ክብር የለሽ የመዘናጋት ሕይወት መጨረሻው ምንድነው ? (ኢካቦድ)


(ትንሽ ረዘም ቢልም ተረጋግታችሁ አንብቡት። ስትጨርሱት ትማሩበታላችሁ።)

(ክፍል፲ ጠያቂ ትምህርት)


በሴሎ መቅደስ ውስጥ የሚነደው የጧፍ ብርሃን እየመነመነ፣ ሌሊቱ በተሸሸገ ምስጢር ተውጦ ሳለ፣ የታሪኩ መጋረጃ ይከፈታል። ይህ ታሪክ ስለ ጦርነት ብቻ አይደለም፤ ይህ ታሪክ ስለ ነፍስ መዘናጋትና ስለ መለኮታዊ ክብር መሰደድ ስለሚያስከትለውም ምህረት የለሽ ቅጣት የሚተርክ ድንቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትውስታ እንጂ!

​ሴሎ ለ፫፻ ዓመታት የታቦተ ሕጉ መገኛ በመሆን የኢየሩሳሌምን ቀዳሚ ሚና ተጫውታለች። በዚያ መቅደስ ውስጥ የሚኖረው ሊቀ ካህኑ ኤሊ፣ መብራቱ ሳይጠፋ፣ ዕጣኑ ሳይቋረጥ ለዘመናት አገልግሏል። ነገር ግን፣ መቅደሱ ውስጥ ያለው ሥርዓት እየደቀቀ ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር ኃይል መራቅ ጀመረ።

በታሪክ አጋጣሚ ሴሎ የምታስተምረን ትልቁ እውነት፣ የእግዚአብሔር ምስጢራዊ መገለጫ በአንድ ቦታ ላይ ስለተቀመጠ ብቻ ያ ቦታ ለዘላለም የተጠበቀ ነው ማለት አለመሆኑን ነው። ልብ ሲርቅ እውነት ሲደፈር፣ መቅደሱ እንደ ተራ ድንኳን ይቆጠራል።

እስኪ ወደ ዋናው ታሪካችን ዘለቅ ብለን እንመልከት፦
የአፍኒንና የፊንሐስ ታሪክ በቤተ መቅደስ ጥላ ሥር ተሸሽጎ የሚኖርን “መንፈሳዊ ዕውርነት” እና “ያልተጠበቀ መዘናጋት” የሚገልጥ አሰቃቂ ታሪክ ነው። እነዚህ ሰዎች የሊቀ ካህናቱ የኤሊ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ፣ የእግዚአብሔር ምስጢር አደራ የተሰጣቸው ባለአደራዎች ነበሩ። ነገር ግን፣ በአገልግሎት ውስጥ መኖርና የአገልግሎቱ ባለቤት መሆን የተለያዩ መሆናቸውን የእነርሱ ሕይወት ምስክር ነው።

​የአፍኒንና የፊንሐስ ድርጊትና መዘናጋት በጥልቁ ሲተነተን የሚከተሉትን ረቂቅ ምስጢራት ይይዛል፦ በሦስት መሠረታዊ ትንታኔ እንቃኘው።

​፩. የመሥዋዕቱ ስርቆት፦ ከቅድስና ወደ ስስት፦

​አፍኒንና ፊንሐስ መሥዋዕቱን የሚቀበሉት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ድልድይ ለመሆን አልነበረም፤ ይልቁንም መቅደሱን እንደ ግል ማዕዳቸው ቆጠሩት። ምን ማለት መሰላችሁ? መሥዋዕቱ ተቀቅሎ ሳይበስል ወይም ስቡ ለእግዚአብሔር ሳይቃጠል፣ እነርሱ ቀድመው ምርጡን ሥጋ በሹካቸው ይለቅሙ ነበር። ምስጢሩ ያለው እዚህ ላይ ነው። ይህ ድርጊታቸው "ሥጋዊ ስስት" ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም እግዚአብሔርን እንደ "ሁለተኛ ደረጃ" የመቁጠር ትዕቢት ነው። በሕጋቸው ስብ የመለኮት ድርሻ እንደሆነ እየታወቀ፣ እነርሱ ግን ከፈጣሪ ቀድመው ለመጥገብ ፈለጉ። ሰርቀውም ከመስዋዕቱ ይበሉ ነበር።

​የመዘናጋቱ ጥልቀት፦ ቅዱስ የሆነውን ነገር "ልማድ" ሲያደርጉት፣ ፍርሃተ እግዚአብሔር ይሞታል። መዘናጋታቸው የጀመረው መቅደሱን እንደ ቤታቸው፣ መሥዋዕቱንም እንደ ንብረታቸው ማየት ሲጀምሩ ነው።

​፪. የዝሙት ድፍረት፦ በመጋረጃው ሥር ያለ ጨለማ፦

​የእነዚህ ካህናት መዘናጋት እስከ መቅደሱ ደጃፍ ድረስ ዘለቀ። በመቅደሱ ደጃፍ የሚያገለግሉትን ሴቶች በመድፈር፣ ቅዱሱን ስፍራ የርኩሰት ማዕከል አደረጉት። ዝሙት በራሱ ኃጢአት ቢሆንም፣ በመቅደስ ውስጥ መፈጸሙ ግን "የእግዚአብሔርን መገኘት ፈጽሞ መካድ" ነው። አፍኒንና ፊንሐስ እግዚአብሔር በዚያ መኖሩን ቢረዱ ኖሮ፣ በፊቱ እንዲህ ለማድረግ አይደፍሩም ነበር። ማለትም "እግዚአብሔር አያይም" ወይም "ቢመለከትም አይቀጣም" የሚል የመንፈስ መደንዘዝ ውስጥ ገብተው ነበር።

​፫. የአባታቸውን ተግሣጽ ማቃለል፦

​ኤሊ ልጆቹን ሲገሥጻቸው፣ "ሰውን ቢበድሉ እግዚአብሔር ይፈርዳል፤ እግዚአብሔርን ቢበድሉ ግን ማን ይለምንላቸዋል?" አላቸው። እነርሱ ግን አልሰሙትም።​ የአባታቸውን ምክር እንደ አሮጌ ተረት ቆጠሩት። ይሄንን ድርጊት መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጸው "እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወዶአልና" ይላል። ይህ ማለት ንስሐ ለመግባት የሚያስችል ልቦናቸው ቀድሞውኑ በክፋታቸው ታሽጓል ማለት ነው። መዘናጋታቸው "የማይመለሱበት (የማይደነግጡበት) የጥፋት አፋፍ" ላይ አድርሷቸው ነበር።

ከዚህ በኋላ የሆነውን ታሪክ ስንመለከት እጅግ አሳዛኝ መጨረሻ ይነበብበታል፦ ነገሩ እንዲህ ነው...

የጥፋት ጽዋ ሲሞላ... የአይሁድ ተራሮች በጭጋግ ተውጠዋል፤ በአፌቅ አውድማ ላይ ግን የሞት ሽታ ነግሦ ነበር። ይህ ታሪክ የአንድ ሀገር ሽንፈት ብቻ አይደለም፤ የመለኮታዊው ክብር "ስደት" እና የጀግኖች ውድቀት የታየበት፣ በብራና ላይ በዕንባ የተጻፈ ዘለዓለማዊ ምስክር እንጂ።

ጦርነቱ ተጀምሮ በአጭር ሰዓት ተፋፋመ...
እስራኤል በመጀመሪያው ዙር ጦርነት ፬ ሺህ ወታደሮችን አጥታ ተሸነፈች። በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎቹ አንድ "የመዘናጋት" ውሳኔ አስተላለፉ፦ "ታቦቱን ከሴሎ እናምጣ፤ እርሱ በመካከላችን ሆኖ ያድነን።" ታቦቱን አፍኒንና ፊንሐስ ተሸክመው ወደ ጦር ሰፈሩ ሲገቡም፣ እስራኤላውያን ምድር እስክትናወጥ ድረስ ጮኹ። የፍልስጥኤም ሠራዊት ድምፁን በሰሙ ጊዜ ደነገጡ። "አማልክት ወደ ሰፈር መጥተዋል! በግብፅ ላይ ተአምር ካደረገው ከዚህ ኃይለኛ አምላክ እጅ ማን ያድነናል?" እያሉ ተጨነቁ።

​እዚህ ጋር አንድ ትልቅ ተቃርኖ አለ። አሕዛብ የታቦቱን ኃይል ፈሩ፤ እስራኤላውያን ግን በታቦቱ ላይ ተመኩ። ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች የሳቱት አንድ እውነት ነበር፦ እግዚአብሔር በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው በቅድስና እንጂ በልማድ አይደለም።

​ነገር ግን ታሪኩ የሚነግረን አንድ መራር እውነት አለ፦ ያለ አምላክ ፈቃድ የሚደረግ ጩኸት ድልን አያመጣም። እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ታቦቱን በድፍረት ይዘው መጡ እንጂ የታቦቱን ባለቤት እግዚአብሔርን ይዘው አልመጡም ነበር። አፍኒንና ፊንሐስ በመካከላቸው እያሉ፣ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር አልነበረም።

ትልቁና አስደንጋጭ ድርጊታቸው በጦርነቱ ወቅት የታየው ነው። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሲዋጉ በኀጢአታቸው ምክንያት ተሸነፉ። በዚህ ጊዜ ንስሐ ከመግባት ይልቅ፣ የታቦተ ሕጉን ወደ ጦር ሜዳ አስመጡት።

ይህንን ​ያደረጉበት ምስጢሩ ምን መሰላችሁ? ታቦቱን ያመጡት አምላክን ፈልገው ሳይሆን፣ ኃይሉን ለጥቅማቸው ሊጠቀሙበት ነው። ለእነርሱ ታቦቱ "የጦር መሣሪያ" እንጂ "ክቡርና ቅዱስ የቃል ኪዳን ምልክት" አልነበረም። ጀግኖች ነን ያሉቱ በዚያው ዕለት ወደቁ፤ ታቦቱም ተማረከ። ​የሕይወት መዝገብ የሚከፈት እዚህ ላይ ነው።

ፍልስጥኤማውያን በረቱና በታቦቱ ዙሪያ የነበሩትን ጠባቂዎች ጨረሱ። አፍኒንና ፊንሐስ—መቅደሱን በዝሙትና በስስት ያረከሱት እነዚያ "ራሳቸውን ያጀገኑ ካህናት"—በታቦቱ እግር ሥር ተረተው ወደቁ። የእግዚአብሔር ታቦት በአሕዛብ እጅ ተጨበጠ! የኪሩቤል ዙፋን፣ የእስራኤል ኩራትና የመቅደሱ ምስጢር እንደ ተራ ምርኮ ተጎተተ።

​በጦር ሜዳው ላይ ፴ ሺህ የሚያኽሉ እስራኤላውያን እንደ ቅጠል ረገፉ። በአፍኒንና በፊንሐስ እጅ የነበረው የወርቅ ታቦት፣ ከካህናቱ ይልቅ ጠላቶቻቸውን ተቀብሎ ተማረከ።

​የታቦቱ መማረክ የእግዚአብሔር መሸነፍ አልነበረም፤ ይልቁንም "ከረከሰ እጅ ጋር ከመቀመጥ፣ በአሕዛብ እጅ መማረክን" የመረጠበት መለኮታዊ ተግሣጽ ነበር።

እዚህ ላይ አንድ አሳዛኝ ታሪክ እንመልከት፦ ​ከጦር ሜዳው አንድ ሰው አምልጦ ወደ ሴሎ ሮጠ። ልብሱ ተቀዷል፣ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሷል። ወደ ከተማይቱ ገብቶ ወሬውን ሲናገር፣ ሴሎ በአንድ ጊዜ በለቅሶ ተናወጠች።

​በዚያን ጊዜ ዕድሜው ፺፰ ዓመት የሆነው፣ ዓይኑ የፈዘዘው ሽማግሌው ኤሊ በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጨነቅ ነበር። ልቡ ስለ ልጆቹ ሳይሆን "ስለ እግዚአብሔር ታቦት" ይንቀጠቀጥ ነበር።

​ሯጩ ወደ ኤሊ ቀረበ። ዜናውንም በቅደም ተከተል እንዲህ ሲህ አረዳው፦

​"እስራኤል በጠላት ፊት ፈረጠጡ..." (ኤሊ ዝም አለ።)
​"ታላቅ እልቂትም ሆነ..." (ኤሊ አሁንም ጸና።)
​"ሁለቱ ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ..." (አባታቸው ካህኑ ኤሊ ልቡ ቢሰበርም አልወደቀም።)
​"የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከ!" ​ይህችን የመጨረሻ ቃል ሲሰማ ግን፣ የኤሊ ዓለም ቆመ። የታቦቱን መማረክ በሰማ ጊዜ፣ ከመቀመጫው ወደ ኋላ ተገንጥሎ ተጠምዝዞ ወደቆ። አንገቱ ተሰበረ፣ ነፍሱም በዚህ ሁኔታ ወጣች።

ካህኑ ​ኤሊ የልጆቹን ሞት ቻለው፤ የታቦቱን መማረክ ግን አልቻለውም። ይህ የሚያሳየው፣ ኤሊ ምንም እንኳ ልጆቹን በመቅጣት ረገድ ቢዘናጋም፣ በውስጡ ግን ለታቦቱ የነበረው ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደነበር ነው። ነገር ግን "መዘናጋት" የሚያስከፍለው ዋጋ የከፋ ነው።
​በዚያው ቅጽበት፣ የፊንሐስ ሚስት ምጥ ላይ ነበረች። የአማቷን ሞት፣ የባሏን መውደቅና የታቦቱን መማረክ ስትሰማ፣ ምጥ ጸናባት። ልጇን ወልዳ ለሞት ስታጣጥር፣ አዋላጆቹ "አይዞሽ ወንድ ልጅ ወልደሻል" አሏት።

​እሷ ግን አልሰማቻቸውም። በመጨረሻው የሕይወት ትንፋሽ አንድ ስም ብቻ አወጣች፦ "ኢካቦድ"። ትርጉሙም፦ "ክብር ከእስራኤል ተለወጠ፤ የታቦቱ ምስጢር ርቋል" ማለት ነው። በዚያች ሌሊት በሴሎ መቅደስ የነበረው መብራት ለዘላለም ጠፋ።

ፍልስጥኤማውያን ታቦቱን ወስደው በአምላካቸው በዳጎን ቤት አኖሩት። በነጋታው ግን ዳጎን በታቦቱ ፊት ተደፍቶ አገኙት። ድጋሚ አቆሙት፤ በሁለተኛው ቀን ግን ምስሉ ተሰባብሮ፣ ራሱና እጆቹ ተቆርጠው በደጃፉ ላይ ወደቁ። "ምርኮኛው" ታቦት ማራኪውን ጣዖት አዋረደው።
​ከዚህም በላይ፣ የአዛጦን ሰዎች በሙሉ በክፉ እብጠትና በብጉንጅ ተመቱ። ከተማይቱም በአይጥ ወረርሽኝ ታመሰች። "የእስራኤል አምላክ እጅ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና ታቦቱ ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ" ብለው ጮኹ።

​ታቦቱ ከአዛጦን ወደ ጌት፣ ከጌትም ወደ አቃሮን ተዛወረ። ነገር ግን በሄደበት ከተማ ሁሉ ሞትና ሽብርን ይዞ መጣ። ፍልስጥኤማውያን ሰባት ወራት ሙሉ ታቦቱን እንደ እሳት ፍም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሲያሸሹት ቆዩ። በመጨረሻም የሀገሪቱ መኳንንት ተሰብስበው "ወደ ስፍራው ይመለስ፣ እኛንና ሕዝባችንን አይግደለን" የሚል ውሳኔ አስተላለፉ። በስተመጨረሻ ታቦቱን በላሞች ሰረገላ አድርገው ​ታቦቱ ወደ ቂርያትይዓሪም ተወስዶ በአሚናዳብ ቤት ተቀመጠ። አሚናዳብም ልጁን መቅደሱንና ታቦቱን እንዲጠብቅ ቀደሰው። ታቦቱ ዳዊት በክብር ወደ ኢየሩሳሌም እስከሚያመጣው ድረስ ለ፳ ዓመታት በዚያ ቆየ።

ነገር ግን...

​"የኤሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፥ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር።" (፩ ሳሙኤል ፪፡፲፪) ይላል። ይህ ቃል ልብ ይነካል። ካህናት ሆነው፣ መቅደስ ውስጥ ኖረው፣ መሥዋዕት አቅርበው ነገር ግን "እግዚአብሔርን አያውቁም" መባላቸው! ዛሬም በመቅደስ ዙሪያ የምንመላለስ እኛ፣ ከስሙ ይልቅ ባለቤቱን እናውቀዋለን? የሚል ዘለዓለማዊ ጥያቄ ይጠይቀናል።

​የሕይወት መዝገብ ማከማቻ ሰዓት፦
​"ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?" (ማቴ ፲፮፡፳፮) ​ለነፍስዎ የሚሆን ወሳኝ የሕይወት ጥያቄ፦

(​የኤሊ፣ የአፍኒንና የፊንሐስ መጨረሻ የሚያስተምረን አንድ ትልቅ እውነት አለ፦ እግዚአብሔርን መፍራት የሌለበት አገልግሎት፣ ፍጻሜው ውድቀት ነው።)

ጥያቄው ይህ ነው፦ አንተ በሕይወትህ ውስጥ በምታደርገው መንፈሳዊ ጉዞ፣ የሚያሳስብህ የራስህ "ዝናና ስም" ነው ወይስ የእግዚአብሔር "ክብር"?

ታቦቱ ከሕይወትህ ሲርቅ፣ ዓለም በሙሉ እጅህ ብትገባም ስምህ "ኢካቦድ" (ክብር የለሽ) ይሆናል። ዛሬ በልብህ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ማነው? የእግዚአብሔር ክብር ወይስ የአፍኒንና የፊንሐስ ዓይነት ሥጋዊ መዘናጋት?

Post a Comment

0 Comments