ለእጆቻችን ጠብን ለጣቶቻችንም ሰልፍን ማን ያስተምራል? መዝ 143፥ 1


 ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

ጠበኝነትን ትኅትናን ከፍርሃት፣ ሰልፍንም ትዕግስትን ከአቅመቢስነት ቆጥሮ ትውልድን ሊያጠፋ ለሚመጣው ጠላት መሣሪያ እንዲኾነን አባታችን አባቶቻችንም አስተምረውናል!

በጠላት መራሹ፣ አስመሳይ አለስላሹ፣ አድርባይ ዘራሹ የ”ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት” ስብከት ጠበኝነት የክፉው ዓለም፣ ሰልፍም የሠራዊቱ መሣሪያ እንደኾነ ይነገራል።

ይህ ትርክት ግን ትውልዱን ከተገኘበት እሴቱ ለይቶ፣ ወኔውን ሰልቦ፣ ለባርነት የሚያመቻች ስውር መርዝ ነው። “እንደ ልቤ” የተባለው ቅዱስ ዳዊት የአባቶቹን እሴት ተከትሎ ባደገበት ወጉ፣ ጎልያድን በዘረረበት ትግሉ፣ ያንንም በዘከረበት መዝሙሩ፦ “ለእጆቼ ጠብን ለጣቶቼም ሰልፍን ያስተማራቸው አምላኬ እግዚአብሔር ይመስገን!” (መዝ 143፥1) በማለት የዘመረው፣ እውነተኛ መንፈሳዊነት ከጥንካሬና ከጥበቃ ጋር የተቆራኘ መኾኑን ያሳያል።

ዛሬ ግን ዘመናዊነትንና መንፈሳዊነትን ከስልብ ጃንደርባነት፣ ከእንከፍ ምስኪንነትና ከአሰስ አልጫነት ጋር እያመሳሰሉ መሳ-ለመሳ የሚሰብኩ አሳሳቾች በዝተዋል።

እነዚህ ሆዳደሮች የሚያሰራጩት ትርክት፣ ወንድ ልጅ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ቤተሰቡንና ማኅበረሰቡን ቤተክርስትያኑንና ሀገሩንም ጭምር በነፍሱ ተወራርዶ እንዳይታደግ ወኔ-ክንዱን የሚሰብር የጥፋት ድግስ ነው።

ወንዱን እንከፍ፣ ምስኪን፣ አቅመ-ቢስ፣ ወኔ-ቢስ፣ አልጫ፣ ጎስቋላ፣ አላዛኝና ነፍራቃ በማድረግ፣ ከነዘር ማንዘሩ በባርነት እንዲያድር የሚያደርግ ስልታዊ ስምሪትም ነው።

ይህ ከትውፊት የተለየ፣ ከእውነት የራቀና እሴትን ያልጠበቀ አስተሳሰብ፣ ጠላት በሆዳደሮች አፍ አማካኝነት በትውልዱ ልብ ላይ የሚዘራው “የሞት ዘር” ነው።

መንፈሳዊነት ማለት ክፋትን ዝም ብሎ ማየት ወይም ለውርደት እጅ መስጠት አይደለም። ይልቁንም ለእውነት መቆም፣ ርስትና ድንበርን ማስከበር፣ ቤተሰብን ከጥቃት መከላከልና ለጽድቅ ጦርነት መዘጋጀት ጭምርም ነው።

ዳዊት እጆቹን ለጠብ፣ ጣቶቹን ለሰልፍ ያሰለጠነው እግዚአብሔር ራሱ እንደኾነ ለዚያም ምስጋና እንዳቀረበ የገለጸው፣ ወንድነትና ተዋጊነት አሸናፊ፣ ተዋጊ፣ ኃይለኛ በዚያም የሰላም አለቃ ከኾነው ከመለኮታዊ ጸጋ የማይነጠሉ መኾናቸውን ለማሳሰብ ነው።

ዛሬ በየመድረኩና በየማኅበራዊ ሚዲያው “ፍቅርና ሰላም” እያሉ የትውልዱን ወኔ የሚያረግፉት ሰባኪያን፣ ወንዱን ለጠላት አሳልፈው የሚሰጡ የይሁዳ መልእክተኞች፣ ወገኔ ላይ የሚሸቅሉ ገበያ የቆመላቸው የሞት ነጋዴዎች ናቸው።

ጀግንነትም በአልጮች አይሰበክም፣ አባወራነትም በምስኪናን አይተረክም፣ ወንድነትም ጃንደርብነትን ካጸደቁት አፍ አይጠበቅም ከኾነ ግን ትውልድን ለባርነት ለመንዳት የተዘረጋ መረብ ይኾናል።

ወንድምዓለም! ትውልዱን በዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ስም በማምከን ስም የሚነግዱትን አሳሳቾች እወቃቸው። አንተ ግን ጽድቁን ትፈጽምባቸው ዘንድ እጆችህ ለጠብ፣ ጣቶችህ ለሰልፍ፣ ልብህም ደግሞ በእምነት የጸና ይኹን!

Post a Comment

0 Comments