ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ(2)


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር  

የሩሲያ መንግስት በሀገሪቱ እየታየ ያለውን የሕዝብ ቁጥር መቀነስ (demographic crisis) ለመታደግ ዐዲስ የጤና መመሪያ አውጥቷል። በዚህ መመሪያ መሠረት ልጅ መውለድ የማይፈልጉ ሴቶች ወደ ሥነ-ልቦና ባለሙያዎች (psychologists) እንዲላኩ ይደረጋል።

ከዚህ በፊት በዚህ ርዕስ ስር የጎረቤታችን ኬንያን ተምክሮ አካፍያችሁ ነበር። “ሴቶችን ማብቃት (Women Empowerment)” ሴቶቻቸውን ትዳር አልባ፣ ቤተሰብ አልባ፣ ትውልድ አልባ፣ ዘር አልባ እያደረገ እያጠፋቸው እንደኾኑ አንዲት የኬንያ የፓርላማ ተወካይን አስተያየት ጠቅሼ ማሳሰቤ ይታወሳል።

እኚሁ የፓርላማ ተወካይ ሴቶቻችን ማብቃት፦ ከትዳር እስኪለያቸው፣ እንዲለያቸው፣ እስኪያርቃቸው መኾን አልነበረበትም፤ ሲሉም ይሟገታሉ።

ዛሬ ደግሞ ይኸው ሴቶችን የማብቃት ጉዳይ በፑቲኗ ራሺያ የፈጠረው የወሊድ ቁጥር ማነስ ያሳሰባቸው የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት “መውለድ አንፈልግም” የሚሉትን የሀገራቸውን ሴቶች ወደ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ሊልኩ እንደኾነ እየሰማን ነው።

የማርክሳውን በተለይም ግራምሺያውያን እቅዳቸው እየደረሰ፣ ውጥናቸው እየሰመረ ነው። የማኅበረሰቡን እሴት በመናድ ነባር ተቋማትን ማፈራረስ ነው(ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ቤተክርስትያን፣ ሀገር)።

በዚህም አስቀድመው ትውልዱን በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ሰበብ ከመጣበት እውነቱ፣ እምነቱ፣ እሴቱ ሲያፋቱት ልብ አልባ ኾነ።

እርሱም ምን እውቀት፣ ንብረትና ስኬት ኖሮት ማስትሬትና ዶክትሬት፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ቢባል በተሳለው አእምሮው ራሱን የሚያጠፋ አልጫ ሲኾን ከዚያ የሚታደገውን ሃሳብና ድርጊት ሁሉ “የሰብአዊ መብት ጥሰት” ይለዋል።

ለምን?

ሰውነቱን የሚወሰነው፣ የሚበይነው እሴቱ ተሽሮ፣ ልቡም ጠፍቶ ልብአልባ ኾኗልና፤ በዚያም ሰውነቱን አጥቶ ለጥፋትና ሞቱ ተላልፎ ተሰጥቷል።

በራሺያ እየኾነ ያለው እጅግ አሳሳቢ ነው። ሴቶቹ “ከወንድ እኩል ትኾናላችሁ” ተብለው አድገው፤ እንዲጠሉትና እንዲጠየፉት በተደረጉት ሴትነት ጸጋቸው መውለድን እንቢ ብለዋል።

የራሺያውያን ትውልድም እያሽቆለቆለ መጥቷል!

ፕሬዝዳንት ፑቲን ሴቶችን ወደ ሥነ-ልቦና ባለሙያ በመላክ ብቻ ይህን የታሪክ ስህተት ሊታደጉት ይችሉ ይኾን? ወይንስ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ” እንደሚባለው ነገሩ ከእጃቸው አምልጧል?

ጥያቄው ለእኛም ጭምር ነው። እኛስ ከቤተ-መንግሥት እስከ ቤተ-ክህነት የዘረጋነው ይኸው ትውልድን ከእሴቱ የመነጠል ማርክሳዊ ሸፍጥ፣ እንዲህ ያለውን ጥፋት ከማስከተሉ በፊት መቼ ይሆን በእብሪት ከታጀርንበት የጥፋት መንገድ የምንመለሰው?

የትውልድ መምከን የሚጀምረው ሴትነት ሲጠላና አባወራነት ሲናቅ ነው። ዛሬ እንደ የኢኦተቤ ያሉ የእምነት ተቋማት ጭምር ባፍጢማቸው በወደቁ ሆዳደር ሊቃውንቷ አማካኝነት ልጆቻቸውን በዚሁ ማርክሳዊ ግራምሺያዊ አጀንዳ ለማለጭ (demoralization) ተሰማርተዋል።

ሴቶቹ ሀገርን የሚረከብ፣ ቤተክርስትንን የሚያስቀጥል ትውልድ የሚያፈሩበትን ሚስትነት፣ እናትነት ሳይኾን የሚማሩት ከወንዶቻቸው ጋር የሚፎካከሩበትን፣ በፉክክርም የሚጠፉበትን ነገር እንጂ።

ሩሲያ ዛሬ መጥና ያልደቆሰችውን ድስት ጥዳ እያለቀሰች ነው። እኛ ደግሞ ከእነርሱ ጠባሳ አልማር ብለን በእብሪት ትዕቢታችን ታጅረን “ያልመጠንነውን ድስት እየደቆስን” ነው፤ ነገ በልጆቻችን ጊዜ ተጥዶ ገንፍሎ ስንጠፋ እንደ እነርሱ እስናዝን እስክናላዝንና እስክንነፋረቅ ድረስ።

ምሁር የለንም! ባለ ማስትሬትና ዶክትሬትም የለንም! ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንትም የለንም! ጋዜጠኛና ዘጋቢም የለንም! ሁሉም ባንድ ባፍጢም የደፉ አድርባይ ኾነውብናል!

ምን ይሻላል?

ዐዲስ የማርክሳውያን የጥፋት የብሶትም እርሾ ያልነካው ትውልድ ማነጽ ብቻ!

Post a Comment

0 Comments