እርግዝና በሽታ ወይስ በረከት

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ራስን በወሊድ መከላከያ ማምከን፣ ውርጃም የጤና አገልግሎት እንደኾነ እየተነገራቸው ከሚያድጉት ልጆቻችን የሀገር ጥፋቷ እንጂ ልማቷ እውን አይኾንም!

ለአባወራ ተከታዮችና የሴቶች ልጆቻችሁ፣ እህቶቻችሁ፣ ሚስቶቻችሁና እናቶቻችሁ ጤንነት ለሚገዳችሁ ሁሉ!

በፋብሪካዎቻችን ደጃፍ፣ በማህበረሰባችንም በራፍ ላይ “የሥነ-ተዋልዶ ጤና” በሚል ለጆሮ ደስ በሚል ስም የሚቸረቸሩት አገልግሎቶች፣ ግባቸው የሴቶችን ጤና መጠበቅ ሳይኾን ትውልድን ለፋብሪካ ማሽንነት (ለአምራችነት) ምቹ አድርጎ መቅረጽ ነው።

በተለይ በግብረ-ሰናይ ስም የመጣው ግብር የማይከፍል ሱቅ ያለው “የትውልድ ነጋዴ” በሴቶቻችን ማህፀንና በልጆቻችን የወደፊት ተስፋ ላይ ቁማር እየተጫወተ ይገኛል።

እነዚህ የትውልድ ነጋዴዎች እርግዝናን እንደ ስጋት፣ እንደ ሥራ መስተጓጎል እና እንደ ድህነት ምንጭ አድርገው ይስሉታል።

አንዲት ሴት በወጣትነት አቅሟ፣ በለምለም ዘመኗ (በእነርሱ ግን በምርታማነት ዘመኗ) ሙሉ ትኩረቷን ለፋብሪካው ብቻ እንድትሰጥ ሲሉ፣ ተፈጥሮአዊ የእናትነት ጸጋዋን እንደ ሸክም እንዲታያት ያደርጋሉ።

🚨 እርግዝና በረከት እንጂ በ”ጤና አገልግሎት” ስም የሚታከም “በሽታ” ተደርጎ ማስትሬትና ዶክትሬት በጫኑቱ የተቆጠረው መቼ ነው?

የወሊድ መከላከያ የጤና አገልግልት፣ ውርጃ ደግሞ የሕጻናትን ነፍስ ማጥፋት መኾኑ ቀርቶ “መብት ነው” ተብሎ ልጆቻችን በሚማሩበት፣ የትውልዱን ልማት፣ የማኅበረሰቡም መስፋት እንዴት ይጠበቃል?

ሴቶች ልጆቻችን የሚሠሩባቸውን መሥሪያ ቤቶች በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩትን እስቲ ጠይቁ?

“ጤንነታቸው የሚጠበቅላቸው” በምንም ምክንያት (እርግዝናንና ወሊድን ጨምሮ) ሳያቋርጡ አምራች ሠራተኛ እንዲኾኑ ነው።

በሥራ ቦታቸው የሚሰጣቸው፣ ከጠዋት እስከማታ በትልልቅ ስክሪንና ድምጽ ማጉያ የሚለፈፍባቸው “የጤና ጥበቃ ማስታወቂያ”፤

ለሴቶች የቆምን ነን ለሚሉ ግብር ለማይከፍሉ “የግበረሰናይ” ሱቅ ያላቸው ተቋማት ተሰጥቶ በየቀኑ ወደ ሥራ ከመሠማራታቸው በፊት እርግዝናን ስለማስቀረትና ስለ ውርጃ እንደሚጋቱ ታውቃላችሁ?

ለዚሁ ዓላማ በተለይ የተቋቋሙ ግብር የማይከፍሉ በ”ግብረሰናይ” ስም የተከፈቱ ሱቆች እንዳሉንስ? ሴቶቻችንን “የሥነ-ተዋልዶ ጤናና መብቱ” እያሉ የሚያጨናግፉበት መመሪያም ጭምር እንዳላቸውስ?

ባለፈው የእነዚህ ግብር የማይከፍሉ “ግብረሰናይ” ሱቆች የሚሠሩትን ሥራ ለኤግዚብሽን ባቀረቡበት መድረክ ተገኝታችሁ “በጄ” እያለችሁ ብትሰሙ ይህንኑ ትረዱ ነበር።

ምን ያክሎቻችሁ ጎበኛችሁ?

በቲቪ ስክሪንና በድምፅ ማጉያ ጠዋትና ማታ “ውርጃ የጤና አገልግሎት ነው” የሚል መርዝ የሚጋቱ ልጆቻችን፣ ነገ ቤተሰብ የመመሥረትና ትውልድ የመተካት ወኔ-ፍላጎታቸው እንዲሰለብ እየተደረገ ነው።

በተጨማሪም የወሊድ መከላከያው እዛው በፋብሪካው ውስጥ በቀላሉ ከነአጠቃቀሙ ይቀርብላቸዋል። ለምን? “ከአላስፈላጊ እርግዝና” እንዲጠበቁ፤ “አላስፈላጊ እርግዝና” ቢከሰትስ ለሱም መፍትሔ አለ የታወቁና የተመሰከረላቸው የሕጻናቱን ነፍስ(ጽንሱን) በመርዝ በጣጥሰው በመቀስ ቆራርጠው የሚያጠፉና የሚያስወርዱ እንዳሉም ይነገራቸዋል።

ይህ የሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነታቸው የሚረጋገጥበት፤ የትውልድ ነጋዴዎች ግብር የማይከፍሉ ግብረሰናይ ሱቆች ገበያ ነው።

ለእነርሱም በመከራ ያሳደግናቸውን ልጆች እንገብራለን!

በዚህ አገልግሎት ሴቷ፦

1ኛ ለፋብሪካው ቋሚና “ያለ መስተጓጎል” የምታመርት ማሽን ትሆንለታለች። በትዳር፣ በእርግዝና፣ በወሊድ፣ በጡት ማጥባት አትቀርበትም!

2ኛ ለሀገር ግን ተተኪ ዜጋ፣ ትውልድ የሚጠፋበት፣ ማኅበረሰብ የሚመክንበት፣ አረጋውያንን የሚረከብ ወጣት የሚታጣበትና ሀገር የምትፈርስበት የጥፋት መንገድ ነው።

ይህ አሠራር የቀድሞዎቹን የሶሻሊስት ሀገራት አሳዛኝ ታሪክ ያስታውሰናል። በዚያ የጨለማው ዘመን መንግሥት ሴቶችን ለፋብሪካ ምርት ሲል ከቤት አውጥቶ፣ ልጆቻቸውን የእነርሱ እስካይመስሉ አባትም እናትም እርሱ ኾኖ በፋብሪካ ማቆያ እያሳደገ፣ ቤተሰብንና ማህበራዊ ትስስርን አውድሞ ነበር።

እኛም ጋር በልማትና ብልጽግናው ካባ ተጠቅልሎ የመጣው ይሄው አጀንዳ፣ እናትነትን ከሴቷ ለይቶ፣ ልጆችን ለተቋማት አሳልፎ በመስጠት “የማህበረሰብ መካንነትን” እየፈጠረ ነው።

ይህንን ኮሚኒስት የነበሩት ሀገራት በዚያ ማርክሳዊ ሶሻሊዝም ወደ ኮሚኒዝም በሚገሰግስበት የጨለማ ዘመን በሴቶቻቸው ላይ ተመሳሳይ ግፍ ሲፈጽሙ እንደ ነበር ከዚህ በፊት ነግሬያችኋለሁ።

ይህ ዛሬም በእኛ ሀገር “ለሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነት ቆመናል” በሚሉ ባፍጢም በተደፉ ልሂቃንና ሊቃውንት ያውም በሴቶቹ በሴቶች ወገኖቻችን ላይ ይፈጸማል።

🚨 ሴቶቻችን ያለባቸውን ይህንን መከራ ማን ይኾን የሚሟገትላቸው?

🚨🚨 የሴቶች “መብትና ነፃነት ተማጋች ነን” የሚሉት ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት ተሰሚነት ያላቸው ልሂቃንና ሊቃውንትማ ለጠላት አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል።

🚨🚨🚨 በቃ እናንተ ይህንን የምታነቡትም እህት እናት ሚስት ልጅ የላችሁምን ወይንስ እናንትም እንደ እነዚያው የወጣላችሁ አስመሳዮች ናችሁን?

ይህንን በግብረ-ሰናይ ስም የመጣ፣ ነገር ግን ግብር የማይከፍል የትውልድ ነጋዴ ሥራ የምንመክተው በጠንካራ የቤተሰብ እሴት ብቻ ነው።

ሴቶቻችን ከፋብሪካ አምራችነት በላይ ቤተሰብ የመመሥረቱ፣ የእናትነቱና ትውልድን የማነጹ ክብር እንዳላቸው ሊረዱ ይገባል።

ቤተሰብ መመሥረት የኋላ ቀርነት ሳይኾን የሥልጣኔና የሰው ልጅ ህልውና መሠረት መኾኑንም እኛ ልናስተምር፣ ከእነዚህ ሆዳደር አጥፊዎቻቸውም ልንጠብቃቸው ይገባል።

ልጆቻችን ስለ ራሳቸው ማንነትና ተፈጥሮአዊ ጸጋ ትክክለኛውን እውቀት እንዲያገኙ በማድረግ ከባዕድ አጀንዳዎች ልንጠብቃቸውና ልንታደጋቸው ይገባል።

ፋብሪካው ምርቱን፣ ነጋዴው ትርፉን ይቆጥራል፤ እኛ ግን የምንቆጥረው የሚተካውን፣ የሚቀጥለውን፣ የሚያስቀጥለውን ትውልድ ነው። ትውልዳችን በፋብሪካ ምርት መስመር ላይ ደርቆና መክኖ እንዲቀር አንፍቀድ!

ሀገር የምትለማው በታታሪ ሠራተኛ ብቻ ሳይኾን፣ የተገነባውንና የገነባውን የተቀበለውንም

👉 እውነት እምነቱን፣

👉 ማንነት እሴቱን፣

👉 ሀገር ድንበሩን የሚቀበልና የሚያስቀጥል ጠንካራ ቤተሰብና ማኅበረሰብም መመሥረት በሚችልና በሚተካ ትውልድ ጭምር ነው!

ሴቶቻችን በእኩልነት መብትና ነፃነት ሰበብ ቤተሰብ እንዳይመሠርቱ፣ ወልደውም በስብዕናው ጠንካራ የኾነ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዳያንጹ እየተደረገ ነው።

ይህ በቀላል ምርመራ የታዘብኩት ሲኾን ጠለቅ ያለ ጥናት በእነዚህ ፋብሪካዎች ላይ ቢደርግ ግን እንደምሰማው ከኾነ ከዚህም የከፋ በደል ይፈጸምባቸዋል፤ ያውም በግብረሰናይ ስም ማስትሬትና ዶክትሬት በጫኑ ሴቶች!

ከዚህ ጋር የተያያዘ የሰማችሁት ወይም የምታውቁትስ ምን አለ?

Post a Comment

0 Comments