በልጆች ማቆያ ትውልድ ይጠፋል እንጂ አይታነጽም!

ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ማርክሳውያን ልጆችን ከወላጆቻቸው በተለይም ከአባታቸው ለመንጠቅ ማቆያ ይሠሩላቸዋል እንጂ ወላጆቻቸው ጋር እንዲያድጉ አያደርጓቸውም። በዚያም ልጆች የወላጆቻቸውን እውነት፣ እምነትና እሴት ጥለው የመንግሥት የግል ንብረቱ ይኾናሉ።

ልጆችን ከቤተሰብ ዐውድ አውጥቶ ለመንግሥትና ለድርጅት መጠቀሚያ የማድረግ ሴራ ጥንታዊው የማርክሳውያንና የሶሻሊስት ኮሚኒስቶች ስልት ነው።

እነዚህ ኃይሎች ቤተሰብን እንደ “ከበርቴ” (የቡርዣ) ተቋም በመፈረጅ፣ ልጆችን ገና በለጋነታቸው ከወላጆቻቸው በተለይም ከአባታቸው ግርማና መመሪያ ለመንጠቅ “ዴይ ኬር” ወይም የልጆች ማቆያን እንደ ትልቅ ሥልጣኔ ያቀርባሉ።

🚨 ዓላማቸውም ግልጽ ነው!

🚨 ሸፍጣቸው ግን ስውር ነው!

🚨 ስሙም ሴቷን ማገዝ ነው!

🚨 ነገሩ ግን ወዲህ ነው፦

🚨🚨 ልጆች በቤት ውስጥ የወላጆቻቸውን እምነት፣ እውነትና እሴት ተቀብለው “ልባም ሰው” ኾነው እንዳያድጉ፣ ይልቁንም በሆዳደሩ ሊቃውንት አማካኝነት ከመንግሥት የሚሰጣቸውን ፕሮፓጋንዳ ብቻ የሚጋቱ የሥርዓቱ ቅጥረኛና የግል ንብረት እንዲኾኑ ማድረግ ነው።

በኮሚኒዝም አስተሳሰብ ልጅ የወላጅ ሳይኾን የ”ማኅበረሰቡ” (የመንግሥት) ነው ተብሎ ስለሚታመን፣ ገና መናገር ሳይጀምር ከእናቱ ጡት ተነጥቆ ወደ ማቆያ እንዲወረወር ይደረጋል።

ይህንን የባርነት መመሪያ ለእኛ ሲሸጡልን “ቤተሰብን ለማገዝ፣ ሸክማቸውን ለመጋራት፣ ሴቶች ደመውዝ በማይከፈልበት የቤት ውስጥ ሥራ ታስረው ከሕልማቸው እንዳይሰናከሉ ለመርዳት...” ይሉናል!

ይህንን የሶሻሊስቶች አደገኛ ተሞክሮ ካፒታሊስቱ ዓለም እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ ግኝት ወስዶ ለገበያ ለሕበረተሰቡ ሰጥቶታል።

በዚያም ወላጆች ለሥራና ለገንዘብ ሩጫ ተገደው ልጆቻቸውን ለ”ዴይ ኬር” እንዲሰጡ ሲደረግ፣ ካፒታሊዝሙ በሰው ኃይል ይበለጽጋል፤ ማኅበረሰቡ ግን በሥነ-ልቦና በስብዕናም ይከስማል።

ይህም አስተዋይ ልብ ላለው፣ እውነት ኾኖ፣ ተገልጦም ይታያል!

በዚህ ሂደት ውስጥ ልጆች የሚያድጉት በወላጆቻቸው ሞቅ ያለ ፍቅርና ጥብቅ ሥነ-ሥርባር(ሥነ-ሥርዓት ወ ምግባር) ሳይኾን፣ ለጠላት ላደሩና በገንዘብ ለሚቀጠሩ “ሆዳደር” ሊቃውንት ፕሮፓጋንዳ ተላልፈው በመሰጠት ነው።

በማቆያ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርትና እንክብካቤ የወላጆችን እምነት የሚሸረሽር፣ ባህልን እንደ ኋላቀርነት የሚያጥላላና ትውልዱን ማንነት-ቢስ፣ እሴት አልባ፣ባህል አልባ፣ ትውፊት የለሽ የሚያደርግ መርዝ ነው።

ልጆች የወላጆቻቸውን እውነት ሳይኾን፣ ሥርዓቱ የፈጠረላቸውን፣ የሰፈረላቸውን፣ የበየናቸውንም “ሰው ሠራሽ” ማንነት ተላብሰው እንዲወጡ ይደረጋል።

በዚያም ምን የተማረ ቢኾን ሰውነት ክብሩን፣ ታሪካዊ ማንነቱን የጣለ፣ የጠላና የተጠየፈ አድርባይ፣ አጎብዳጅና ሆዳደር ትውልድ ይፈጠራል።

በዚህ የተሳሳተ መንገድ የሚያድግ ትውልድ መጨረሻው መጥፋትና መምከን ነው። ወላጅ ልጁን በማቆያ ውስጥ ሲጥል፣ ትውልዱን ለባዕዳን ትርክት፣ ለማንነት ክህደት፣ አሳልፎ እየሰጠ መኾኑን አይረዳም።

በዚያ የሚታነጹ ልጆች በአባታቸው ግርማ የማያርፉ፣ ለሕጉ የማይገዙ፣ ለእምነታቸው ደንታ የሌላቸው፣ ለሀገራቸው ወኔ የሌላቸው፣ የእናት ፍቅር የማይገዳቸው ነገር ግን አስመሳዮች ኾነው ይወጣሉ።

የዴይ ኬር ሥርዓት ትውልድን የማምከኛ ፋብሪካ እንጂ ትውልድን ማስቀጠያ፣ ማነጫም ቦታ አይደለም። ልጆች የወላጆቻቸው ቅጂ መኾናቸው ቀርቶ፣ የሆዳደር ሊቃውንት ፕሮፓጋንዳ ውጤት ሲኾኑ፣ ሀገርም ኾነ ቤተሰብ ከልብአልባ ትውልዳቸው የተነሳ መሪ አልባ ይኾናሉ።

ልጅህ የመንግሥት ወይም የድርጅት ንብረት አይደለም፤ የእግዚአብሔር ስጦታና የአንተ ማንነት ቀጣይ ነው። ልጆቻችንን ከማቆያ መርዝ አውጥተን በገዛ እቅፋችን፣ በገዛ እሴታችንና በእምነታችን ካላሳደግናቸው፣ ነገ የሚረከቡን ሀገርና ቤተሰብ አይኖረንም። ትውልድን ማዳን የሚቻለው ከዴይ ኬር ባርነት አውጥቶ ወደ አባወራው ክንድ ወደ እናትም እቅፍ በመመለስ ብቻ ነው!

መንግሥት “ልጆቻችሁን ስጡኝ ላሳድጋቸው” ከማለት ይልቅ፤ “የጠንካራ ስብዕና ባለቤት ኾነው እናንተው ጋር ያድጉ ዘንድ ምን ላግዛችሁ?” ይበለን!

ችግራችንን ተጠቅሞ ልጆቻችንን ባይነጥቀን!

🚨 ወንድሞቼ! ከዚህ አጀንዳ ጀርባ ማርክሳውያን የውጭ ተቋማትና የእኛው ሀገር ሆዳደር ልሂቃንና ሊቃውንት እንዳሉበት በተጨባጭ እናውቃለን!

🚨 🚨 ምዕራባውያን በዴይ ኬር ያሳደጉት ትውልድ የቤተሰብ ትርጉምን አያውቅምና “ቤተሰቤ” የሚላቸው ከእርሱ ጋር በሕጻናት ማቆያ የታጎሩትን ነበርና፤ አድጎ “ሙሉ ሰው” ሲኾን አግብቶ ቤተሰብ የመመሥረት ሂደቱ፣ ጥቅሙ፣ ውጤቱም አይገባውም አይታየውም!

🚨🚨🚨 ስለኾነም የትም፣ ከማንም ይዳራል እንጂ ትውልድን ማስቀጠል አይችልም፣ አልቻለምም፣ አልቻለምምና ዐይናችን እያየ ትውልዳቸው እየጠፋ፣ ማኅበረሰባቸውም እየመከነ ነው!

Post a Comment

0 Comments