናቸው ነው!

UN Women በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመመደብ፣ በየሀገራቱ ያሉ “ግብረ-ሰናይ” ድርጅቶችን (NGOs) እንደ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ይጠቀማል።

“በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት” እኩይ ምክር ተንጦ ለሚፈረሰው፣ እንዲፈርስም ታቅዶ ለሚነቀነቀው ትዳር፣ ከእርሱም ለሚገኙ ልጆች የሚኾን ደግሞ ወጥመድ አለ።

እርሱም የእንክብካቤ ኢኮኖሚ (Care Economy) እያሉ የሚያወሩት እናቶች ከባሎቻቸውም ይኹን ከማንም የሚያመጧቸውን ልጆች በሺዎች ለሚቆጠሩ ማቆያ ማዕከላት (Daycares) አስረክበው ወደ “ሥራ” እንዲሰማሩ የሚደረገው ግፊት፣ እናትን ከልጅ፣ ትውልድን ከትውፊት የመነጠል የግራምሺያን እቅድ ማስፈጸሚያ ነው።

ወንድምዓለም! ነባር እሴትን በመናድ የሚታነጽ ማኅበረሰብ የለም፤ የሚፈርስ እንጂ። የሰው ልጅ “ሰው” የሚኾነው በቤተሰብ ውስጥ በሚያገኘው ፍቅር፣ እምነትና ታሪክ ነው።

ልጆች ገና በጠዋቱ በሕጻናት ማቆያ ማዕከላት በቢሮክራሲና በባለሙያ እጅ ካደጉ፣ የወላጆቻቸውን ማንነትና የሀገራቸውን ትውፊት ሳይቀስሙ ቀርተው፤ ራሳቸውን፣ ማኅበረሰባቸውንና ሀገራቸውን የሚያጠፋ ሌላ ማንነት እንደሚይዙ የትራምፗ ሰሜን አሜሪካ ጉልህ ማሳያ ናት!

ለዚህ በተለይም በUNwomen እና በግብርአበሮቹ የ2030 ዕቅድ መፍትሔ የሚኾነው፦

ሴቶቻችንን ጠበቅ ወንዶቻችንን ጠንቀቅ አደርጎ በአባታቸው ጸጋ ላይ፣ በተለየላቸው ሚና እንዲሠለጥኑ፣ እንዲበለጽጉና እንዲያይሉ ጽድቅም እንዲሠሩበት ማስተማር ነው።

የሚጀምረው ግን ካንተ ነው!

ቤተሰብ ተፈጥሯዊና መለኮታዊ ተቋም ነው። ይህንን ተቋም ማፍረስ የሰውን ልጅ ማንነት ማጥፋት ነው። ከቀደመው ሰይጣን በካርል ማርክስ ተነድፎ፣ በግራምሺ ታርሞ ወደ ተቋማት ታጋብቶ የቀጠለው ትውልዱ የታነጸበትን እሴት የማፍረስ ሥራ የሰውን ልጅ ከተፈጥርአዊው ባህሪው አርቆ የሚያጠፋው ነው።

UNwomen በ2030 አሳካዋለሁ የሚለው “የጾታ እኩልነት፣ መብትና ነፃነት”፤ አስቀረዋለሁ የሚለው “የሴቶች ጥቃት”፣ አቀርበዋለሁ የሚለው “የወሊድ መከላከያና ውርጃ” ለሴቶቻችን የታሰበ መልካም መሳይ ክፉ መጥፊያቸው መጥፊያችንም ነው!

መች ሰማሁና እንዳትል ተጻፈ!

Post a Comment

0 Comments