ልቡን ያጠፉት ትውልድ ሕይወት ድኅነቱን አያውቅም!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

መልአካዊ አዋቂነትን እና እንሰሳዊ(ስጋዊ) ስሜታዊነትን በተሰጠው ልብ አደላድሎ ውብም ተደርጎ የተፈጠረው ሰው ልቡ ቢጠፋ ሰውነቱም እንዲኹ ይጠፋል!

ሲ.ኤስ. ሊውስ ከሰማንያ ዓመታት በፊት የተነበየው ያ አስፈሪ ዘመን ዛሬ በእኛ ደጃፍ ደርሷል። “ልብ አልባ ሰዎች” (Men without Chests) እያለ የጠራቸው ያ ትውልድ ዛሬ በምሁርነት፣ በፖሊሲ አውጭነትና በ”ሕይወት አሠልጣኝነት ከቤታችን ገብቷል።

አስተውሉ!

ሰው የተፈጠረው በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ነው፦

1ኛ ጭንቅላት (አእምሮ)፦ የመልአካዊ አዋቂነት፣ የሎጂክና የእውቀት፣ የሃሳብም አመንጭ።

2ኛ ሆድ (ሥጋዊ ፍላጎት)፦ የእንሰሳዊ ስሜት፣ የረሃብና የፍትወት፣ የሁሉም ፍላጎቶች መነሻና ማደሪያ።

3ኛ ልብ (ደረት)፦ በእነዚህ በሁለቱ መካከል የሚቆም፣ አደላዳይ “ሚዛን”።

ልብ ጭንቅላት ያመነጨውን እውነቀት ወደ ተግባር የሚቀይር፣ ሆድ የሚጠይቀውን እንሰሳዊ ፍላጎት ደግሞ በሕግና በሥርዓት በሥነ-ምግባርም የሚገታ ታላቅ ሚዛን ነው። ልብ ከሌለ ግን ሰውነት ይሻራል።

ዛሬ የምናያቸው ብዙዎቹ ምሁራን “ጭንቅላት” አላቸው፤ ዲግሪና ማስትሬት ተጭነውበታል። ነገር ግን ያን እውቀት የሚመዝን “ልብ” የላቸውም።

ልብ ስለሌላቸውም ለእውነት መቆም፣ ለፍትሕ መጮህ አይችሉም፤ ለጥቅምና ለሆዳቸው ሲሉ ትውልዱን የሚሸጥ SRHR የሚባል መርዝ ሲሰራጭ ዝምታን ይመርጣሉ።

ሊውስ እንዳለው፦ “የትውልዳችንን አእምሮአቸውን በማሳደግ፣ ልባቸውን ግን በማመንመን፣ በማክሳት አምክነናቸው፤ ከዚያም ‘ባለ ግርማ’ እንዲኾኑ እንጠብቃለን፤ ይህ ግን የማይኾን ነው!”

ልብ በጠፋበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሆድ (ስሜት) ይነግሣል። ዛሬ “መብት” እና “ነፃነት” በሚል ስም የሚሰበከው ልቅነት የሆድ ንግሥና ነው።

ልጆች ስሜታቸውን መግታት (Self-control) እንዳይችሉ፣ በልቅ ወሲብና በፍትወት እንዲሰክሩ የሚደረገው “ልብ” የሚባለውን የሞራል ሚዛን ስላዛቡት ነው።

ልብ የሌለው ሰው ስሜቱን መቆጣጠር አይችልም፤ ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው ደግሞ ለመነዳትና ለመገዛት ይመቻል።

አባወራነት በዋናነት ልባምነት ነው። ሚስቱን የሚወድበት፣ ልጆቹን የሚመራበትና ጠላትን የሚመክትበት፣ ስሜት ፍላጎቱን ሃሳብ ዝንባሌውን የሚገዛበት ልብ!

ጠላቶቻችን በሆዳደሮቹ የራሳችን ሊቃውንት አማካኝነት በ”ጾታ እኩልነት” እና በ”መብት” ስም መጀመሪያ የመቱት የአባወራውን ልብ ነው፤ ልባልባ፣ ወኔቢስ፣ አልጫ፣ ጃንደርባ እንዲኾን እነርሱኑ “መንፈሳዊነት ነው” ሲሉ አጽድቀው አደረጉት።

👉 ልቡ የጠፋ ወንድ ቤተሰቡን አይደለም ራሱን መጠበቅ አይችልም፤

👉 ልቡ የጠፋ ወንድ ለምቾቱና ለሆዱ ሲል እሴቱን ይሸጣል፤

👉 ልቡ የጠፋ ወንድ በትረካ ተሸንፎ ለጠላት አጀንዳ ተላላኪ ይሆናል።

💪 ይህ ትውልድ የጠፋበትን ልብ መመለስ አለበት!

💪 አንድም ትውልዱ ወደ ልቡ መመለስ አለበት! ያለ ልብ የምናገኘው እውቀት፣ ስለት ሁሉ ጥፋት ነው፤ ያለ ልብ የምንመራው ስሜት ሁሉ እሳት-እንሰሳዊነት ነው።

ልቡን ያጠፉት ትውልድ ሕይወት ድኅነቱን አያውቅም! ሰውነታችን የሚጸናው ልባችን ከልኩና ከተገቢው ተፈጥሮ ሲገጥም ብቻ ነው። ወንድ ልጅ ጭንቅላቱና ሆዱ ላይ ሲሠለጥን ብቻ ሳይኾን ልቡን በእውነት፣ እምነትና እሴቱ ላይ ሲያሠለጥን ብቻ ነው፤ ከሰውነት ልኩ፣ ከወንድነቱ ቁና፣ ከአባወራነቱ ማማ የሚደርሰው!

Post a Comment

0 Comments