✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ሰውማ ሞልቷል፤ ወንድስ መች ጠፍቷል፦ ያውም ተምሯል፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንትም ተብሏል፤ የልባም ድርቅ መትቶን ብርቁን፦አባወራ ስንፈልግ ባጀን እንጂ!
በየአደባባዩ “ሰው” ሞልቷል። በየቢሮውና በየመድረኩ ማስትሬትና ዶክትሬት የደረደረ፣ “ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት” የተባለ ቁጥር ስፍር የለውም።
ነገር ግን ሀገር የምትደገፍበት፣ ትውልድ የሚጠለልበት፣ እውነትን አንግቦ ለጽድቅ የሚጨክን ልባም አባወራ ግን ብርቅና ድንቅ ኾነብን እንጂ።
አእምሮው በሃሳብ ሞረድ የተሳለ፣ ልቡ ግን ከእውነት እምነቱ እሴቱም የተለየ፣ በባዕድ መርዝ የዛለ “ምሁር፣ ሊቅ” ሀገርን ለባህል ወረራ፣ ትውልዷንም ለባርነት አሳልፎ ሰጣት እንጂ ለነፃነት አላበቃትም።
አእምሮው ብቻ የሠለጠነ ምሁር፣ ልቡ ግን በእምነትና በእሴት ካልታነጸ በሆዳደርነት ለባንዳነት የሚመለመል አደገኛ የጠላት መሣሪያ ነው።
የእርሱ ማስትሬትና ዶክትሬቱ፣ ሊቅና -ሊቃውንትነቱ ለሆዱ መሙያ፣ በምንደኝት ማደሪያ፣ ግብር ለማይከፍሉ ትውልድን ለሚሸጡ ሱቆች መክፈቻ ይኾናል።
እውነትን ተናግሮ ዋጋ ከመክፈል ይልቅ፣ ዋሽቶ፣ መስሎ፣ ተመሳስሎ፣ አመሳስሎ ጥቅም ማግኘትን መርጧል፤ “ጊዜውን የዋጀ ብልሃትም” ይለዋል፤ ወኔቢስነት መኾኑ ጠፍቶበታል።
ይህ የልባምነት ድርቅ፣ ለምሁሩ ሀገሩን ከልቡ አውጥቶ፣ በቦታው ሆዳደርነትን አንግሦበት የባዕዳን ሎሌ አድርጎታል። እንዲህ ያለው ልብ የሌለው፣ ልብ አልባው አእምሮ ለጥፋት፣ ያውም ራሱን ለማጥፋት እንጂ ለልማት ብልጽግናው አይውልም።
ትውልዱ እሴቱ ተበርዞና ተደልዞ እንዲጠፋ የተደረገው፣ ልቡን በጽድቅ የሚያሠልጥንለት እውነት እምነቱን እሴት ጥብዓቱን የሚያስተምረው፣ የሚያሳየው እውነተኛ እረኛ፣ አባት በማጣቱ ነው።
ስለኾነም ወገኔ እንደ ጨው ዓለምን ማጣፈጥ ሲገባው፣ ማጣፈጥም ሲችል፤ ከዚያ ቀርቶ እንደ ገለባ በነፋስ(በማንም) የሚጠለፍና የሚወሰድ፤ ጠጣር ስብዕናውንም አሽቀንጥሮ ጥሎ እንደ ሰም የሚቀልጥ ቀበጥ፣ ቀላጭ “አልጫ” ኾነ።
አእምሮው በተሳለ ምሁር ቢከበብም፣ ልቡን የሚገዛውና ማንነቱን የሚያሳየው አርአያ አጣ። ልብ-አልባ ትውልድ ማለት ምን ቢማር ለጽድቅ ባልሠለጠነለት ልቡ ለጠላት አጀንዳ የተመቸ፣ የራሱን ክብር የናቀ፣ ለባርነቱ እርሱኑ ያጸደቀ፣ ጥፋት ሞቱን የመረጠ ማለት ነው።
ይኸው የጥፋት መንገዱን በመሃይምነት ከያዙት ይልቅ ምሁር፣ አዋቂ፣ መጣቂ፣ ሊቅ በተባሉት ዘንድ ይብሳል። ምክንያቱም በተሳለ አእምሮአቸው፣ ጽድቅን በማያውቅ ልባቸው ራሳቸውንም ኾነ ሌላውን ለማጥፋት ይቸኩላሉና።
ዛሬ ሀገሬን የቸገራት “አዋቂ” ነኝ ባይ አድርባይ፣ አስመሳይ፣ ሽልጥልጥ፣ አልጫ አይደለም። የናፈቃትና የጠፋባት፦
👉 በራሱ ላይ የሠለጠነ፣
👉 ልቡን ለጽድቅ ያሠለጠነ፣
👉 ለቤተሰቡ ራስ የኾነ፣
👉 ለሚስቱና ለልጆቹ ሥርዓትና ተግሳጽ የሚሰጥ፣ የሚጠብቃቸውም፣
👉 በጽድቁ መንገድም አርአያ የሚኾናቸው፣
👉 አስመሳይነትን የሚጠየፍ፣
👉 ልባም አባወራ ነው!
አባወራነት ከቤታችን ወጥቶ፣ ሥርዓት አልበኝነት በምሁራን ልጆቻችን ልብ ነግሦ፣ በ”እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” ስም አባወራው አንባገነን ሲባል፣ ፍቺ፣ አመንዝራነት፣ ዝሙትና ውርጃ ወግ ሲኾን ትውልድ ጠፋ!
የተማረ ሊቅማ ሞልቷል፤ ነገር ግን ጽድቅን የተራበ፣ ፍትሕን የተጠማ፣ ለሀገሩ የሚቆም “ሰው” ከሰውም ወንዱ፣ ከወንዱም አባወራው እንጂ ቸግሯል!
ማስትሬትና ዶክትሬት መጫንህ፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት መባልህ የልባምነት ማረጋገጫ፣ ጽድቁን ልትፈጽም እንዳለህ ማስረገጫ አይደለም። ሰው፣ ከሰውም የሰው ቁናነትህ
፣ የሚለካው ለጽድቅ በሚጨክነው የልብህ ጽናትና በግብርህ እውነተኛነት ነው።
🌟 ልብህን በእውነት፣ በእምንት፣ በእሴት ለጽድቅ አሠልጥን!
🌟🌟 ከአድርባይና ከአስመሳይ፣ ከታይና ይኹን።፣ ከቅልጥና ከሽልጥልጥ አኗኗርህ ውጣ!
🌟🌟🌟 የአባቶችህን “አዎ” እና “አይደለም” ብሎ ቃልን ጠብቆ ከመሸበት የማደርን ማንነት ገንዘብ አድርግ!
🌟🌟🌟 ሀገሬን ልባም ሰው ቸገራት እንጂ፣ “ተማርኩ” የሚል ሆድ አምላኪ፣ ወሬኛ፣ አስመሳይማ በየቦታው ሞልቷታል!
አባወራው አለህ? የት ነህ?
0 Comments