በአባወራው የጽድቅ ሥራ አልጫው ይረበሻል!


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ለዘመናት እውነቱ፣ እምነቱ፣ እሴቱ ተበርዞ፣ ተደልዞና ተሰርዞ ልአልባ አልጫ ለኾነው፤ ምን መንፈሳዊ ነኝ ቢል የዓለም አልጫነት ይስማማዋል፣ ጨውነት ጽድቁም ያስቆጣዋል!

ዛሬ ላይ ቆመን ስናስተውል፣ ትውልዱ ኾን ተብሎ “አልጫ” እንዲኾን ተሰርቷል። ይህ ትውልድ ለዘመናት በጆሮው የተጋተው መርዝ፣ አባወራነትን እንደ ወንጀል፣ ወንድነትን ደግሞ እንደ ጭቆና እንዲቆጥር አድርጎታል።

አባወራው “በዝባዥ፣ ጨቋኝ፣ በዳይ ነው” እየተባለ ላደገው የዘመኔ ትውልድ ሚስቱን መምራት፣ ልጆቹን መቅጣት፣ ለቤተሰቡ ራስ መኾን “ኩነኔው” ነው።

ለዘመናት ጽድቅ ይፈጽምበት ዘንድ(ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ቤተሰቡንና ማኅበረሰቡን ከባርነት ነፃ ያወጣበት ዘንድ) አባቱ የሰጠውን ወኔ-ልቡን፣ ጥንካሬ-ጡንቻውን፣ ጉልበት-ኃይሉን፤ ጠላት የላካቸው አስመሳይ አድርባዮች፣ ሆዳደር ባንዳዎች “ስጋ ለበሬ ነው፣ ጡንቻ ላንበሳ ነው” ብለው አኮላሽተውታል።

ዛሬ ሐኪም “ስፖርት ካልሠራህ ልትሞት፣ ልትበሰብስ ነው” ካላለው በቀር ወይ ሰላላ፣ ኮስማና፣ ጎስቋላ ነው፤ አልያም ቦርጫም፣ ዝርጥጥ ዝርፍጥ ነው።

ይህንን ትርክት ተቀብሎ ያደገው የዘመኑ “አልጫ” ወንድ፣ ኃላፊነትን መሸከም ይፈራል። መሪ መኾንን፣ ለመሪነት የሚያበቃው የተሰጠው ጸጋ ላይ መሠልጠንን እንደ ኃጢአት ቆጥሮ ከውጪ ከባዕዳን “የአመራር ሥልጠና” ይቀላውጣል። ቤቱ ሲፈርስ እያየ “ሰላማዊ ነኝ” በሚል የሽንገላ ቃልም ራሱን ያታልላል።

እንዲህ ዓይነቱ አልጫ ግን አባወራው በሰውነቱ ላይ ሠልጥኖ፣ አበልጽጎትና አይሎበት ጽድቅ ሊሠራበት ሲፋጠን “ምን ለስጋው፣ ለሰውነቱ፣ ለዓለም ያደላ፤ ለጠብ የሚጋበዝ...” እያለ ይረበሻል።

አባቶቻችን ሚስታቸውን፣ ልጆቻቸውንና ማኅበረሰባቸውን ከባርነት ነፃ ያወጡበት ዘንድ ፈጣሪ የሰጣቸውን ልብ-ወኔያቸውን፣ ጡንቻ-ጥንካሬያቸውን፣ ኃይል-ጉልበታቸውን ጽድቅ ይፈጽሙበት ነበር።

ዛሬ ግን ጠላት የላካቸው ሆዳደር ባንዳዎችና አስመሳይ አድርባዮች ይህንን ልብ አኮላሽተውታል። “ሥጋ ለበሬ ነው፣ ጡንቻ ላንበሳ ነው፣ ክርስትያን የሚያምረው፣ በጾም ሲከሳ፣ በስግደት ሲጠወልግ ነው” የሚል ያልጮች ትምህርት ዘርተዋል።

🌟 ወንዱ ወኔው ተሰልቦ “ምስኪንና የወጣለት እንከፍ” ሲኾን “እንዴት ያለ መንፈሳዊ ነው” ተባለ፤ ብለውም አያበቁም፤ ጡንቻው የሰለለ፣ ሰውነቱ የተጎሳቆለ፣ ትከሻው የጎበጠ ለንቋጣም ሲኾን ለትውልዱ በተለይም ለወንዱ “አርአያ” አድርገው ያመጡታል እንጂ።

በዚህም ምክንያት ዛሬ የምናየው ወንድ ሰላላ፣ ኮስማና፣ ጎስቋላ ነው፤ አልያም ቦርጫም፣ ዝርጥጥ ዝርፍጥ ነው። ሐኪም ካላዘዘው በቀር ለጽድቁ ሥራ፣ ብቃትና ትጋቱም የሚኾን የሚንቀሳቀስ ጡንቻ፣ ወኔ ኃይልም የለውም!

ሌላ ሰው ትዝ አይበልህ! ራስህን ታዘብ!

አባወራው በሰውነቱ ላይ ሠልጥኖ፣ አባቱ የሰጠውን አቅሙን አበልጽጎና አይሎበት ጽድቅ ሊሠራ ሲፋጠን፣ እነዚያ “አልጫዎች” ይረበሻሉ። አባወራው ለቤተሰቡ ክብር ሲቆም፣ ልጆቹን ለሥነ-ምግባር ሲቀጣና በጠንካራ ስብዕና ሲያንጻቸው፦

“ምን ያካብዳል፣ ምን ለሥጋው ያደላል” ይሉታል። ሰውነቱ የተስተካከለ፣ ቁመናው የሰጠ፣ በጡንቻው ኃይልን የታጠቀ፣ ዓይኑ ንቁና እሳት የለበሰ፣ አረማመዱም የጠነቀቀ ሲኾን፤ “ለዓለም ያደላ፣ ለጠብ የሚጋበዝ...” እያሉ ያሙታል።

ይህ የአልጫ መረበሽ የመነጨው ከገዛ አሰስ (አልጫ፣ ሰነፍ፣ ሰበበኛና ስሜታዊ) ከኾኑበት ድካማቸው ነው። እነርሱ ተፈጥሮአቸውን፣ ጸጋቸውን፣ ወንድነት መክሊታቸውን፣ ማንነት እሴታቸውን የጣሉ አልጮች ስለኾኑ፣ በጨውነቱ መስዋዕት ኾኖ ዓለምን ያጣፍጥ ዘንድ እረፍት ያጣው የአባወራ ጽድቁ ያቃጥላቸዋል። እነርሱ ምን ቢማሩ ከአልጫነታቸው የተነሳ አስመሳይ፣ ሽልጥልጥ አድርባይ ከመኾን ስላላለፉ፣ የአባወራው ጀግንነት ያስቆጣቸዋል።

እውነተኛ መንፈሳዊነት ዓለምን የሚያጣፍጥ ጨውነት እንጂ፣ ከዓለም ጋር በአስመሳይ አድርባይነት አብሮ መዝለፍለፍ፣ መሽለጥለጥ፣ መሽሎክሎክ፣ መርመጥመጥም አይደለም!

አሁንም ሌላ ሰው ትዝ አይበልህ! ራስህን ታዘብ እንጂ!

የአባቶቻችንን ክርስትና ከዓለም ከምንቀላውጠው ከምዕራባውያኑም የሚለየው እንዲህ እውነት፣ እምነትና እሴት የተገመዱበት አርበኝነት የነበረው ስለኾነ ነው።

ዛሬ ግን “መንፈሳዊ ነኝ” የሚለው አስመሳይ ሁሉ የዓለምን ቀላዋጭነት፣ ቀባጭ-ቀላጭነት፣ አልጫነትንም መርጧል። ቆራጥና ቆፍጣና የቃሉ ሰው የኾነውን፤ አባወራውንና የጽድቅ ሥራውን ዕውቅና ከመስጠት ከመከተልም ይልቅ፣ ለጠላት ባርነት የሚያመቸውን የ”ልስልስ፣ ቅልስልስ፣ ኩንስንስ” ክርስትና ማስተዋወቅ ይቀለዋል።

ታናሼ! በአንተ አባወራነት አልጫው ቢረበሽ፣ የቀድሞ ወዳጆችህ ቢቆጡ አትገረም። ጨውነትህ የሚያቃጥለው ባስመሳይነት ወድቆ የቆሰለውን በዘመኑ አሠራር የሠራ አካላቱን ስለኾነ ነው።

ወኔህን በጭራሽ አትስለብ! ጡንቻህን ለጽድቅ አዘጋጅ! ሚስትህን፣ ልጆችህን ቤተሰብህን በኃይልና በሥልጣን ምራ! ከዚህ በተቃራኒው “መንፈሳዊነት ነው” እያሉ የሚነግሩህ አልጫነትክን አጽድቀው በባርነት ሊሸጡህ የሚያስማሙህ ሸቃጮች ናቸው!

“ዐለም ተረበሸች፣ ኑሮ ተወደደ፣ መንግሥት ተገለበጠ፣ ክርስቶስ ሊመጣ ነው...” ይሉሃል እንደ እነርሱ ከዓላማህ ተናጥፈህ፣ ከአባትህ ፈቃድ ወጥተህ እንድታዝን፣ እንድታላዝን፣ እንድትነፋረቅ።

አንተ ግን ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ! ርቦሃል አዎን፣ ደክሞሃል በርግጥ ነገር ግን የመጣህበትን ጉዳይ ልትፈጽም አለህና፤ ለእርሱም ትበቃ ዘንድ በሰውነትህ ላይ ሠልጥነህበታልና ደረትክን ነፍተህ፣ ካንገትህ ቀና ብለህ ዓይኖችህ ከአባትህ ተክለህ፣ ዓላማህን ሰቅለህ ትጓዛለህ!

ዓለም ያልጮች ናት! የሚያላዝኑ የሚነፋረቁትን፣ የሚያስመስሉ የሚሽለጠለጡትን ትመርጣቸዋለች። አልጫዋ በጨዉ ቢጣፍጥም እርሷ ግን ምርጫዋ “ምንጊዜም አልጫ!” ነው!

ይኹን እንጂ እርሷ ጣዕም የምታገኘው አባቶችህ በሄዱበት ፈለግ ተከትለህ፣ አባትህ በሰጠህ ጸጋ በልጽገህ፣ ጽድቁን የምትፈጽምበት ዐለምን የምታጣፍጥበት ጨውነትህን ስትገልጥ ብቻ ነው! ለእርሱም ምስጋና አትጠብቅም ግዳጅህ ነውና!

ይህ እምነቱን ከልቡ፣ እውነቱን ከቃሉ፣ እሴቱን ከኑሮው ሳይለይ ባንድ በራሱ አስባብሮ፣ አዛምዶ፣ አሰናስሎ የሚገኘው አርበኛዊው፣ ኢትትዮጵያዊው አባወራነት ነው!


Post a Comment

0 Comments