✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ተፈጥሮን ከሰው(ክስ)፣ ማንነትን ወቅሰው፣ ሚናን ኮንነው በሚግቱት "ዘመናዊነትም ኾነ መንፈሳዊነት" ትውልድ መጥፋቱ ማኅበረሰብ መምከኑ እንደማይቀር ሃሳቡን ካመነጩት እየጠፉበትም ካሉት መረዳት ይቻላል!
ከሁለት ሳምንት በፊት በጀርመን ሙኒክ የተካሄደ የሀገራት የደኅንነት ጉባኤ ነበር። በዚያም የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማይ እመቤት ሂላሪ ክሊንተን አንድ መድረክ መርተዋል።
በዚሁም መድረክ "ከጥቂት ዓመታት" ወዲህ በብዙ ጥረት የተደረሰበትን "የሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነት" ለመቀልበስ የሚደረገው ግፊት "አይሏል" ሲሉ የጠቆሙበት ሲኾን በዚያም ደግሞ ስለ "ሴቶች መብት" እንዲወያይ የጋበዙት አንድ ሰው ተገኝቷል።
ይህ ሰው በተፈጥሮው ወንድ ሲኾን ነገር ግን ጾታውን ወደ ሴት "ቀይሮ"፣ "ሴት ነኝ" የሚል የአሜሪካ የምክር ቤት አባል ነው፤ ሂላሪ ክሊንተንም "ጾታውን ቢቀይርም ባዲሱ ማንነቱ፦ሴት ናት" ብላ ስለ ሴቶች፣ ለሴቶች፣ እንደ "ሴትነቱ" እንዲሟገት ያመጣችው ነበር።
በዚህ መድረክ ላይ ጾታውን ወደ ሴት የቀየረ ወንድም "ሴት" እንደኾነ አጽንዖት መሰጠቱ፤ ሂላሪም የዚሁ እብደት አቀላጣፊ፣ አሳላጭና አስፋፊ መኾኗ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ "ምንም አታመጡም" ስትል ግልጽ አድርጋዋለች።
የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋችም (ኢሴመተ) የሂላሪ ክሊንተንን "የሴቶች መብት" የተመለከ የቆየ አስተያየት ማስተላለፉ ባጋጣሚ፤ ወይንስ የእርሷን የጥፋት አጀንዳ ተጋሪ፣ ተባባሪ፣ አስተባባሪ፣ መሪ መኾኑንና "ምንም አታመጡም" ሲል እንድናውቅለት ፊትለፊት እየነገረን ይኾን?
ሴቶቻችንን ከተፈጥሮአዊ ሴትነታቸው ማራቅ፣ ከጠባቂ አባታቸው ከባላቸውም መለየት የሚፈልገው ጠላት እንጂ ወዳጅ እንዳልኾነ ሲታወቅ፤ ጉዳዩ እንደ ቀላል ነገር ሊታይና ሊታለፍ አይገባም።
"የሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነት" አስጠባቂዎቹ አጀንዳቸው የእህቶቻችን ጥቃት ሳይኾን ባፍጢም በተደፉበት ሆዳቸው የጠላትን የጥፋት ዓላማ ማስፈጸም ነው።
በእነዚህ ዜናዎች መካከል ምን ይታይሃል?
🚨 የሴቶች መብት የሰው መብት ነው!
🚨 ጾታቸውን ከወንድ ወደ ሴት የቀየሩ ሁሉ ሴት ናቸው!
🚨 መብታቸው፦ መኝታቸውም፣ መራቢያቸውም፣ መሥሪያቸውም፣ መዋያቸውም አንድ ዓይነት ነው!
ኢሴመተን የመሰሉ ተቋማት በእንደ እኔ ዓይነት "መሃይምና ደሀ" ሳይኾን ማስትሬትና ዶክትሬት ባላቸው "ሊቃውንት" የተሞሉ፣ ለትውልዳችን አስበውና ተጨንቀው፣ እንቅልፍና እረፍት አጥተው" ፖሊሲ ሲቀርጹና ሲያማክሩ የሚያሳልፉ፣ በብዙ ዶላሮች የሚደገፉ ናቸው።
ያንተ ዝምታ ትውልድን የሚያንጽ፣ ጽድቅ የሚፈጽም ሳይኾን ትውልድን አጥፊ ለኾነ ክፉ ሃሳብ መራቢያና መፈንጪያ ጊዜና ስፍራ የሚሰጥ እንጂ ነው!
0 Comments