✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
የዘመኔ ማፈሪያ ሊቃውንት በትውልዴ ይሸቅሉበታል፤ አእምሮን (Intellect) እንጂ ልብን የማያሠልጥን፣ ጽድቅ መሥራትና ለጽድቅ መጨከን የማይችል ወኔ-ቢስ፣ ልብአልባም ያደረጉታል። ልባም ቸገረን እንጂ አዋቂማ ሞልቷል!
ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንትነት ትልቅ የተከበረ ሞያ ማዕረግም ነበር። እንደዛሬው ሊቃውንቱ ልብ አልባ ኾነው ተሰልበው ከAI ጋር ሳይስተካከሉ በፊት።
AI “ሰው ሠራሹ አስተውሎት” ጽድቅ የሚሠራበት ልብ ባይኖረውም መረጃን በማስረጃ አስደግፎ ሲያስተምር ፍጹም ያስደምማል። ኾኖም ግን ሰው አይደለምና፣ ልብም የለውምና ትውልዱን የመረጃ ቋት፣ ለሃሳብም ስል እንጂ ልባም ማድረግ ያቅተዋል።
የዘመኔም ሊቃውንት ትልቁ ጥፋት ሰውነትን የሚበይነውን ልብ ትተው፣ ነገር የሚያስበውን፣ የሚያሰላስለውን የሚያመነዥገውንም አእምሮ ብቻ በእውቀት ሞረድ መሳላቸው ነው።
በዚያም የተማረ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት የኾነ፣ ነገር ግን ወኔ-ቢስ፣ አልጫ፣ ሆዳደር ትውልድ አፍርተዋል። ፍሬውም ዛሬ በግልጥ የሚታይ መራራና አሳፋሪ፣ አጥፊም ኾኗል።
የሚዘሩት እውቀት አእምሮን (Intellect) ብቻ የሚያሳብጥ ያውም በትዕቢት እንጂ የትውልዱን ልብ በእውነት፣ ባባቶቹ እምነትና እሴት የሚገነባ አይደለም። እርሱ በመረጃ ናዳ ቢደነቁርም፣ ቢሸመድድም፣ እንደሸመደደውም ቢለፈልፍም፤ ለመንፈሳዊ ጽናትና ለሰውነት ክብር የሚኾን “እሳት” ተነፍጎታል።
ይህ ዓይነት እውቀት ለጽድቅ የሚጨክን ወንድ፣ ለቤተሰቡ የሚቆም አባወራ አይፈጥርም። ይልቁንም በወሬ የረካ፣ ለተግባር ግን የዘገየ እንከፍ (Passive) ትውልድ ያመርታል። ይህንማ ማሽኑም በተሻለ ፍጥነት ይሠራዋል!
ታዲያ የሰው መምህርነቱ፣ እረኝነቱ፣ አርአያነቱ፣ ወዴት አለ?
በየመድረኩ በሚደረገው ሽቀላ፣ ትውልዱ ለእውነትና ጽድቁ ሳይኾን ለገዢዎች ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ የ “ጃንደርባነት” ማኅተም እየታተመበት ነው።
ይህ አእምሮው ብቻ በእውቀት እንዲሰባ ሲደረግ ልቡ ግን ከጭካኔ እንዲከሳ፣ እውነትን በተግባር ጽድቁንም በሕይወት የሚገልጥበት ወኔ ድፍረቱም እንዲከዳው ተደርጓል።
ሥልጣኔ በሚል ስም ትውልዱ ኃላፊነትን እንዲሸሽ፣ ለሥጋው እንዲያድርና አባወራነቱን እንዲተው ጃንደርብነቱን እንዲይዝ በእርሱም እንዲመጻደቅ ይደረጋል።
ሐኪም በእውቀቱ እንዳይመጻደቅ ቀዶጥገናውን ጭምር AI ተረክቦታል። ሊቁም በእውቀቱ እንዳይታበይ የማይደክም የማያርፈው AI መጥቶበታል። እንግዲህ ትውልዱን አስተምረው የእውቀት ባለቤት የሚያደርጉቱ ከልባልባው AI ሊለዩ ይገባል።
እርሱም ትውልዱን በተግባር መገለጥ የሚችል፣ ጽድቅን የሚያስፈጽም ወኔ ድፍረቱን፣ ትውፊት እሴቱን፣ ጽኑዕ እምነቱን፣ ደረቅ እውነቱን በልቡ በመዝራት እንጂ፤ ይህንን AI አይሠራውምና!
አለበለዚያ ሰባኪው ስብከቱን ከAI ባልተሻለ ሲሰብክ፣ ሐኪሙም ኃላፊነቱን AI ሲሰጥ፣ ትውልዱም እንደ AIዩ “ልብ-አልባ” ይኾናል።
በውጤቱም ራሱንና ትውልዱን፣ ቤተሰብና ማኅበረሰቡን፣ ቤተክርስትያኑንና ሀገሩን ሸጦ የሚበላ፣ የሚያጠፋ በእውቀቱ የታበየ ልብአልባ አድርባይ ብቻ ይተርፋል።
የገዛ ማንነቱንና እሴቱን እንደ “ኋላ ቀር” ቆጥሮ የጠላ ትውልድ፣ በሚያየው ውድቀት ማማረር አይችልም። የጥፋቱን መንገድ በፈቃዱ መርጦ ውጤቱን ሲያይ መነፋረቅም ትርጉም የለውም!
አዋቂነትህ፣ አስተዋይነትህ፣ አሳቢ አሰላሳይነትህ ከAI ፍጹም ሊለይ ይገባል። እርሱም ..... በገባህ መጠን ጨርሰው እስቲ!
0 Comments