የሀገር ውድቀቷ ከድንበሯ ሳይኾን ከእሴቷ ይጀምራል!


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ሰውነትን የገነባ፣ ማንነትን የበየነ፣ ሥነ-ሥርዓትና ሥነ-ምግባርን ያስተማረ እሴት “በሊቃውነቱ”፦ ስር የሰደደ ጨቋኝ አባወራዊ ሥርዓት፤ ሲባል የሀገር ውድቀቷ መነሻ ይኾናል።

ሀገር በድንበርና በወታደር ብቻ አትጠበቅም፤ ይልቁንም በጽኑ እውነትና በጠንካራ ስብዕና ላይ በተገነባ “ልቦና” ሰውነትም እንጂ!

ይህንን የትውልዱን ልቦና የመጠበቅ፣ የመመገብና “መልካም፣ ልክ፣ ተገቢና ውብ” በኾነው የማነጽ ኃላፊነት ደግሞ የእነርሱ የምሁራን፣ የሊቃውንቱ ነው።

ነገር ግን ምሁሩ ጽድቅ የሚሠራበት ልቡ ከአእምሮው ጋር ተስተካክሎ ሳያድግ ቀርቶ አስመሳይ አድርባይ ባደረገው ጠባዩ “አሞራን ጅግራ” እያለ መሸጥ ሲጀምር፣ ሀገር ወደ ውድቀት፣ ትውልድም ወደ ጥፋት ገደል ይገፋሉ፣ ይጣላሉም።

እናት፦ ወላጅ እናት፣ ቤተክርስትያን፣ ሀገር፤ ልጇን ያስተማረችው ከራሱ አልፎ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለእሴቱ እንዲጠቅም እንዲጨምር ነበር።

ነገር ግን የዛሬው ምሁር ማስትሬትና ዶክትሬቱን የውጭ አጀንዳዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ሰርገው የሚገቡበት “ጥናታዊ ጽሑፍ፣ አጀንዳ” መሥሪያ አድርጎ ተጠቀመበት።

በዶላርና በፓውንድ የሚከፍሉ NGOዎች የሚሰጡትን መመሪያ ያለ ምንም ትችት (Critical thinking) የሚቀበል “ምሁር” ለገንዘብ ባርነት ያደረ፣ ከሕሊናው ይልቅ ጥቅሙን ያስቀደመ እርሱ ነው።

ምሁሩ የሚያውቀውን እውነት ሳይኾን፣ የሚከፈለውን “ትርክት” ያስተምራል። አጥፊ እንደኾነ እያወቀ “እድገት-መብት ነው” ይላል፤ ገዳይ እንደኾነ እያወቀ “ሕይወት-ዘመናዊነት ነው”፣ ትውልድ እንደሚሰልብ ሲያውቀው “ልምላሜ-መንፈሳዊነት ነው” ሲል ይዋሻል።

ይህ አስመሳይነት፣ ሆዳደርነት፣ ምንደኝነት፣ አድርባይነት፣ ባንዳነት፤ ምሁሩን፣ ሊቁን፣ ሊቀ-ሊቃውንቱን በአፉ(በአፍአ) ለሀገሩ የቆመ አስመስሎ ነገር ግን ከሀገሩ አውጥቶ አርቆም የባዕዳን ሎሌ አድርጎታል።

ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት ያሉ ምሁራን “የጾታ እኩልነት” እና “ጸረ-ጾታዊ ጥቃት” በሚሉ መርሐግብሮች እየተከፈላቸው፣ የኢትዮጵያዊቷን ሴት ማንነት ለማጥፋት፣ ከቤተሰቧም ለመለየት፣ ከፈጣሪዋም ለማቆራረጥ ይሠራሉ፤ በሚከፈላቸውም ገንዘብ ቤት ይሠራሉ፣ ሆዳቸውን ይሞላሉ.... ትውልድ ግን ይጠፋል።

ነገር ግን “አዋቂ፣ ታዋቂም” ናቸውና ማንም አይወቅሳቸውም፤ እንዳውም እነርሱ ያስተማሩት፣ ያስከተሉት፣ የመረቁት ሁሉ የእነርሱን ፈለግ በመከተል፣ እንደ እነርሱ ትውልዱን “በሁለት ወገን በተሳለ ሰይፉ” አጋድሞ ለመንጨት ለመጋጥም የሚያስችሉትን ግብር የማይከፍሉ “ግብረሰናይ” ሱቆችን የሚከፍትበት ዕቅድ “project” ለማጸደቅ ይቸኩላል እንጂ!

ሴቷን ከአባቷ ሥርዓት፣ ከባሏ ጥበቃና ከእናታዊ ጸጋዋ፣ ተፈጥሮዋ እንድትለይ “በመብት” ስም፦

🚨 መማር አለብሽ፣

🚨 መሥራት አለብሽ፣

🚨 ትዳር የት ይሄድብሻል፣

🚨 ማግባትን ማን ይወስድብሻል፣

🚨 መውለድንስ ማን ይነጥቅሻል፣

🚨 ይልቅ ከባልሽ እኩል ወጥተሽ ብትገቢ ይበጅሻል፤

🚨 ተይ ኋላ ይቆጭሻል፤

🚨 በጊዜሽ፣ እንደጊዜው ብትኾኚ ይሻልሻል፤

🚨 ከወንዱ እኩል ለመኾን ምን ያንስሻል፤

🚨 እንዳታረግዢ ክኒን መቃም ይቻልሻል፤

🚨 ብታረግዢም በጣጥሰውና ቆራርጠው ያወጡልሻል፤.... እያሉ ይሰብኳታል።

ጋብቻን እንደ “ጭቆና”፣ ዝሙትንና ፅንስ ማስወረድን ግን እንደ “ነፃነትና ዘመናዊነትም”፣ አመጸኝነትንም እንደ ልከኛ መንፈሳዊነት አድርገው “በከፍተኛ የጥናት ጽሑፎች፣ ሴሚናሮች፣ ሥልጠናዎችና የፖሊሲ ምክረሃሳቦች” ያቀርባሉ።

(በአንድ ወቅት አንዱን “Podcaster” በዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ አጠናለሁ እባክህ በትውልዱ ላይ ያንጃበበውን የጥፋት አደጋ በማስረጃ በተደገፈ ተጨባጭ መረጃ እነግረው ዘንድ አቅርበኝ ስለው፤ “የታተመ ‘Journal’ አለህ ወይ” አላለኝም! ልክ ባሳተሙት “Journal” ክብደትና ይዘት እንግዶችን የሚያቀርብ ይመስል!

ይህንንም ታነበው ይኾናል! ውርድ ከራሴ!

የትውልዱን ጥፋት እያዩ፣ እያወቁ እውነትን በዝምታ ያለፉ፣ የሸፈኑ፣ ያስቀሩ፣ የደበቁ፣ የቀበሩቱ ካጥፊዎቹ ቢከፉ እንጂ በምን ይተናነሳሉ?!)

በዚህ ሸፍጥ እናትነቷን የናቀች፣ የጠላች፣ የተጠየፈች፤ ስለኾነም የወርአበባ “ሳታይና” ሳታረግዝ፣ ሳትወልድና ሳታጠባ፣ ልክ እንደወንዱ ከእርሱ “እኩል” ከትምህርቷ በትዳርና በልጆች ሳትጨናገፍ የምትኖር ሴት፤

አንድም ትዳሯ የፈረሰና ልጆቿን ያለ አባት በማሳደግ፣ የፈረሰ ቤተሰብ የምትስልላቸው ለባዕድ ርዕዮተ-ዓለምም የተጋለጠች፣ የተጠለፈች ሴት ትፈጠራለች። ሴቷ ስትጠፋ ደግሞ ቤተሰብ ትውልድም ይጠፋል፤ ቤተሰብ ሲጠፋ ልጆች ሲበተኑ ሀገር ትወድቃለች።

ምሁራኑ ለወንዱ የሚግቱት “ዘመናዊነት” ወንድነቱን የሰለበ ነው!

🚨 ቆራጥ አባወራነትን እንደ “ኋላቀርነት” እና “አምባገነንነት” ይፈርጁታል፤ ወንዱ በገዛ ቤቱ ላይ ሥልጣንና ሥርዓት እንዳይኖረው “ምስኪን” ኾኖ እንዲያድግ፣ ካገኘ በልቶ ካጣ ተደፍቶ የሚያድር “እንከፍ” እንዲኾን ይደሰኩራሉ።

🚨 ምሁሩ ራሱ ለሆዱ አድርባይ በመኾኑ፣ ትውልዱንም “አጎብዳጅና አስመሳይ” እንዲኾን በአርአያነቱ ያሰለጥነዋል። ለእውነት የማይቆም፣ ለጽድቅ የማይጨክን፣ ለፍትሕ የማይሟገት፣ በአቋሙ የማይጸና ስልብ፦ ጃንደርባ ትውልድ የሊቃውንቱ የአድርባይነት ፍሬ ነው!

እነዚህ ሊቃውንት ሀገርና ቤተክርስቲያን ባስተማሯቸው እውቀት፣ የገዛ እናት፦ ሀገራቸውን ቤተክርስትያናቸውን፤ ጡት ነካሽ ናቸው!

የአባቶቻቸውን ገድል፣ ተጋድሎ እነርሱ ከማውራት የዘለለ “በእጃቸው ጨብጠው፣ በእግራቸው ተራምደው፣ በምላሳቸው ቀምሰው” አይኖሩትምና “አፈ-ታሪክ” ይሉታል።

አባቶቻችን ትናንት የመጡበትን፣ ትውልዱ የሚታነጽበትን፣ ማንነቱ የሚበየንበትን፦ እምነቱን፣ እውነቱን፣ እሴቱን “ባህል” ብቻ አድርገው ያጣጥሉታል፣ ያቃልሉታል፣ ያቀሉታልም!

በምትኩ፣ ለሀገር የማይበጅና ለትውልድ የማይመጥን፣ የማይሄድ፣ ባዕድ የውጭ “አሞራ” እያመጡ “ጅግራ ናት” እያሉ አርደውና በልተው፣ አብስለውና ፈትፍተው ሕዝቡን ያበሉታል።

ትውልዴም መብሉ በሆዱ፣ ኧረ ገና በጉሮሮውም ሳለ ወደ ጥፋትና ሞቱ ቸኮለ! በጥርጣሬና በፉክክር ተለያየ፣ ከሕብረት ራቀ፣ ከአንድነት ተለየ፣ ውሕደቱ የማይታሰብ ኾነ፦ ቤተሰብ መሥርቶ፣ ትውልድ አፍርቶና አንጾ መኖር ተረት፣ የሕልም እንጀራም ኾነበት!

ይህ ሁሉ ውድቀት በዘመኔ፣ አሁን ባለንበት ጊዜና ዘመን ባሉ ምሁራን፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት በኾኑትም፣ የትውልዱን ልቦና በዚያም ሀገርን ከክፉና አጥፊ ሃሳብ ሊጠብቁ፣ በመልካሙም ሊያንጹት በሚገባቸው ተፈጸመ!

ምሁራን ለእውነት መቆም ሲያቅታቸውና ሆዳቸውን ከጽድቁ ሲያስቀድሙ፣ ሀገር በመሪና በአስተማሪ እጦት ትታወራለች። ዛሬ የምናየው ማኅበራዊ ቀውስ፣ የሞራል ውድቀትና የቤተሰብ መፈራረስ ምንጩ እነዚህ “አዋቂ ነን” ባይ በልተው የማይጠግቡ፣ ጠግበው የማይረኩ አድርባዮች ናቸው።

ሀገር የምትድነው፣ ምሁሩ ከምንደኝነት ወጥቶ የአባቶቹን ፈለግ ሲከተል፣ እውቀቱን ለሆዱ ሳይኾን ለትውልዱ ድኅነት፣ ለሀገር ልማትና ብልጽግና ሲያውል ብቻ ነው።

እነዚህ “አሞራን ጅግራ” የሚሉ ነጋዴዎችን ለይቶ ማወቅና ቤተሰቡንና ማኅበረሰቡን ከእነርሱ ተውሳክ ነገቀርሳም ከኾነ “ትምህርት ስብከታቸው” መጠበቅ የአባወራው ድርሻ ነውና ይህ ንቅናቄ አስፈለገ!

Post a Comment

0 Comments