ወሲብን ከትዳር፣ ትውልድንም ከማፍራት መለየት!

ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

“የሥነ-ተዋልዶ ትምህርት” ተብሎ ለልጆቻችን የሚሰጠው፤ ልጆች ወሲብን ቤተሰብ ከመመስረት፣ ትውልድን ከማስቀጠል፤ ማኅበረሰብን ወደሚያመክን ራስወዳድነት እንዲወስዱት ያደርጋቸዋል።

ዛሬ በምዕራባውያኑ ዘንድ (Compulsory Sexual Education ወይም Comprehensive Sexuality Education- CSE)፣ “የሥነ-ተዋልዶ ጤና” ወይም በቆንጆ ቃላት “የሕይወት ክህሎት” እየተባለ ለልጆቻችን የሚሰጠው ትምህርት፣ ግቡ ትውልድን ማነጽ ሳይኾን የቤተሰብን መሠረት መናድ ነው።
ይህ ትርክት ወሲብን ቤተሰብ ከመመሥረት፣ ልጆችን ከመውለድና ትውልድን ከማስቀጠል ቅዱስ ዓላማው ለይቶ፣ ወደ ግላዊ ስሜትና መብት ብቻ ዝቅ ያደርገዋል።

ምዕራባውያኑ ይህንን መንገድ ተከትለው ማኅበረሰባቸውን አምክነዋል፣ ራሳቸውን አጥፍተዋል፣ ከእነርሱ ስሕተት አለመማር ደግሞ እብሪት (arrogance ) ይባላል።

ወሲብ ትዳር የሚጸናበት፣ ቤተሰብ የሚመሠረትበት፣ ትውልድ የሚቀጥልበት፣ ማኅበረሰብ የሚገነባበት መኾኑ ቀርቶ “ተፈጥሮአዊ ፍላጎት” እና እንደ “ግል ነፃነት” ተቆጥሮ የሚፈጸምበት ይኾናል።

በዚያም ወሲብ ኃላፊነት ያለበት ጋብቻ መሥርቶ ትውልድ የሚቀጠልበት መሣሪያ መኾኑ ቀርቶ፣ ከማንም ጋር የትም የሚፈጸም “መዝናኛ” ኾኗል።

በውጤቱም ኃላፊነት የማይሰማው ወሲብ፣ አባት የሌላቸው ልጆችን፣ የፈረሱ ቤተሰቦችንና በብቸኝነት የሚማቅቅ ማኅበረሰብን ፈጥሯል።

የምዕራባውያን ትምህርት ወጣቱ “የራሱን ሕይወት እንዲኖር፣ ራሱን ያማከለ፣ ራሱን ብቻ የወደደ፣ ራስወዳድ ሕይወት” ይሰብካል።

ይህም ወጣቶች ጋብቻን እንደ የነፃነታቸው ገዳይ፣ ልጅ መውለድን ደግሞ እንደ ኢኮኖሚ ሸክምና እስር እንዲያዩት ተደርገዋል።

ስለኾነም ዛሬ በብዙ የምዕራባውያን አገራት ከሚወለደው ሟቹ በልጧል። የሚወልድ ትውልድ ጠፍቶ አገራቱ በሽማግሌዎች ተሞልተዋል፤ ማኅበረሰቡም በቁጥር ስብጥሩ እየመከነና እየጠፋ ነው።

ትምህርቱ “የእኔ አካል የእኔ መብት” በሚል መሪ ቃል፣ ግለሰቡ ለማኅበረሰቡና ለትውልዱ ያለበትን ግዴታ እንዲረሳና ግለኛ እንዲኾን ይደርገዋል።

ይህ በራስ-ወዳድነት የተለመደ መዳራት በምዕራባውያን ዘንድ “ዝሙትን” እንደ ሥልጣኔ፣ ፅንስ ማቋረጥን(ውርጃን) እንደ መብት፣ ጋብቻን ደግሞ እንደ ኋላቀርነት አስቆጥሯል።

በዚያም ትውልድ የሚተካበት የተፈጥሮ መንገዱ(ጋብቻና መውለዱ) ተዘግቶ፣ ማኅበረሰቡ “በሕይወት እያለ የሞተ”፣ የመኸነም ኾኗል።

🚨 እኛም ጋር እንዲሁ እየኾነ ነው!

ወሲብን ከጋብቻና ከትውልድ ማፍራት ሲለዩት፣ ቀጥሎ የሚመጣው የማንነት ቀውስ ነው። ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ወንድነቱንና ሴትነቱን የጠላ፣ ተፈጥሮውን የካደና “ስልብ” የኾነ፣ ዘሩን የማይተካ፣ ለመተካትም ወኔ የሌለው ጃንደርባ ትውልድ የበዛው የዚህ “ትምህርት” ሰለባ በመኾኑ ነው።

አባወራነትንና እናትነትን የናቀ፣ እንደ እንሰሳት ከመዳራት ውጪ አእምሮዉን፣ ልቡን መጠቀም ያልቻለ ትውልድ፣ መጨረሻው ለማንም የማይበጅ “አልጫ” ኾኖ ጠፊ ነው።

ወንድምዓለም! ይህ “የሥነ-ተዋልዶ ትምህርት” በ”የሕይወት ክህሎት” ስም ወደ እኛም ቤት ሰርጎ እየገባ ነው። ዓላማው ልጆቻችንን እንደ አባቶቻቸው ባለ ግርማ አባወራ እንዳይኾኑ፣ ይልቁንም ወሲብን በጋለ ስሜታቸው፣ ባልሠለጠኑበት ብልታቸውን የሚዳሩበት ብቻ እንዲኾኑ ያደርጋል።

ስለ ልጆቻችን የሚገደን መች ይኾን?

ምዕራባውያን በዝምታቸው ጠፉ፣ ከሰውነት ወጥተው፣ ከእንሰሳነትም አልፈው፣ ትውልዳቸውም ከእብደቱ የተነሳ ጠፋ፣ ማኅበረሰባቸውም መከነ!

ነግ በእኛ በሉ!



Post a Comment

0 Comments