ፍርሃት የነገሠበት ያስመሳዮች ክርስትና አልተሰጠንም!


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ሽልጥልጥ አስመሳይነት የክርስትያኖች መገለጫ የኾነው የአባቶቻችንን እሴት ጠልተንና ጥለን የባዕዳንን ስንቀላውጥ የተገኘንበት ዝቅጠት ነው!

የኢትዮጵያ ክርስትና የታሪክ ማህደር ብቻ አይደለም፤ የጀግንነት፣ የጽናትና የእውነተኛነት መገለጫ እንጂ። አባቶቻችን ያወረሱን ክርስትና በፍርሃት የሚሸማቀቅ፣ በጥቅም የሚደለል ወይም ለታይታ የሚደረግ አልነበረም። ይልቁንም ለእውነት የሚሞት፣ ለሀገር የሚሰዋና በግብር የሚገለጥ እውነተኛ እምነት ነበር።

ነገር ግን ዛሬ ይህንን ክብር ጥለን፣ የምዕራባውያንን የቅብጠት፣ የታይታና የ”አፍአ” ክርስትና ወርሰናል። ይህም እውነተኛውን ክርስትና በማንነታችን ላይ እንዳይገለጥ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የሀገር ባለውለታና የመንፈሳዊነት መሠረት፣ የሥነ-ሥርዓትና የሥነ-ምግባርም ውሃ-ልክና ድምድማታቸው ኾና ቆይታለች።

አባቶቻችን ክርስትናን የተቀበሉት በልባቸው ጽላት ጽፈው፣ በሕይወት በተግባራቸው ገለጠው ሊኖሩት፦ ባህል፣ ወግ፣ ልብስ፣ ሥልጣኔ፣ ምግባር፣ መብል፣ መጠጥ ሊያደርጉት እንጂ በአፋቸው ሊሰብኩት ብቻ አልነበረም።

ለእምነታቸውና ለሀገራቸው ሲሉ አንገታቸውን ለሰይፍ የሰጡ፣ ለጽድቅ የቆሙና የጀግንነት አርአያ የኾኑት አባቶቻችን፤ በዚያ ጽድቅ ሊሠሩበት በእውነት፣ እምነትና እሴት በታነጸ ልባቸው ሰውነት ማንነታቸውን፣ ኢትዮጵያዊ አባወራነታቸውን ስላሠለጠኑት፣ ስለሠለጠነላቸውም ነው!

ይህ አርበኛዊ ክርስትና በፍርሃት ተሸማቆ የሚገዛ ሳይኾን፣ በእምነት የሚበረታና ለእውነት የሚቆም ነበር። በጦር ሜዳም ሆነ በጸሎት፣ በአስተዳደርም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወት፣ የክርስትና እሴቶች ይገለጡበት ነበር።

ሐውርያው ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ በ2ኛው ጦማሩ ጢሞ 1፥7 የላከውን መልዕክት፦ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና፤ የሚለውን ስንት የዘመኔ አስመሳይ ሽልጥልጦች ዓውደምህረት ላይ ሰብከውት፣ በዩቲዩብ ሸቅለውበት፣ በመጽሐፍም ከትበውት ይኾን?

እነዚያ የእውነት፣ የእምነት፣ የእሴት በር ማኅተም የኾኑት አባቶች ግን በዝምታ ነገር ግን በተግባር ኖረውታል በለሆሳስ ነገር ግን በማይካድ ጽኑ ስብዕና ገልጠውታል፣ ሰማዕት ኾነውበታል፣ መስዋዕትነት ከፍለውበታል፣ በሕይወት አስተምረውታል።

አባቶቻችን “አዎ”አቸው “አዎ”፣ “አይደለም”አቸው ደግሞ “አይደለም” ነበር። ዛሬ ግን “... ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ...” የተባለው የምስኪናን መዘነጫ፣ የአልጮች ማምረቻ፣ የቀባጮች ማንገቻ በኾነ ክርስትናችንም የአባቶቻችን የማይመስል “አዎ”አችንን በ”አይ” የምናጥፍጠፋ ሽልጥልጦች ኾነናል!

እነዚህ ከባዕዳን እየቀዱ ከማርክሳውያን ዘመናዊነትን እየበረዙ ለትውልዱ መጽሐፍ የጻፉት ትውልዱን አባቶቹ በማይመስል የጥፋት ጎዳና መሩት።

ይህም ውስጣዊ ጽናታችንን አጥፍቶ፣ በሰው ፊት ብቻ የምንታይ፣ ለመታየትም እንደ እስስት የምንቀያየር፣ የወጣልንና የተዋጣልን አስመሳዮች አደረገን።

(እኔ ባደሩበት አድርባይነት የትውልዱን ወኔ ተፈጥሮውን፣ ወንድነት መክሊቱን ሰልበው፣ ቆርጠውና ቀጥቅጠው፤ በክርስትና ስም ለጠላት የሚያደልቡበትን ሙክት ጃንደርብነትቱን የሚያጸድቁበትን፣ ለባርነት የሚያሰቡበትን መጽሐፋቸውን አላነብም። ለዚህም አጻጻፌ ይመሰክራል የማናቸውንም አይመስልም!)

ክብራችንን፣ ማንነታችንን ጥለን፣ የምዕራባውያንን የ”ታይታ” እና የ”ቅብጠት” ክርስትና ወረስን። ይህ ክርስትና በውጪ በአደባባይ የሚሽቆጠቆጥ፣ በመብራትና በጌጥ የሚንቆጠቆጥ፣ በልብስና በአልባሳት የሚሽሞነሞን፣ በለስላሳ ቃላት የሚንቆረቆር ፍሬ የሌለው ገለባ ነው። ለዚያም ነው ጽድቅን ለተራበ ሕዝባችን፣ ፍትሕን ለተጠማ ወገናችን አንዳች ረብ የማይፈጽመው። አስመሳይነትን ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተሞሸርንበት፣ የተሾምንበት ነውና!

ይህ ክርስትና በታይታና ዕውቅና፣ በቁጥር ብዛትና ድምቀት፣ በመታወቅና በመወደድ ላይ ያተኩራል። እውነተኛው መንፈሳዊነት ግን በግብርና በሥነ-ምግባር ይገለጣል። ሲገለጥም አልጫዋን ዓለም የሚያጣፍጥ ጨው ይኾናል።

በሰዎች ዘንድ ለመታየት፣ ተከታይ ለማብዛት፣ መወደድን ለማግኘት፣ ዓለማዊ ጥቅምን ማሳደድ፣ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድ አልያም በዩኔስኮ መመዝገብ የአባቶቻችን ያልኾነ የማይመስላቸውም የባዕዳን ጠባይ ነው።

መንፈሳዊነታችን በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ ሳይኾን፣ በሕግ የተመጻደቀ፣ በቅጣቱም የሚመካ ሲኾን የአልጮች ኾኖ ሽልጥልጥ አስመሳይነት መገለጫችን፣ እንከፍ ምስኪናንን ማፍራታችን እርግጥ ይኾናል።

Post a Comment

0 Comments