ትውልዱ የአባቶቹን እምነትና እሴት እንዲጠላ የሚያደርጉት እውነትን ሸቅጠው በአስመሳይነት የሚነግዱበት “የአምልኮ መልክ” ያላቸው ዓይነ ደረቆች ናቸው። እነርሱ ትውልድ አጥፊ አስመሳዮች Hypocrite ናቸው!
እንዲህ ያለው አስመሳይነት ስር ከሰደደ፣ ራስን ካልተቀበለ፣ ነገር ግን ታይታና ይኹንታን በእጅጉ ከፈለገ፣ ዋጋውንም በዚያ ከተመነ፣ ይህንንም እንደመንፈሳዊነት አጽድቆ ከተወዘተ ምስኪናዊነት ይመነጫል። ስለ ምስኪንነት ባወራንባቸው በብዙ ጽሑፎች ውስጥ ይህንን ትረዳላችሁ።
ከዚያ በበለጠ ደግሞ በአባወራ ሥልጠናችን የመጀመሪያውና ሰፊው ክፍል እንዲህ ዓይነቱን በዘመናዊነት አሳቦ የገባን ምስኪንነት፣ በመንፈሳዊነት አሳቦ የተጣባንን አስመሳይነት ከውሳጥችን ነቅሎ የሚጥል ነው!
በመንፈሳዊነት ሰበብ የሚደረግ አስመሳይነት ማህበረሰቡ በእውነተኛ እሴቶች ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ያደርጋል። ሰዎች “መንፈሳዊ” የሚባሉ ሰዎችን መጠራጠር ሲጀምሩ፣ ትክክለኛው የሞራል ግንባታ፣ የትውፊት ቅብብሎሽ አደጋ ላይ ይወድቃል።
ትውልዱ እነዚህን የእውነት፣ የእምነት፣ የእሴትም ጠባቂና መምህር አድርጎ የሚያያቸው ሰዎች፤ ታይታና ይኹንታን ሲፈልጉ የማይኖሩትን እውነት፣ የሚኖሩትንም ሐሰት ለስሜት ደስ እንዲል አድርገው በነዚህ ተቋማትና ማኅበራት ስር ተጠልለው ሲያቀርቡት ሲናገሩት ሲያይ ትውልዱ ከተቋማቱና ከማኅበራቱ ይቀራል።
ተቋማት በተለይም የሃይማኖቱ የአስመሳዮች ማኅበር፣ የአደርባዮች “መናኃሪያ”፣ የሆዳደሮችም “የግል ንብረት” (Full of hypocrite) ሲኾን ትውልድን ያርቃል፣ ያደርቃልም።
አንድም በቅዱሱ ቦታ “አንተ ሐጢያተኛ ተመለስ” መባልን በግልጥ ባይጠይቅም፤ ማንነቱን እያወቁ ገንዘቡን የሚሹት ግን “አንተ ጻድቅ፣ ቅዱስና ደግ ሕዝብ” እያሉ እንዲነግዱበትም አይፈልግም፤ ስለኾነም በአስመሳዮች ከተሞላው ተቋምና ማኅበር ሲርቅ አንገረም!
እነዚህን ሰዎች ስናይ እግዚአብሄር ይህን ሁሉ እያየ እያወቀም በእኛ ላይ ያበዛውን ቸርነቱንና ትዕግስቱንም እጅግ እናደንቃለን።
☀️ ግሩም ድንቅ ነው ትዕግስቱ! ምስኪን ይወድቅበታል እንጂ በእብሪቱ!
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮማውያን በላከው ክታቡ እንዲህ ይላል፦
“ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?” ሮሜ 2፥4
ብዙዎች ፦
👉 በአስመሳይነት ከወጡበት፣
👉 ተቀባይነት ካገኙበት፣
👉 ገንዘብም ከሚያገኙበት ማማ መውረድ ይቸገራሉ።
አንዳንዴም ያገኙትን የሰው “ተቀባይነት” ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር አገናኝተው በዚያው በአስመሳይ በአድርባይነታቸው እስከ “የእናት ጡት ነካሽ” ባንዳነት (የክህደት ድፍረት) ድረስ ተጠርንገው ይጠፋሉ።
“እውነትን ብናገር ጥቅሜ ይቋረጣል፣ ጭንብሌን ባወልቅ ክብሬ ይረክሳል” በሚል ስሌት፣ እግዚአብሔር የሰጣቸውን የንስሐ ጊዜ ለተጨማሪ ድራማና ንግድ፤ ጨርሰውም እስከመጥፋት ይጠቀሙበታል።
🚨 ይህ የቸርነቱን ባለጠግነት መናቅ ነው! ፈጣሪ የታገሰህ እንድትመለስ እንጂ እንድትነግድበት አይደለም!
ነገር ግን እንዳንተ ዓይነት ምስኪንነቱ ያየለበት፣ እንከፍነቱ የገነነበት ንክር አስመሳይ፣ የሰውን ጭብጨባ ከፈጣሪ ፍርድ አስበልጦ ስለሚመርጥ፣ በገዛ እብሪቱ ገደል እስኪገባ ድረስ በውሸት ማማው ላይ ተንጠልጥሎ ይኖራል።
የአስመሳዮች ትልቁ መሸሸጊያ የእግዚአብሔር “ዝምታ” ነው። እግዚአብሔር ስለታገሳቸው ብቻ የያዙት መንገድ እውነት፣ የለበሱት ጭንብልም ጽድቅ ይመስላቸዋል። ይህ ግን የቸርነቱ ውጤት እንጂ የእነርሱ ትክክለኛ ማንነት መገለጫ አይደለም።
አንተም በአስመሳይነት በምትዘራበት የእግዚአብሄርን ቁጣ በአናትህ ላይ እየከመርክ እንደኾነ እወቅ! በ”ዝምታው” ፈቃድ ስምምነቱ ሳይኾን የቸርነቱ የትዕግስቱ ባለጠግነቱ እንደኾነ አውቀህ፣ አንተም ወድቀህ ልጆቹን ከምትጥልበት እብሪትህ ተነስተህ ንስሃ ግባ!
በቤቱ ልጆቹን የሚያጠፉ ምንደኛ አስመሳይ ሊቃውንት ሲበዙ ስታይ፤ ተስማምቶት፣ ፈቅዶላቸው፣ ልኳቸውም ሳይኾን የንስሃ ጊዜ ሰጥቷቸው እንደኾነ ተረድተህ ሕይወት መቅረዝህን ሳትነጠቅ በፊት ደግሜ እነግርሃለሁ፦ ንስሃ ግባ!
እኛ ግን ቤተሰባችንን፣ ልጆቻችንን ከእናንተ በሁለት ወገን ከተሳለ፣ ትውልድን የሚግጥ የአስመሳዮች ስለት መጠበቅ ግዴታ ኃላፊነትም አለብንና እንታደገው ዘንድ እውነቱን እንዘራለን!
በምስኪንነት በተለይም በመንፈሳዊነት “ካባ” ከወደቅህበት አስመሳይነት ውጣ! ባለቤት አባትም አለውና ትውልዱ ላይ አትቀልድ!
በምትመክረው ትምህርት መጀመሪያ ተመከር! ከምታስተምረው ትምህርትም ተማርና በሕይወትህ ፍሬ አፍራ! በአስመሳይነት ተገልጠህ ከማውራትህ በፊት!
0 Comments